ሀዋሳ፤ ሲዳማ ክልል በመኪና አደጋ የ71 ሰዎች ሕይወት አለፈ
በሲዳማ ክልል በደረሰ የመኪና አደጋ የ71 ሰዎች ሕይወት አለፈ። የተጎዱም አሉ። አደጋው የደረሰው ትናንት ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ በክልሉ ምሥራቃዊ ዞን ቦና ዙሪያ ወረዳ ውስጥ ነው። አደጋው የተከሰተው በአይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ተሳፍረው ከቦና ወደ በንሳ ሲጓዙ በነበሩ የሠርግ እድምተኞች ላይ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
ድልድይ የጣሰው ተሽከርካሪ በደረሰበት አደጋ 71 ሰዎች ወዲያውኑ መሞታቸውን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአደጋው የተጎዱ አራት መንገደኞች በወረዳው ጤና ተቋማት የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ኮሚሽነር ሽመልስም አክለው ገልጸዋል።
ክስተቱ በክልሉ የትራፊክ አደጋ ታሪክ ዘግናኝ ነው ያሉት የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዳንቾ በበኩላቸው የአደጋው ሰለባዎች ሴቶን ሙሽራ ለማምጣት መንገድ ላይ እንደነበሩ ነው የገለጹት።
ናይሮቢ፤ ኬንያ ውስጥ እገታ እንዲቆም ለተቃውሞ የወጡ በርካቶች ታሠሩ
ኬንያ ውስጥ መንግሥትን የሚተቹ ወጣት ዜጎች ላይ ያነጣጠረ እገታ እንዲቆም ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ በርካቶች ታሠሩ። በዛሬው ዕለት ናይሮቢ ከተማ ከታሰሩት መካከል ተቃዋሚ የፖለቲካ አባልም ይገኙበታል። ሴናተር ኦኪያ ኦምታታ፤ ዋና ከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ተቀምጠው መንግሥት ባለፈው ወር ያገታቸውን ሰባት ሰዎች እንዲለቅ ድምፅ ሲያሰሙ ከነበሩት ጋር አብረው እንደነበሩ አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል። ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ቢተኩስም የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ባለመንቀሳቀሳቸው እንዳሰራቸውም አመልክቷል።
የኬንያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሐሙስ ዕለት መንግሥትን የሚተቹ በርካቶች ይታገታሉ መባሉ ስጋቱን ከፍ እንዳደረገው አመልክቷል። እንደ ኮሚሽኑ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ እስካሁን የታገቱት ቁጥር 82 ደርሷል። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በበኩላቸው ቅዳሜ ዕለት ወጣቶች በሰላም እንዲኖሩ መንግሥት እገታውን ያስቆማል ማለታቸውም በዘገባው ተጠቅሷል። የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከእገታው ጀርባ የፖሊስ እጅ እንዳለ ይጠረጥራሉ።
ትሪኒዳንና ቶቤጎ፤ በወንጀል መጨመር ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ታወጀ
የወንጀል ድርጊት በመጨመሩ ምክንያት ትሪኒዳድና ቶቤጎ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ታወጀ። የቬንዙዌላ ጎረቤት የሆነችው የካረቢያን ደሴቷ ሀገር ፕሬዝደንት በዛሬው ዕለት የሕዝቡን ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ባሉት የወንጀል ድርጊት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ማወጃቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የወጣው መግለጫ ያመለክታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በዚሁ መግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው ፖሊስ በሰጠው ምክር መሆኑን አስታውቋል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በሀገሪቱ ምሥራቅ ምዕራብ ኮሪደር አካባቢ በወሮበሎች በተሰነዘረ ጥቃት ትናንት ማምሻውን የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። ቅዳሜ ዕለትም እንዲሁ አንድ ሰው በጥይት መገደሉም ተገልጿል። በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 ባጠቃላይ ከ600 ሰዎች በላይ መገደላቸው ነው የተነገረው። ምንም እንኳን ቀደም ባሉት ዓመታትም መንግሥት ወንጀሎችን ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም ተባብሶ መቀጠሉ የሀገሪቱን መንግሥት እንዳሳሰበው ተገልጿል።
ዋሽንግተን፤ የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ተጨማሪ የ2,5 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ መፍቀዱ
ተሰናባቹ የአሜሪካን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ተጨማሪ የ2,5 ቢሊየን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ መፍቀዱ ተነገረ። ባይደን ከነጩ ቤተመንግሥት በመጪው ጥር ወር ከመሰናበታቸው አስቀድሞ በሩሲያ ጥቃት ስር የምትገኘው ዩክሬንን የመከላከል አቅም ለማጠንከር ማለማቸው ተገልጿል። በኮንግረስ ይሁንታ ያገኘው ይኸው እርዳታ 1,25 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶችን እንዲሁም ተጨማሪ 1,22 ቢሊየን ዶላር የደኅንነት ድጋፍን ለማቅረብ ያለመ መሆኑን የ ዋይትሀውስ መግለጫ ያመለክታል። የጀርመን የዜና ወኪል ዲፒኤ እንደዘገበው ባይደን አስተዳደራቸው ኮንግረሱ ለዩክሬን ያጸደቀውን የድጋፍ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ቁርጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል። በባይደን የሥልጣን ዘመን ፤ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተችበት ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ ዋነኛዋ የኪዩቭ ደጋፊ ሀገር ናት። ሆኖም ግን ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ሊለውጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለም ዘገባው ጠቅሷል።
ሞስኮ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን የጦር እስረኞችን ተለዋወጡ
በተባበሩት አረብ ኤሜሬት አደራዳሪነት ሩሲያ እና ዩክሬን የጦርነት ወቅት እስረኞችን መለዋወጣቸውን ሩሲያ አስታወቀች። ሮይተርስ ከሞስኮ የሩሲያን የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው እያንዳንዳቸው 150 የጦር እስረኞችን ለሌላቸው ሰጥተዋል። በዚሁም መሠረት የሩሲያ እስረኞች ቤላሩስ ግዛት ውስጥ የተለቀቁ ሲሆን ወደ ሩሲያ እንደሚወሰዱ ተገልጿል። የጦር እስረኞች ልውውጡ ሂደትም በተባበሩት አረብ ኤሜሬት አማካኝነት መከናወኑንም መግለጫው አመልክቷል።
ዋሽንግተን፤ 39ነኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
39ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። መቶ ዓመታቸው ነበር። ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሀገራቸው ታላቅ ሰው አጣች በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
«ይህ የሀዘን ቀን ነው፤ ሆኖም መልካም ትዝታዎችን የምናስብበት ድንቅ አጋጣሚ ነው። ዛሬ አሜሪካና ዓለም በእኔ እይታ ትልቅ መሪ አጥተዋል። የመንግሥት መሪ እና ሰብአዊነት የተላበሱ ሰው ነበሩ። እኔ እና ጂል ደግሞ ውድ ጓደኛችንን አጣን። ለ50 ዓመታት ከጂሚ ካርተር ጋር አብሬ ነበርኩ። ለበርካታ ዓመታት ስለብዙ ነገሮች ተወያይተናል። ይቀልዱብኝ ነበር፤ በ1976 ለፕሬዝደንት ድምፅኔን ሰጥቼቻቸዋለሁ። ለዚህ ደግም በርካታ ምክንያቶች አሉ። ባሕርያቸው! ስለጂሚ ካርተር ካስገረሙኝ ነገሮች አንዱ፤ በመላው ዓለም ሚሊዮኖች በአካል አግኝተዋቸው ባያውቁም እንኳን የግል ወዳጃቸውን እንዳጡ ነው የተሰማቸው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጂሚ ካርተር በወሬ ብቻ ሳይሆን ቃላቸውን በተግባር የኖሩ በመሆናቸው ነው።»
ከእሳቸው አስቀድመው የአሜሪካን ፕሬዝደንቶች የነበሩት እንዲሁም የተለያዩ ሃገራት መሪዎችም በየበኩላቸው የሀዘን መልእክቶችን አስተላልፈዋል። እስካሁን ባለው ታሪክ ረዥም ዕድሜን የኖሩት ብቸኛው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ላለፉት 22 ወራት ገደማ የህክምና ክትትል በቤታቸው ሲደረግላቸው መቆየቱን አሶሲየትድ ፕረስ ዘትቧል። ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰንን ከሥልጣን ባስወገደው የዎተርጌት ቅሌት በመባል በታወቀው የአሜሪካ ፖለቲካዊ ቀውስ ማግሥት ፕሬዝደንት የሆኑት ካርተር በሥልጣን ዘመናቸው ግብፅና እስራኤልን ለማስማማት ባከናወኑት የሰላም ጥረት ይታወሳሉ። በጎርጎሪዮሳዊው 1924 ዓ,ም የተወለዱት ካርተር፤ በወጣትነታቸው የባሕር ኃይል አካዳሚ ገብተው፤ በዘርፉ አገልግለዋል። የአባታቸውን ሞት ተከትሎም ለበርካታ ዓመታት የቤተሰባቸውን የኦቾሎኒ እርሻ በማስተዳደርም በገበሬነት ቆይተዋል። ለአንድ ዘመነ ሥልጣን አሜሪካንን ያስተዳደሩት ጂሚ ካርተር ወዲያው ወደ ሰብአዊ አገልግሎት ነው ፊታቸውን ያዞሩት። ከባለቤታቸው ጋር ካርተር ማዕከልን በማቋቋም በመላው አለም ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት እና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲሰፍን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይነገርላቸዋል። በትዳር ሕይወት ለ77 ዓመታት የኖሩት ጂሚ ካርተር 33 መጽሐፎችን ጽፈዋል። ባለቤታቸው ሮዛሊን ካርተር ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር በ96 ዓመታቸው ነው ቀድመዋቸው ያረፉት። የአራት ልጆች አባት የሆኑት ጂሚ ካርተር የበርካቶች አያትና ቅድመ አያትም ሆነዋል። ቀብራቸው ከ10 ቀናት በኋላ ይፈጸማል።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ