1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሥራ አጥነት በትግራይ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2016

በትግራይ ያሉ ወጣቶች በስራ ዕድል መጥፋት እና የተለያዩ ድጋፎች እጦት ያማርራሉ። በመቐለ እና ሌሎች የትግራይ ከተሞች መታዘብ እንደሚቻለው በርካታ ወጣቶች ከስራ ውጭ ናቸው፣ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ግዚያቸው በስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ እንዲሁም የተለያዩ የዕድል ጨዋታዎች በማካሄድ ማሳለፍ የተለመደ ሆንዋል።

https://p.dw.com/p/4arhO
ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎችን ሲከታተሉ
ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎችን ሲከታተሉ-መቀሌምስል Million Hailesilasse/DW

የትግራይ ሥራ አጥ ወጣቶች ፈተና

በትግራይ ጦርነቱ ከቆመ ከዓመት በላይ ቢቆጠርም፥ እስካሁን በርካታ ነገሮች ሳይቀየሩ ቀጥለዋል። በተለይም በትግራይ ያሉ ወጣቶች በስራ ዕድል መጥፋት እና የተለያዩ ድጋፎች እጦት ያማርራሉ።

በመቐለ እና ሌሎች የትግራይ ከተሞች መታዘብ እንደሚቻለው በርካታ ወጣቶች ከስራ ውጭ ናቸው፣ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ግዚያቸው በስፖርታዊ ጨዋታዎች ውርርድ እንዲሁም የተለያዩ የዕድል ጨዋታዎች በማካሄድ ማሳለፍ የተለመደ ሆንዋል።

የቀድሞዉ የህወሓት ተዋጊዎች አቤቱታ

በመቐለ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ወጣቶች እንደሚሉት በተለይም ከጦርነቱ በኃላ በትግራይ የስራ ዕድል መጥፋት፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አለመመለስ፣ እንዲሁም አስፈላጊ የፋይናንስ ይሁን የስነልቦና ድጋፍ ማጣት ከባድ ሕይወት ላይ እንዲወድቁ እንዳደረጋቸው ይገልፃሉ። 

የ32 ዓመት ወጣት ቢንያም ገብሩ "አንፃራዊ ሰላም እንኳን ቢኖር ወጣቱ ግን እስካሁን ምንም ያገኘው ነገር የለም። የስራ ዕድል ፈጠራ የለም፣ ብድር የለም፣የመንግስት ይሁን የግል ድርጅቶች የሚያወጡት የስራ ዕድል የለም፣ ብዙ ሰው ይቀጥሩ የነበሩ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ጨምሮ ሌሎች ኢንዳስትሪዎች አሁንም ወደ ስራ አልተመለሱም። የተቀየረ ነገር የለም። ስለዚህ ወጣቱ አማራጭ አጥቶ ነው ያለው። በዚህም ስደት፣ ቁማር፣ ሱስ አማራጭ እያደረገ ነው" ይላል።

ከጦር ሜዳ የተመለሱ የትግራይ ወጣቶች ቃል የተገባላቸዉ ድጎማ አልሰጠንም ይላሉ
ትግራይ ዉስጥ ጦርነቱ ከቆመ በህዋላ ከህብረተሰቡ የተቀየጡ የቀድሞ ተዋጊዎች ሥራም፣ በቂ ድጎማም አላገኙምምስል Million Haileselasie/DW

ሌሎች አስተያየት የሰጡን ወጣቶችም በርካቶች ተስፋ በመቁረጥ ሁኔታ ላይ መሆናቸው ይናገራሉ። በጦርነቱ ወቅት ውግያ ላይ የነበሩ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም እንዲሁ፥ ይደረግላቹሃል የተባለ ድጋፍ አጥተው፣ አሁን ላይ በስራ ዕድል ማጣት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች እየተሰቃዩ ነው።

የቀድሞ ተዋጊው ጎይትኦም ፀጋይ ፥ ከመንግስት ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ይላል። ጎይትኦም "ትንሽም ቢሆን የሚቋቋምበት ነገር ካገኘ ይህ ሁሉ ወጣት ሰርቶ መኖር የማችል፣ የሚቀነር ነው። ይህ ካልሆነ ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ብቻ ሳይሆን ስነልቦናውም እየተጎዳ ነው ያለው" ባይ ነው።

ፌድራል መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ

ይህ ስራ አጥነት የፈጠረው የሚባል ወንጀል መበራከት የትግራይ ከተሞች ፈተና ሆኖ ይገኛል። ይህ ችግር ለመፍታት ጥረት ላይ መሆኑ የሚገልፀው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የመነሻ ካፒታል ችግር ፈታኝ ሆኖበት እንዳለ ያነሳል። የትግራይ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሐላፊ አቶ ሓይሽ ስባጋድስ እንደሚሉት በትግራይ ያለው የከፋ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ተገንዝበው መፍትሔ እንዲያበጁ ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ። 

በትግራይ ያለው ሁኔታ በመሸሽ በርካታ ወጣቶች ክልሉን ለቀው ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጨምሮ በሕገወጥ መንገድ ወደ ዓረብ ሀገራት እንዲሁም ሊቢያ በብዛት እየጎረፉ እንዳለ የክልሉ አስተዳደር ይገልፃል።

ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር