1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የንፋሱ ፍልሚያ» የመጀመርያዉ በዓለም አቀፍ ለዉድድር የቀረበ ፊልም

ሐሙስ፣ ሰኔ 22 2015

“በእውነተኛ ሁኔታ ላይ የተመሰረተዉ ፊልም ነዉ።በአዲስ አበባ የጎዳና ሕይወትን አሰቃቂና አሳዛኝ ገጽታን የሚያንፀባርቅ፤ ብሎም በከባድና በአስጨናቂ ጊዜዎች ሁሉ ጸንቶ መቆም የቻለ ጓደኝነትና በጥንካሪ ህልም እና ምኞት ስኬትን ማግኘታቸዉን ያንፀባርቃል ነዉ። ፊልሙ በጣም አዎንታዊ መልክት ያዘለና ለኢትዮጵያ አዎንታዊ አቀራረብ ያለው ፊልም ነው።»

https://p.dw.com/p/4TD3X
Film | Running Against the Wind
የነፋሱ ፍልሚያምስል R&B FILM

ፊልሙ የሁለት ጓደኛሞች የህይወት ዉጣ ዉረድ ብሎም ትግልና የዓላማ ጽናትን ይተርካል

ጀርመናዊ የፊልም ፕሮዲዉሰር ያን ፊሊፕ ቫይል ይባላል። በአምስት ዓመት ዉስጥ አማርኛን የተማረዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሳለ ነዉ ። አሁን ደሞ በስራ ምክንያት ሎሳንጀለስ በመሆኔና በእንጊሊዝኛ ብቻ በመነጋገሪ አማርኛዉ ትንሽ እየጠፋብኝ ነዉ፤ ቢሆንም ወደ ምወዳት ኢትዮጵያ መመለሴ አይቀርም ይላል። ጀርመናዊዉ ያን ፊሊፕ ኢትዮጵያን የተዋወቀዉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ ነበር። ከአምስት እና ከስድስት ዓመት ወዲህ ደግሞ ለፊልም ስራ ወደ ኢትዮጵያ አቅንቶ ቀድሞ ሲያልመዉ የነበረዉን ፊልም ሰርቶ ፊልሙን በቅርቡ በኢስካር አካዳሚ ለዉድድር እንዲበቃ አድርጓል። በኢትዮጵያ በነበረበት ወቅትም አማርኛ  ቋንቋን በመንገድ ላይ አልያም ከኢትዮጵያዊ ጓደኞቹ ጋር በመነጋገር ለምዶ ጥሩ መግባባት ይችላል። ለፊልም ስራዉ በአሁኑ ሰአት ሎሳንጀለስ የሚገኘዉን ፊሊፕን በስልክ ሃሎ አልነዉ።

«ያን ፊሊፕ ቫይል እባላለሁ. በኦስካር ፊል አካዳሚ የቀረበዉ የመጀመርያዉ የኢትዮጵያ አጭር ፊልም ደራሲ እና አዘጋጅ ነኝ። የፊልሙ ስም Running Against the Wind በአማርኛ ስሙ «የንፋሱ ፍልሚያ» ይባላል። የዚህ ፊልም ሥራ ተጠናቆ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለእይታ የበቃዉ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2019 ዓም መስከረም ወር ላይ ነበር። ከዝያም ነዉ ፊልሙ በብዙ አገር ታይቶ ለዉድድር በኦስካር አካዳሚ የቀረበዉ። አሁን በመጨረሻ ይህ ፊልም ከሁለት ሳምንት በኋላ በጀርመን  በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የፊልም አዳራሾች እና ትያትር ቤቶች መታየት ይጀምራል።»

Film | Running Against the Wind
የነፋሱ ፍልሚያምስል R&B FILM

በኢንግሊዘኛው «Running Against the wind» ወይም “የነፋሱ ፍልሚያ” የተሰኘዉ እና ፊሊፕ በኢትዮጵያ የሰራዉ ፊልም ለኦስካር (አካዳሚ አዋርድ) ሽልማት ኢትዮጵያን ወክሎ፤ ምርጥ ዓለም አቀፍ ፊልም (Best International feature film) በሚለው ዘርፍ ለውድድር ቀርቦ ነበር።  “በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተዉ ይህ ፊልም፤ በአዲስ አበባ የጎዳና ሕይወትን አሰቃቂና አሳዛኝ ገጽታን የሚያንፀባርቅ፤ ብሎም በከባድ እና በአስጨናቂ ጊዜዎች ሁሉ፤ት ጸንቶ መቆም የቻለ ጓደኝነት እና በጥንካሪ ህልም እና ምኞት ስኬትን ማግኘታቸዉን የሚያንፀባርቅ ፊልም መሆኑን ፊልሙ የታዩባቸዉ ሃገራት ስለ ፊልሙ የተለያዩ ዘገባዎች አስነብበዋል። ይሁንና ይህ ፊልም እንደወጣ በኢትዮጵያ ለእይታ ሲበቃ የኮሮና የዝዉዉር እገዳ መጣሉ ነገሩን አክብዶት ነበር።

«አዎን ፣ ይህ ትክክል ነው ። ፊልሙን በመስከረም ወር 2019 ዓ.ም ለእይታ እንደወጣ ከጥቂት ግዚያት በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 2020 ከመጋቢት ወር ጀምሮ የኮሮና የዝዉዉር እገዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ጀመረ። በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ሲኒማዎች በራቸዉ በመቆለፉ ለዚህ ፊልምም የመጀመርያ እይታ ጅማሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር የፈጠረበት።»

ይሁና ይላል የፊልም ባለሞያዉ ጀርመናዊ ያን ፊሊፕ፤ የኮሮና እገዳ ከተነሳ በኋላ የንፋሱ ፍልምያ የተባለዉ ፊልም  በተለያዩ የዓለም ሃገራት መታየቱን ቀጥሏል፤ በርካታ አወንታዊ አስተያየቶችም እየተሰጡን ነዉ።  

«የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉ ይህ ፊልሜን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የዓለም ሃገራት ታይቷል፤ ለዚህም ብዙ ስጋት የለኝም። የኮሮና እገዳ ከተነሳ ጊዜ አንስቶ፣ ፊልሙ በታየባቸዉ ሃገራት ሁሉ በጣም አስደናቂ የሆነ አስተያየት እየተቀበልን ነው። ከኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያ፤ ብሎም በድያስፖራ ካሉ ኢትዮጵያዉያንም ሁሉ እጅግ ጥሩ አስተያየቶች እየደረሱን ነዉ።»

የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ያን ፊሊፕ በፊልም ሥራ የቆየ ልምድ አለዉ። ለኢትዮጵያም ልዩ ፍቅር አለው። ፊልሙን ለመሥራት በ 2005 ዓመት ገንዳ አብዲ የምትባል ከሐረር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ አካባቢ ላይ ያያቸዉን የዘጠኝ እና የአስር ዓመት ህጻናት በማሰብ  ነው። ገንዳ አብዲ በሰዎች ለሰዎች በጎ አድራጎት ድርጅት ትምህርት ቤትና መሠረተ ልማት የተሟላላት፤ ግን ብዙ ሰው የማያውቃት ትንሽ መንደር ናት። ታድያ ያን ህልሙን ዛሬ አሳክቶ እሱ ራሱ ፊልሙን በዓለም አአፍ የዉድድር መድረክ አሰልፎታል።

«በጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር  በ 2016, 2017 የፊልም ስራዉን ለመጀመር ሁሉን ነገር በማሰባሰብ ቀረጻ ጀመርን።  መስራት የፈለኩት በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ፊልምን ነበር። «Running Against the Wind» የተባለዉ ፊልም  መስራት ማሰብ የጀመርኩት፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ.ም ነዉ። ይህ እንደሚሳካልኝ አዉቅ ነበር ፤ ዛሬ ይህ ህልሜ በመሳካቱ ደስተኛ ነኝ ። ይህ ፊልም አንድ ቀን በኢትዮጵያ ቴቭዥን ቢሰራጭ ህዝብ ቢያየዉ ከምንም በላይ በጣም በጣም ደስተኛ እሆን ነበር።»

ያን ፊሊፕን ስለ ፊልሙ በጥቂቱንም ቢሆን አጫዉተን አልነዉ።

«የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉ ፊልም በሁለት ኢትዮጵያዉያን ቅርብ ጓደኛሞች የህይወት ታሪክ ላይ ያጠነጥናል።  የጀብደኝነት፤ የአላማ ጽኑነት፤ ጥንካሪ የተሞላበት 150 ደቂቃ ፊልም ነው። ለመላው ቤተሰብ በምሳሌነት የሚቀርብ ታሪክ አዘል አጭር ፊልም ነው። ታሪኩ የሚጀምረዉ በጣም ትንሽ ከሆነች በስተምሥራቅ ሐረር ባቤሌ  አካባቢ ከምትገኝ የገጠር መንደር ነዉ። ከዚህ አካባቢ የመጡ ሁለት የቅርብ ጓደኛሞች የሚያደርጉትን የህይወት ዉጣ ዉረድ እና ትግልን፤  ጽናትን ያሳያል። ሁለቱ ጓደኛሞች በዘጠኝ ዓመት ዕድሜያቸው በሕይወታቸው ውስጥ ምን መሆን እንደሚፈልጉ ሕልም ነበራቸዉ። አንዱ ሰለሞን ይባላል። ፎቶ አንሺ ለመሆን የሚያደርገዉ ጥረት አለ።  የሰለሞን ቅርብ ጓደኛ አብዲ ደግሞ ታላቅ አርአያ አድርጎ እንደያዘዉ እንደ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ሯጭ ለመሆን ህልሙን ለማሳካት የሚያደርገዉን ትግል የሚተርክ ፊልም ነው።» 

በፊልሙ የሚተዉኑት አክተሮች ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ። በፊልም ሥራ ሂደቱ፤ የተዋናይ መረጣ ከ 2014 የጀመረ መሆኑን ያን  ፊሊፕ ተናግሯል። በመጀመሪያ 4000 የሚደርሱ ሰዎች፤ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ጨምሮ፤ አትሌቶችም በተዋናይ መረጣ ላይ ተሳትፈዋል። በመጨረሻ በዋናነት የሚተውኑ ሦስት ተዋንያን ከዛ ውስጥ ሊገኙ መቻላቸዉን ያን ፊሊፕ ተርኮልናል። በፊልሙ ላይ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፤ በሙዚቃ እጀባ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)ይገኙባቸዋል። ያን ፊሊፕ እንድያም ሆኖ ይላል፤ ፊልሙን ለዓለም አቀፍ መድረክ ለማብቃት የባህል ሚኒስቴር አንዳንድ ፎርሙላዎችን ማሟላት ያስፈልግ ስለነበር ከፍተኛ ትብብር ማግኘቱን አመስግኗል።

Jan Philipp Weyl
ጀርመናዊ የፊልም ፕሮዲዉሰር ያን ፊሊፕ ቫይል ምስል Amanuel Tadesse

«ይህ የኢትዮጵያ ፊልም በዓለም አቀፍ ፊልም የፊልም መድረክ ኦስካር አካዳሚ ተወዳዳሪ ሆኖ ሲቀርብ  ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። መላው የፊልሙ ሰራተኞች ሁሉ በዚህ  በጣም ኮርተናል። እንዲህ አይነት ፊልም በይፋ በዓለም በኦስካር ለዉድድር ሊቀርብ የሚችለዉ በመንግሥት ተቋም በኩል ተመርጦ በአገር ዉስጥ ፈቃድ ሲያገኝ ብቻ ነዉ። «የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉ ፊልም የባህል ሚኒስትር ፈቃድ ተሰጥቶት ነዉ፤ በኦስካር የዉድድር መድረክ ለመቅረብ የበቃዉ።  የቀድሞዋ የባህል ሚኒስቴር ከአራት ወራት በላይ ከአካዳሚው ጋር በመገናኘት አስፈላጊውን ፎርም እና የቢሮክራሲ ጥያቄዎችን አሟልተዋል። ዛሬ የኦስካር አካዳሚ ኢትዮጵያ የፊልም ሰራተኛ አገር መሆኗን መዝግቧል፤ አዉቋል።»    

ያን ፊሊፕ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለተኛ ፊልም ለመስራት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀና ተናግሯል። ለወጣቶች የፊልም ስልጠና ሞያንም ይሰጣል። የኢትዮጵያ የፊልም ስራ እና ቀረፃ መሻሻሉን ይናገራል።

«አዎን ፣ ኢትዮጵያ ፊልም ሰራተኛ ሃገር ናት ማለት እችላለሁ። ከ16 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን አዉቃታለሁ።  ብዙ ተሞክሮም አለኝ። በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ሦስት ያህል ፊልም ይሰራ ነበር ማለት እችላለሁ፤ ምንም እንኳ በዓመት እስከ 50 ፊልሞች ለእይታ ቢበቁም። የፍቅር ፤ ኮመዲ፤ ድራማ፤  ሲኒማዎች ብዙ ይሰሩ ነበር። አሁን ግን በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በጣም ብዙ አዳዲስና ተሰጥኦ ያላቸው የፊልም አዘጋጆች፣ ዳይሬክተሮች፣ ወደ መድረኩ መምጣታቸዉን አይቻለሁ። እነዚህ ብዙ እምቅ እዉቀት ያላቸዉ ባለሞያዎች በእውነትም የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ መሰረት እየገነቡ ያሉ በመሆናቸው እጅግ በጣም አስገራሚ ነው።»

ያን ፊሊፕ እንደሚለዉ የፊልም ስራ ብቻዉን ለፊልም ኢንዱስትሪዉ የሚያመጣዉ ፋይዳ የለም ይላል። ዋናዉ ነገር ፊልሙን ማሰራጨቱ እና ብዙ ተመልካች  እንዲኖረዉ ማድረጉ ዋና ስራ ነዉ። ባለፈዉ ገና አካባቢ ኢትዮጵያ ሳለሁ ለወጣት ፊልም ሰሪዎች ስልጠና ሰጥቻለሁ፤ ብዙ እምቅ ጉልበትም አይቻለሁ ብሏል።

«በቅርቡ አዲስ አበባ ዉስጥ በ 19 እና  32 እድሜ ክልል የሚገኙ 62 ወጣት ፊልም አዘጋጆችን የፊልም ስራ ስልጠናን ሰጥቻለሁ። አብዛኞቹ «የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉን ፊልማችንን ያዩ እና ስራችንን የሚያዉቁ ናቸዉ። ስልጠና በምሰጥበት ዉቅት ብዙ እምቅ የፊልም ስራ እዉቀት እና የተለያዩ ሃሳቦች እንዳላቸዉ ተገንዝብያለሁ። በቅርቡ የንግድ ድርጅቶች፣ አምራቾች፣ ነጋዴዎች የሚመረተዉን ፊልም የማሰራጨት አቅም ይኖራቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።  ምክንያቱም አዲስ ፊልምን ማሰራጨት፤ በእርግጥም ለፊልም ኢንዱስትሪዉ የጀርባ አጥንት ነዉ።  ፊልም መስራት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገዉ፤ ማሰራጨት እና የማስታወቅያ አቅም እንዲኖር ያስፈልጋል። በኢትዮጵጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ይህ አይነት እዉቀት እና ንቃት  ይመጣል ብዬ ነው እገምታለሁ። »

ፊሊፕ ኢትዮጵያን እንዴት ተዋወቃት ይሆን? ፊሊፕ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በሰዎች ለሰዎች ድርጅት መሥራች በጎ አድራጊው፤ በዶክተር ካርል ሃይንስ በም ግብዣ ነበር። ያን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበር።  ያን ፊሊፕ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ ወደ አገሩ ወደ ጀርመን ሲመለስ ከእድሜ እኩዮቹ ጋር በሚማርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብስኩት እና ኬክ በመሸጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመረ።  በመጨረሻ ያን ከጓደኞቹ ጋር  23 ሺህ ዩሮ አሰባስበዉ፤ በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኩል በኩል  ሁለት ትምህርት ቤቶችን አሰርተዋል። ያን ፊሊፕ  ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሙኒክ የፊልም ስራ ትምህርቱን አጠናቋል። ኢትዮጵያን  ከተዋወቀበት ጊዜ ከ 18 ዓመት እድሜዉ ጀምሮ  በየጊዜዉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አላቆመም። ብዙ ጓደኞችን አፍርቷል፤ በአማርኛ ቋንቋም አይታማም።  የሰዎች ለሰዎች በጎ አድራጊ ድርጅት መስራች ዶክተር ካርል ሃይንስ በም የነገሩኝ አንድ ነገር ፍጹም ከአይምሮዬ አይጠፋም፤ ይላል ያን ፊሊፕ፤

«አንድ የተናገሩትን ነገር አልረሳውም፤ ይህንም ማካፈል እወዳለሁ። ምን አሉኝ፤ ወደ ኢትዮጵያ ከሄድክ በኋላ ተመልሰህ ልምዶችህን ከመልአክ አንደበት ጋር ትናገራለህ። አሉኝ። በዚያን ጊዜ ደግሞ 17 ዓመቴ ነበር።  ምን ማለታቸዉ ነዉ ብዬ አሰብኩ። ለኔ ጠንካራ እና ለመረዳት የሚያስቸግር ንግግር ነበር። አሁን ይህ ምን ማለት እንደሆን ይገባኛል።»

ያን ፊሊፕ ሰሞኑን በጀርመን በተለያዩ ከተሞች የንፋሱ ፍልምያ የተሰኘዉ ፊልም በተለያዩ ፊልም እና ትያትር ቤቶች መታየት ይጀምራል፤ በጀርመን የምትገኙ ኢትዮጵያዉያን እንድትመለከቱ እጋብዛለሁ ብሏል።

Film | Running Against the Wind
የነፋሱ ፍልሚያምስል R&B FILM

«የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉን ፊልማችን ያልተመከቱ ፊልሙን ቢያዩ ደስ ይለኛል። ፊልሙ በጀርመን ፊልም ቤቶች እና ትያትር ቤቶች በሚቀጥሉት ሳምንታት ለተመልካች መቅረቡን ስገልጽ በደስታ ነዉ። እናም በተቻለ መጠን በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ፊልሙን እንዲመለከቱ እጋብዛለሁ።»

ኢትዮጵያን ወዳጁ ጀርመናዊዉ የፊልም ስራ ባለሞያ ያን ፊሊፕ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ህዝቡ ሰላም እንዲያገኝ እና ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ከፍታዋ እንድትመለስ ምኞቱን ገልጿል።

«በኢትዮጵያ ጦርነቱ በመቆሙ በጣም ደስተኛ ነኝ። በቀጣይ የኢትዮጵያ የሆኑ መልካም ነገሮች በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያን እንደሚመለሱም እርግጠኛ ነኝ። «የንፋሱ ፍልሚያ»  የተሰኘዉ ፊልም በጣም አዎንታዊ መልክት ያዘለ  እና ለኢትዮጵያ አዎንታዊ አቀራረብ ያለው ፊልም ነው ብዬም አምናለሁ።»

አማርኛ ቋንቋ ትንሽ ትንሽ ኦሮምኛንም የሚሞክረዉ ያን ፊሊፕ በመጨረሻ የዶቼ ቬለን አድማጮች በነዚህ ቋንቋዎች ተሰናብቷል።

“የነፋሱ ፍልሚያ” በጀርመን ከተሞች በየትኞቹ ፊልም ቤቶች እና ትያትር ቤቶች እንደሚቀርብ ያለዉን ፕሮግራም እና አድራሻ በድረ-ገጻችን ላይ እንለጥፋለን። አድማጮች በዚሁ የፊልም ባለሞያዉን ጀርመናዊ ያን ፊሊፕን ለሰጠን ቃለ-ምልልስ እያመሰገንኩ የዛሬዉን ዝግጅቴን አጠናቅቃለሁ።

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ