የኢትጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌድዮን ጤሞትዮስ ከጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ ጋር ተነጋገሩ። ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኦማር ጌሌህ ጋር የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት እና ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ባለስልጣናቱ በተለይ 17ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ትኩረት በተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ አጽንዖት መስጠታቸውንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌድዮን አስቀድሞ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድም ከእስማኤል ሀሰን ጉሌህ ጋር መነጋገራቸውን የሶማሊያ መንግሥት የሚቆጣጠረው ሶና የዜና ወኪል ዘግቧል። ኢትዮጵያ የወደብ እና የባህር በር የሚያስገኝላትን ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ ጋር ከተፈራረመች ወዲህ ጂቡቲ የታጁራ ወደቧን አልምታ ኢትዮጵያ እንድትገለገልበት መጋበዟ ይታወሳል።
የግብጽ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት የደረሱበትን ሥምምነት “በቅርብ እየተከታተሉ” እንደሚገኙ ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።
ፕሬዝደንቱ ሥምምነቱ “በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ጸጥታ እና መረጋጋት ለማስፈን አስተዋጽዖ ያበረክታል” የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ በአንካራ ተገናኝተው ወደፊት ለመደራደር የደረሱበት ሥምምነት “ከዓለም አቀፍ ሕግ መርኆዎች ጋር የተስማማ ይሆናል” ብለው እንደሚጠብቁ ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ መናገራቸውን በጽህፈት ቤታቸው በኩል የወጣ መግለጫ ይጠቁማል።
አል-ሲሲ በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አስተያየት የሰጡት ትላንት ቅዳሜ ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ነው። ከግብጹ ፕሬዝደንት በስልክ የተነጋገሩት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ባለፈው ሣምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መነጋገራቸው አይዘነጋም።
ሁለቱ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ መሠረት በቱርክ አመቻቺነት ድርድሩ በመጪው የካቲት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ሀገራቱ ድርድሩን በበአራት ወራት ውስጥ አጠናቀው ለመፈራረም ዕቅድ አላቸው።
ቻዳዉያን ዛሬ የፓርላማ ተወካዮቻቸውን ሲመርጡ ውለዋል።
ሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተሳተፉበት ምርጫው የፕሬዚዳንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ወደ ህገመንግስታዊ ስረዓት የሚያደርጉትን ሽግግር አቅም ሳይፈጥርላቸው አይቀርም ተብሏል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ልጅ የሆኑት ማህማት ከሶስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ በኋላ በአነታራኪ ምርጫ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ነበር የሀገሪቱ ፕሬዚደንት መሆናቸውን ያረጋገጡት ።
በሀገሪቱ በአስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የህግ አውጪዎች ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኤስ ኤም ቲ መሪ እና ሌሎች በርካታ ፓርቲዎች አስታውቀዋል። ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በተሰጠው የድምጽ አሰጣጥ የከተማ እና የክልል መስተዳድሮች አባላት ምርጫ ተካሂዷል። ዉጤቱም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይፋ ይደረጋል ፤ ተብሏል።
የምዕራባዉያን ጠንካራ አጋር የነበረችው ቻድ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ትብብር አፍርሳለች። በተጨማሪም ከቀጣናው ህብረ ብሄራዊ ወታደራዊ ትብብር ራሷን ልታገል እንደምትችል አስጠንቅቃለች
ለ181 ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነው የደቡብ ኮሪያው የአውሮፕላን አደጋ በወፎች መንጋ ምክንያት ሳይከሰት እንዳልቀረ ባለሞያዎች አመለከቱ ።
በአውሮፕላኑ የበረራ መስመር የወፎች መንጋ መከሰቱን የበረራ መቆጣጠረያ ክፍል ለአብራሪው ካሳወቀ በኋላ አደጋው መድረሱ ተገልጿል። ባለአንድ ሞተሩ ቦይንግ 737/ 800 አውሮፕላን ከበረራ መስመሩ ውጭ ማረፊያ ባልነበረበት አካባቢ ለማረፍ ሲሞክር መከስከሱን እና በእሳት መጋየቱን በማህበራዊ መገናኛ ገጾች ሲንሸራሸሩ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አመልክተዋል። አውሮፕላኑ ከታይላንድ ወደ ደቡብ ኮሪያ ይበር እንደነበር ተገልጿል። በአደጋው የበረ,ራ ሰራተኞችን ጨምሮ አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 181 ሰዎች ህይወት አልፏል። አውሮፕላኑ ለመከስከሱ በርግጥ በወፎች መንጋ ተመትቶ ይሁን ወይም ሌላ ምክንያት ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ደቡብ ኮሪያ በአደጋው ምክንያት ለጠፋው የዜጎቿ ህይወት የ7 ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጃለች ።
መነሻዋን ከሰሜናዊ ፈረንሳይ ያደረገች እና ስደተኞችን ጭና ወደ እንግሊዝ ልትሻገር የሞከረች ጀልባ በደረሰባት አደጋ በትንሹ ሶስት ሰዎች ሞቱ ።
ሌሎች በርካቶች ላይ ጉዳት ደርሷል። ዛሬ ማለዳ ወደ እንግሊዝ ለመድረስ በጉዞ ላይ በነበረችው ጀልባ ላይ ለደረሰው አደጋ በባህር ላይ የነበረው መጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የፈረንሳይ የድንገተኛ አገልግሎት አስታውቋል። አደጋውን ተከትሎ በአካባቢው የደረሰው የህይወት አድን ቡድን የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጧል። በአደጋው ብርቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሌሎች አራት ሰዎች በሄሊኮፕተር ወደ ህክምና መውሰዳቸውንም ገልጸዋል። ጀልባዋ ወደ እንግሊዝ ጉዞ ከመጀመሯ አስቀድሞ 50 ያህል ሰዎች አሳፍራ እንደነበር የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል። ጀልባዋ በዚህ በመጥፎ የአየር ሁኔታ ወቅት እንዴት ጉዞ እንዳደረገ,ች ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ የሀገሪቱ ዓቃቢያነ ህግ ተናግረዋል ። መነሻቸውን ከሰሜናዊ ፈረንሳይ ያደረጉ እና ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ሙከራ የሚያደርጉ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ማሻቀቡን ዘገባው አመልክቷል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ