የአማራ ክልል ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እና ምርጫው
ሰኞ፣ ሰኔ 21 2013
በአማራ ክልል የተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ በአብዛኛው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል። በጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱ መሰረት፣ በባሕር ዳር ከተማ የምርጫ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለክልልና ለፌደራል ምክርቤቶች የተካሄደውን ምርጫ ማሸነፉን የከተማዋ ምርጫ ክልል አስተባባሪ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።አለምነው መኮንን ከባህርዳር ዝርዝሩን አዘጋጅቷል።ከቀደሙት ምርጫዎች በማወዳደር የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ ነው ሲሉ ብዙዎቹ መስክረዋል፣ ወከባ፣ ማጭበርበርና ጫና ብዙም እንዳልነበረውም የተናገሩት።በመሆኑም በቅድመ ምርጫና በምርጫው ቀን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መራጩ ህዝብና ባለድርሻ አካላት በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ በመቻላቸው 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አድኃን) ሊቀመንበርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ቅድመ ምርጫውና ምርጫው በአብዛኛው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ገምግመውታል።ምርጫው መቶ በመቶ እንከን የለበትም ባይባልም አንዳንድ የታዩ ችግሮችና ድህረ ምርጫውን ተከትሎ የሚመጣ ችግር ካለም በውይይትና በመግባባት እንዲፈቱ የጋራ ምክር ቤቱ መስማማቱንም አቶ ተስፋሁን አመልክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ችግሮች ከተፈጠሩም ችግሮችን ተመልክቶና መርምሮ መፍትሔ የሚሰጥ 5 አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩንም ሰብሳቢው ገልፀዋል።አቶ ተስፋሁን አክለውም አጠቃላይ የምርጫው ውጤቱ ምንም ይሁን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተገለፀ በኋላ ቅሬታ የሚያቀርብ አካል ካለም ሕጋዊ መስመሩን ብቻ ተከትሎ እንዲፈታ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ 144 የምርጫ ጣቢያዎች ባሉት የባሕር ዳር ምርጫ ክልል በአጠቃላይ ድምር በጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱ መሰረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለክልልና ለተወካዮች ምክር ቤት ማሸነፉን የባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል አስተባባሪ ማህደር አዳሙ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።አጠቃለይ በአማራ ክልል የተካሄደውን ምርጫ ውጤት በተመለከተ የክልሉን ምርጫ ቦርድ ኃላፊ አቶ መኳንንት መከተን ጠይቀናቸው ውጤቱ ተጠቃልሎ የገባ ባለመሆኑ የተጠቃለለ ውጤት ለመስጠት እንደማይችሉ ገልፀውልናል።በአማራ ክልል በፀጥታና በሌሎችም ምክንያቶች ምርጫ ያልተካሄደባቸውን ጨምሮ በዘንድሮው ምርጫ 138 የምርጫ ክልሎች፣ 12ሺ 199 ምርጫ ጣቢያዎች ሲገኙ፣ 18 የፖለቲካ ርቲዎች በምርጫው ተወዳድረዋል፣ 7 ሚሊዮን 400 ሺህ ህዝብ ደግሞ የመራጭነት ካርድ ወስደዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ