የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔና የኢሰመጉ ጥሪ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26 2015በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና የተፈጠሩ ችግሮችን መንግስት አጣርቶ ጥፋተኛዎቹን ለይቶ ፍትሀዊ ውሳኔ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠየቀ። ኢሰመጉ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በፈተናው ወቅት በፀጥታ ችግርና በድልድይ መደርመስ ደረሰ ያለው የተማሪዎች ሞት ተጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድም አሳስቧል። በሌላ በኩል ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የሕግ ባለሞያ የኢትዮጵያ ትምሕርት ሚኒስቴር ፈተና አቋርጠው የወጡ ተማሪዎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ጥቅል ነው ሲሉ ተችተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ ትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ቀደም ሲል በሕገወጥ መንገድ ይወጣ እንደነበርና ይህን ችግር ለመከላከል ተማሪዎቹ በየዩኒቨርሲቲዎች እንዲፈተኑ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ይሁን እንጂ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች በተሰጠው የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ከዩኒቨርሲቲዎች የተወሰኑ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይፈተኑ መቅረታቸውን አስታውሷል፡፡ኢሰመጉ “በመቀደላ አምባ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደብረ ታቦር እና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ፈተናውን ሳይፈተኑ የወጡ ተማሪዎች ሳይፈተኑ የወጡበትን ምክንያት በተገቢው ሁኔታ በማጣራት እነኚህ ተማሪዎች ለቤተሰብም ለሀገርም ሀብት በመሆናቸው ጥፋተኛ ተማሪዎችን በሚገባ በመለየት ፍትሀዊ የሆነ ውሳኔን እንዲሰጥ” ሲል ጠይቋል፡፡በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር አንድ ተማሪ መገደሉን ያስታወሰው የኢሰመጉ መግለጫ ጉዳዩ ምርመራ ተደርጎ አስፈላጊው ህግዊ እርምጃ እንዲወሰድም አሳስቧል፡፡በተመሳሳይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በድልድይ መደርመስ የአንድ ተማሪ ህይወት ያለፈ ሲሆን ግንባታውን ካከናወኑና የጥራት ማረጋገጫ ከሰጡ፣ እንዲሁም በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ላይ ተገቢ ምርመራ በማድረግ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች አስፈላጊው ህክምና እንዲደረግላቸውና የፈተና ጊዜ እንዲመቻችላቸውም ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ሰሞኑን ለብዙሀን መገናኛ በሰጡት መግለጫ በራሳቸው ፈቃድ ፈተና ያቋረጡ ተማሪዎች በመደበኛ ተማሪነት እንደማይፈተኑ ገልፀዋል፡፡
“ ፈተና አንፈተንም ብለው ጥለው ወጡ ተማሪዎችን በተመለከተ ዳግም በመደበኛ ተማሪነት የመፈተን እድል የማይሰጣቸው ሲሆን በግላቸው በ2015 ዓ ም የትምህርት ዘመን የመፈተን መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡” ነው ያሉት፡፡
የአማራ ተማሪዎች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት እሸቱ ጌትነት ትምህርት ሚኒስቴር ምክንያቶችን ሳያጠና በጅምላ የወሰደው ያለውን እርምጃ ተቃውሟል፡፡
“ እነዚህ ልጆች ከዚህ በኋላ ከትምህርቱ ዓለም አያስፈልጉም የሚል ውሳኔ ነው የተቀመጠው እንጂ ምክንያቱን እነዚህ እነዚህ ነገሮች ትክክል ስላልነበሩ ብሎኮ ትክክል ያልሆኑ ምክንያቶች እንኳ ማግኘት እኮ አልቻልንም እንኳን ከአንድ ተቋም አንድ ግለሰብ እንኳ ውሳኔ ለመወሰን በጣም ብዙ ሂደቶችንና እርቀቶችን ይሄዳል፣ መጀመሪያም ትክክል አይደልም ትክክልም ሊሆን አይችልም፣ እንኳን የአንድ አገሪቱ ተቋም ይቅርና ሌለም ነገር ቢሆን ይህንን ነገር ሊወስን አይችልም፡፡”
በሕግ ሙያ ረጅም ልምድ ያላቸው የሕግ፣ የሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መርሐጽድቅ መኮንን ትምህርት ሚኒስትር አንድ እርምጃ ወደፊት ጉዳዩን ቢመለከተው የተሸለ እንደሚሆን ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡
“ሚኒስቴሩ የወሰደው እርምጃ አስተዳደራዊ ነው፣ ስህተት የፈፀሙ ተማሪዎች አሉ፣ ከ12ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች እንደዚህ ባለ ህይወትን በሚመለከት ጉዳይ ላይ ተሳስተውም ይሁን አንዳንዶቹ ከመካከላቸው አጥፍተው በራሳቸው ላይም እርምጃ ቢወስዱ ይህ በራሳቸው ላይ የወሰዱት እርምጃ አንደምታው አብሮ መታየት አለበት፣ እንደዚህ ባለ ጊዜ ሁለቴ ቆም ብለህ ማየት ይኖርብሀል፣ በግል ይፈተኑ ፣ሙሉ በሙሉ አይፈተኑም ስትል ፊት ለፊት ስታየው ትክክል ነው፣ አንፈተንም ብለው ነው የወጡት፣ አንፈተንም ብለው ከወጡ ትምህርት (ሚኒስቴር) ምን ማድረግ ነበረበት የሚል መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ፣ ራሳቸውን ብቻ የሚመለከት አይደለም፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ይመለከታል፣ ማህበረሰቡን ይመለከታል፣ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄደህ ማጣራት ይኖርብሀል፡፡”
ኢሰመጉ ያወጣው መግለጫም በተመለከተ አቶ መርሐጽድቅ፣ …ይህ ሁሉ በጅምላ ሲወጣ ሁሉም ጥፋተኛ ነው ብለህ አትወስድም፣ ምን ዓይነት የተሳሳተ መልዕክት ቢደርሳቸው ነው፣ እንዲህ ኣይነት እርምጃ ሊወስዱ የቻሉት በራሳቸው ላይ የሚኒስቴሩ እርምጃ ትንሽ ምርር ያለ ይመስላል፣ ሁለተኛ እንዲያየው ማድረግ ያስፈልጋል፣ አጣርተህ በጥቂቶች ላይ እርምጃ ካልወሰድህ በስተቀር አብዛኛው ላይ ተመሳሳይ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የመንግስትና የዜጎች ግንኙነት አደጋ ላይ ይወድቃል በአገር ላይም ኪሳራ ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ማጣራት የሚለው (የኢሰመጉ መግለጫ) ተገቢ ነው፣ ችግር ፈጠሩት ጥቂት ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ እስከተቻለ ድረስ አንድ እርምጃ ሄደህ ብታጣራ ነው እንጂ የሚሻለው እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ተገቢ አይደለም፡፡”
በዚህ ወር መጀመሪያ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ማህበራዊ ፈተና በአማራ ክልል በሚገኙ 4 ዩኒቨርሲቲዎች ለፈተና ከተቀመጡት መካከል 12 ሺህ 993 ተማሪዎች ፈተና አቋርጠው መውጣታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዮ ለገሠ