1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑሮ ውድነትና የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ

እሑድ፣ ግንቦት 13 2015

ኢሰማኮ አስቸኳይ ያላቸውን የበኩሉን መፍትሄዎችም ከ3 ሳምንት በፊት በተከበረው በዓለም የሠራተኞች ቀን በአደባባይ ሰልፍ ለማቅረብ ቢያቅድም ሰልፉ ባለመፈቀዱ ሳይሳካላት ቀርቷል። ኮንፈደሬሽኑ ጥረቱን በመቀጠል ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ለሌሎችም ባለስልጣናት ሊተገበሩ ይገባቸዋል ያላቸውን መፍትሄዎች ያካተተ ደብዳቤ መላኩን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4RcDg
  Ethiopia - Market in Amhara Region - Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በኢትዮጵያ ከቀን ቀን እየተባባሰ የሄደው የኑሮ ውድነት የምግብ፣የፍጆታ፣የቁሳቁሶች፣የትራንስፖርትና የአገልግሎት ዋጋ ግሽበት አብዛኛውን ዜጋ አቅም አሳጥቷል።በተለይ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የኑሮ ውድነትን መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ከደረሱ ሰንብቷል።  የቤት ኪራይ ዋጋ እና የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ በየጊዜው መናር ኑሮን እጅግ አክብዶታል። መንግሥት  ለዓመታት የዘለቀውን የዋጋ ንረት ለማቃለል ይረዳሉ ያላቸውን የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ቢያሳውቅም የኑሮ ውድነቱ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ አልሄደም ።

 ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥያቄ እየቀረበለት ነው። የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ማድረጉን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈደሬሽን በምህጻሩ (ኢሰማኮ) በቅርቡ መንግስት ችግሩን መቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስቧል። የሠራተኛው ደሞዝ የአሁኑን የገበያ ዋጋ ሊቋቋም በማይችልበት ደረጃ ላይ ነው የሚለው አንድ ሚሊዮን አባላት ያሉት ኢሰማኮ አስቸኳይ ያላቸውን የበኩሉን መፍትሄዎችም ከሦስት ሳምንት በፊት በተከበረው በዓለም የሠራተኞች ቀን በአደባባይ ሰልፍ ለማቅረብ ቢያቅድም ሰልፉ ባለመፈቀዱ ሳይሳካላት ቀርቷል። ሆኖም ኮንፈደሬሽኑ ጥረቱን በመቀጠል ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገንዘብ ሚኒስትርን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ላላቸው ባለስልጣናት የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽ በአስቸኳይ ሊተገበሩ ይገባቸዋል ያላቸውን መፍትሄዎች ያካተተ ደብዳቤ መላኩን አስታውቋል። 

  Ethiopia - Market in Amhara Region - Bahir Dar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የኑሮ ውድነትና የህዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ የዛሬው እንወያይ ርዕስ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወያዩ አራት እንግዶች አሉን።እነርሱም አቶ አያሌው አህመድ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፈደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ዶክተር አረጋ ሹመት በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ተመራማሪና በኑሮ ውድነት ላይ ጥናት ያካሄዱ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ፣ ዶክተር አዳነ ካሴ በፖሊሲ ጥናት ተቋም የፖሊሲ አጥኚና በተለይ በኢትዮጵያ ሰራተኛ ማኅበራት ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሞያ እንዲሁም ወይዘሮ ጫልቱ ተገኝ የኢትዮጵያ የኅብረት ስራ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ናቸው።

ኂሩት መለሰ