የአማራ ክልል መንግሥት «ህወሓት ጦርነት ከፍቶብኛል» አለ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016
የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት «ህወሓትና ግብረ አበሮቹ» ያላቸው አካላት ሁለቱ ወገኖች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱባቸውና ሰሞኑን በኃይል ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳሰበ። የአማራ ክልላዊ መንግሥት በመግለጫው የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበርም ጠይቋል። በሌላ በኩል ሰሞኑን በራያ አላማጣ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ቆቦና ወልዲያ ከተሞች መድረሳቸውን የሰሜን ወሎ ዞን አስታውቋል።
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ የአማራ ክልል ተማሪዎችን የመማሪያ መጽሐፍት እንደ ሰበብ ተጠቅሞ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ ም ይፋ ጦርነት አውጇል ብሏል። መግለጫው አክሎም ችግሮቹን በፌደራል መንግሥት አማካኝነት በውይይት ለመፍታት ጥረት ቢደረግም እንዳልተሳካ አመልክቶ «ህወሓት የማንነት ጥያቄ ባለባቸው በራያ አላማጣ፣ በራያ ባላ፣ በኮረምና ዛታ አካባቢዎች ጥቃት ከፍቷል» ነው ያለው። ወልቃይትን፣ ጠገዴንና ጠለምትን ጨምሮ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት አስተዳደራዊ መዋቅሮቹን ህወሃት በኃይል መውሰዱን መግለጫው አስታውሷል።
በመሆኑም ህወሓትና ግብረ አበሮቹ የተባሉ አካላት ደም አፋሳሽ ጦርነት ከማካሄድ እንዲቆጠቡና ችግሮቹ በተቀመጠው የሰላም ስምምነት መሠረት እንዲፈታ ከያዟቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ እንዲወጡ የአማራ ክልል መንግሥትጠይቋል።
ጦርነት እንደተከፈተበት ያመለከተው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት «የተከፈተብንን» ያለውን ጦርነት ለመመከት በሚደረገው ጥረት የክልሉ ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ አሳስቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት «ቡድኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወረራቸው አካባቢዎች ለቅቆ እንዲያስወጣና ህዝቡን ከጥፋት እንዲታደግ» ሲል መግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው፤ «ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓት የፈፀመውን ጥቃት እንዲያወግዝም አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባንችልም የህወሓት ኃይሎች ትናንት ከሰዓት በኋላ የኮረም ከተማን መቆጣጠራቸውን አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል። እንደ አስተያየት ሰጪው ተዋጊዎቹ በጭፈራና በፉከራ ትናንት ማምሻውን ከተማዋን ተቆጣጥረዋል።
ሰሞኑን ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ከአላማጣና ከኮረም ከተሞች ወደ ሌሎች የአማራ ክልልከተሞች የሚደረጉ መፈናቀሎች ቀጥለዋል። አንድ ከአላማጣ ተፈናቅለው ቆቦ የሚገኙ ግለሰብ ምንም ነገር በሌለበት አካባቢ እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን ጠቅሰው የቀረበ እርዳታም የለም ነው ያሉት።
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ተፈናቃዮች ቆቦና ወልዲያ ከተሞች ደርሰዋል ብለዋል። የዕለት እርዳታ ማቅረብ አለመቻሉን አቶ ዓለሙ ገልጠው የሚመለከተው ሁሉ እጁን ለእርዳታ እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።
የራያ አላማጣ አካባቢ አንድ የሥራ ኃላፊ አብዛኛው የወረዳው አካባቢዎች በትግራይ ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል። የትግራይ ክልለ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንትና በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ «ችግሩን እየፈጠሩት ያሉት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበር ሚፈልጉ አካላት ናቸው» ማለታቸው ይታወሳል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጀኔራል ታደሰ ወረደ ትናንት መቀሌ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ደግሞ «በኃይል የተያዙ የትግራይ አካባቢዎች» ያሏቸውን ቦታዎች በኃይል ለማስመለስ እንደማይፈልጉ ገልጠው፣ ችግሮቹን ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገርና በመግባባት የሚፈቱ እንደሚሆን ገልፀው ነበር፡፡
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ