መቃዲሹ፤ የሶማሊያ የወረራ ክስና የኢትዮጵያ ማስተባበያ
የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ጦር በድንበር አካባቢ ባሉ ሁለት ከተሞች ላይ ጥቃት አድርሶብኛል ሲል ከሰሰ። የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ ትናንት ከቀትር በፊት በዶሎ እና በጁባላንድ ከተሞች ላይ መፈጸሙን አመልክቷል። ጥቃቱ በሦስት የጦር ሰፈሮች ላይ መድረሱንም ገልጿል። በተጠቀሱት የጦር ሰፈሮችም የሶማሊያ ጦር፤ የፖሊስ እንዲሁም የስለላ እና የጸጥታ ተቋም ባልደረቦች የሚገኙበት መሆኑንም ጠቅሷል። የሶማሊያ ክስ የተሰማው የመቃዲሹ እና አዲስ አበባ መሪዎች በአንካራ ቱርክ ላይ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላ ነው። ከሶማሊያ ባለሥልጣናት የተሰማውን ክስ አስደንጋጭ ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የቀረበው ክስ ሀሰት ነው ሲል ዛሬ ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ አስተባብሏል። የተባለው አጋጣሚም የሶማሊያ እና ኢትዮጵያን ጤናማ ግንኙነት ለማበላሸት ባለሙ ኃይሎች የተፈጸመ ነውም ብሏል። እነዚህ ኃይሎችም የአፍሪቃውን ቀንድ ለማተራመስ ያቀዱ ናቸው ሲልም በበኩሉ ሦስተኛ ወገን ያላቸውን ኃይሎች ከሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ግብፅ የአፍሪቃ ሕብረት በሶማሊያ ለሚያሰማራው የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ለማዋጣት መዘጋጀቷን ትናንት አስታውቃለች። ግብፅ ወታደሮቿን የምትልከው በሶማሊያ መንግሥት ጥያቄ መሠረት መሆኑንም ገልጻለች።
ዶሀ፤ ቀጠር ሶርያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ባስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቀች
ቀጠር ሶርያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ባስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቀች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጅድ አል አንሳሪ በዛሬው ዕለት ባቀረቡት ጥሪ፤ ሶርያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ምክንያት የሆነው አሁን ስለሌለ ማዕቀቡ ባስቸኳይ መነሳቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
«የቀጠር አቋም በዚህ ጉዳይ ግልጽ ነው፤ ማዕቀቦች ለመጣል ምክንያት የነበረው ነገር አሁን ስለሌለ እና ወደዚህ እርምጃ ያመራው ወንጀሎችን የፈጸመው የቀድሞው አገዛዝ ፈጽሞ ስለተወገደ ማዕቀቡን ባስቸኳይ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ይህ ማዕቀብ ለመጣሉ ማሳመኛ የነበረው ምክንያት አሁን የለም፤ በመሆኑም አሁን ማዕቀቦቹን ለማንሳት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ይሆናል።»
ማዕቀቡ ይነሳ የሚለው የቀጠር ሃሳብ የቀረበው ከፍተኛ የልዑካን ቡድኗ ደማስቆን በጎበኘ ማግስት መሆኑ ተገልጿል። ከ13 ዓመታት መለያየት በኋላ ዳግም ከሶርያ ጋር ግንኙነቷን ያደሰችው ቀጠር ኤምባሲዋንም ባሳለፍነው እሑድ ዕለት ዳግም ከፍታለች። አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደዘገበው ከሆነ ዶሀ በሽር አሳድን ከሥልጣን ያስወገዱትን አማፅያን ከሚደግፉ የውጭ ኃይሎች አንዷ ናት።
ሞስኮ፤ የሩሲያ ዕቃ ጫኝ መርከብ ስፔን አቅራቢያ ሰመጠች
16 ሰዎች አሳፍራ የነበረች አንድ የሩሲያ ዕቃ ጫኝ መርከብ ስፔን አቅራቢያ መስመጧ ተሰማ። ከተሳፋሪዎቹ ሁለቱ አልተገኙም። መርከቧ የሰመጠችው ሞተሯ ውስጥ የተከሰተውን ፍንዳታ ተከትሎ መሆኑን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋግጧል። ዑርሳ ማጆር የተሰኘችው መርከብ ሶርያ ውስጥ ለሚገኙ የሩሲያ ወታደሮች ዕቃ ጭና በመንገድ ላይ እንደነበረች የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ በዘገባው ጠቅሷል። ትናንት እኩለ ቀን ገደማ በሜዲትራኒያን ዓለም አቀፍ የባሕር ግዛት መርከቧ ላይ አደጋ መድረሱን ተከትሎ ሕይወት ለማዳን የስፔን የባሕር ኃይል እና የደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአካባቢው ተሰማርተው 14ቱን ተሳፋሪዎች ማዳን ተችሏል። ቀይ መስቀል በበኩሉ ተጨማሪ እርዳታ ለመስጠት ሀኪሞችና የስነልቡና ባለሙያዎቹን መላኩ ተገልጿል።
ዋሽንግተን፤ የአሜሪካ አየርመንገዶች በረራ መቋረጥ
የአሜሪካ አየር መንገድ ጠቅላላ በረራዎቹን የቴክኒክ ችግር ባለው ምክንያት ማቋረጡን ዛሬ አስታወቀ። አውሮፕላን ውስጥ ከተሳፈሩ በኋላ በመላው አሜሪካ ተፈጠረ በተባለው የቴክኒክ ችግር ምክንያት እንዲወርዱ የተጠየቁት መንገደኞች ቅሬታቸውን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እየገለጹ ነው። ለፈረንጆች ገና ዋዜማ ወደየቤተሰቦቻቸው ለመጓዝ ያልቻሉት አብዛኞቹ መንገደኞች በረራው ዳግም መቼ እንደሚጀምር እንዳልተነገራቸው ነው ዘገባዎች ያመለከቱት። አውሮፕላኖቹ ዛሬ ማለዳ ጀምረው ባሉት በረራዎች ጠቅላላ የቴክኒክ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል። የመንገደኞቻችን ደኅንነት ቀዳሚው ጉዳያችን ነው ያለው የአሜሪካ አየር መንገድ ችግሩ መፍትሄ እንዳገኘ አገልግሎቱ እንደሚቀጥል አስታውቋል። አየር መንገዱ የቴክኒክ ቡድኑ ችግሩን ለማስወገድ እየሠራ መሆኑን ቢያመለክትም፤ መቼ የሚለውን አለመመለሱ በዓልን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመሆን ለተመኙ መንገደኞችን ግራ እንዳጋባ ነው የተነገረው። አንዳንዶቹም የኮምፕዩተር ችግር መሆኑን እየጠቆሙ ነው።
ዶሀ፤ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የቀጠለው የተኩስ ማቆም ድርድር
በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ድርድር መቀጠሉን ቀጠር አስታወቀች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ድርድሩ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ መቼ ከስምምነት ይደረሳል የሚለውን ለመናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማጅድ አል አንሳሪ፤
«ድርድሩን በተመለከተ፤ ጋዛ ላይ ተኩስ እንዲቆም ድርድሮቹ ቀጥለዋል። እንደምታውቁት በአሁኑ ጊዜ ቴክኒካዊ እና የድርድር ሂደቶች እዚህ ዶሃ በመካሄድ ላይ ናቸው። በተጨማሪም፤ በተለያዩ አውዶች ካይሮ ላይ በሌላ መስመር እየተሠራ ነው። እንደምትረዱት፤ በግብፅ አረብ ሪፐብሊክl በወንድሞቻችን ትብብር እየቀጠለ ነው። በዚህ መስመር የተለያየ ሚና ሲኖር ዋናው መስመር ድርድር ነው።
ትናንት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋዛ ላይ የተኩስ አቁም ለማድረግና ታጋቾችን ለማስለቀቅ የተጀመረው ንግግር አንዳንድ ለውጥ እያሳየ ነው በማለት ጠቁመዋል። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ማለቂያ ገደማ ሀማስ 250 ሰዎችን ማገቱን ተከትሎ እስራኤል ጥቃት መጀመሯ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ዛሬ ምሽት በቤተልሔም ለሚከበረው የፈረንጆቹ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በከተማዋ ዝግጅት ሲደረግ መዋሉን የከተማዋ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ ለወትሮው በዚህ የበዓል ወቅት ከተማዋን ያደምቁ የነበሩ የገና ዛፍና መብራቶች እንደሌሉ ነው አሶሲየትድ ፕረስ ከስፍራው በላከው ዜና ያመለከተው። የበዓሉ ድባብም መቀዛቀዙን አክሏል።
አምስተርዳም፤ ኔዘርላንድ ውስጥ እስራኤላውያን ላይ በተፈጸመው ጥቃት አምስት ጥፋተኛ ተባሉ
የኔዘርላንድ ፍርድ ቤት ባለፈው ወር በእስራኤላውያን የእግር ኳስ ደጋፊዎች ላይ አምስተርዳም ስታዲየም ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት አምስት ተከሳሾችን ጥፋተኛ ናቸው አለ። ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት ተከሳሾቹን የማክቢ ቴል አቪቭ ቡድን ደጋፊዎችን ከመመደብደብ አንስቶ በበርካታ ወንጀሎች ነው ጥፋተኞች ያላቸው። ፀረ ሴማዊ ድርጊት ተብሎ በተወገዘው ጥቃት በተሳተፉት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ቅጣት የስድስት ወር እስራት መሆኑ ተገልጿል። የስድስት ወር እስራት የተፈረደበት ከድርጊቱ ተሳታፊዎቹ አንዱ ሰፋ ኦ ተብሎ የተጠቀሰው ግለሰብ ነው። አቃቤ ሕግ ግለሰቡ የሰዎችን ጭንቅላት እና አካል በመደብደብ ወንጀል ግንባር ቀደም ነው ሲል ከሷል። ሲደበድብ የሚያሳይ መረጃም ለፍርድ ቤት አቅርቧል። በእስራኤላውያኑ ላይ በተፈጸመው ድብደባ ሀኪም ቤት እስከመግባት የደረሱ መኖራቸው ተነግሯል። ሁለት ቀናት በዘለቀው ግጭት የማካቢ ቴል አቪቭ ቡድን ደጋፊዎችም ፀረ አረብ ዘፈኖችን ማሰማታቸውን፤ ታክሲ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውና የፍልስጤምን ሰንደቅ አላማ ማቃጠላቸው ተገልጿል። ፖሊስ ከሁለቱም ወገን በድርጊቱ የተሳተፉ የ45 ሰዎችን ጉዳይ መመርመሩን አስታወቋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ