1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአረንጓዴ ጀግናዋ ሱ ኤድዋርድስ

ማክሰኞ፣ የካቲት 13 2010

የተፈጥሮ ይዞታቸው ተበላሽቶ የነበረ የትግራይ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በተከናወኑ ተግባራት፤ የአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ ባደረጉት አስተዋፅኦ ስማቸው ይነሳል። ለአርሶ አደሮች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ባሳዩት ቀረቤታ ብዙዎች እናታችን ይሏቸዋል።

https://p.dw.com/p/2t0i9
Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
ምስል ISD

ለአካባቢ ተፈጥሮ ሲቆረቆሩ ለሀገራዊ ዕዉቀት ትኩረት ሲሰጡ ኖረዋል፤

 

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
ምስል ISD

ሱዛን በርኔል ኤድዋርድስ እንግሊዛዊቷ የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪ እና የሀገር በቀል እዉቀቶች አድናቂ የነበሩት ሱ ኤድዋርድስ ሙሉ መጠሪያ ነው። በቅርበት የሚያዉቋቸው እንደሚናገሩት ግን እሳቸው ትዳር መስርተው ወልደው ከብደው ከ40 ዓመታት በላይ በኖሩባት ኢትዮጵያ፤ ስማቸው ኢትዮጵያዊ ይዘት እንዲኖረው ስለሚሹ ሶስና ኤድዋርድስ መባልን ይመርጡ ነበር። እንግሊዛዊቷ ወይዘሮ ወደኢትዮጵያ በሄዱበት በ19 60ዎቹ መባቻ ገደማ አንስተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ መምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በዚህ አጋጣሚም  እንደእሳቸው ሁሉ ለአካባቢ ተፈጥሮ ልዩ ትኩረት የሚሰጡ እና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት ባለቤታቸው ጋር መተዋወቃቸውን ለመረዳት ችለናል። በባዮሎጂ የትምህርት ክፍል በማስተማር ላይ ሳሉ በቀጣይ የሠሯቸውን የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ግዛው ገብረ ማርያም መለስ ብለው እንዲህ ይዘረዝራሉ፤

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
ምስል ISD

«በባዮሎጂ ዲፓርትመን እያስተማሩ እያሉ በ1976ዓ,ም ወደ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ከአዲሱ የትዳር አጋራቸው ጋር ዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ጋር በመሄድ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ላይ የመጀመሪያው ሥራቸው የነበረው የማሪን ባዮሎጂ ዲፓርትመንትን ማቋቋም ነበር። ይሄም ተሳክቶላቸዋል። ከዚያ በመቀጠል በኢትዮጵያ ትልቁ ፈር ቀዳጅ የሆነው ሥራ የሠሩት የኢትዮጵያን የዕፅዋት ብዝሃ ሕይወት በመመዝገብ፣ በማጥናት እና አከታትሎም የዚያን የጥናት ዉጤት ዋና አርታኢ በመሆን ሠርተዋል።»

በ1983ዓ,ም ከተካሄደው የመንግሥት ለውጥ በኋላ ከባለቤታቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው የተመለሱት ወ/ሮ ሱዛን ኤድዋርድስ፤ በ1989ዓ,ም ከመኖሪያ ቤታቸው አንዷን ክፍል ለቢሮነት በመጠቀም ዘላቂ ልማት መካነ ጥናትን ከባለቤታቸው  ከዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ጋር አቋቋሙ። እንደተረዳነው ይህ ድርጅት አሁን 21ኛ ዓመቱን አገባዷል።  ዘላቂ ልማት መካነ ጥናትን ያቋቋሙበትን መነሻ የድርጅቱ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ግዛው ሲገልፁ፤

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
በጤፍ እርሻ ዉስጥምስል ISD

«ዘላቂ ልማት መካነ ጥናትን ለማቋቋም ያነሳሳቸው አንዱም በተፈጥሮ የተቸራቸው የተፈጥሮ አፍቃሪ እና ለማኅበረሰብ ለውጥ እጅግ በጣም የተጉ ለአካባቢ ጥበቃ በጣም የተጉ፤ ሰው በመሆናቸው፤ በተለይ ኢትዮጵያ ከርሃብ እና ከኋላ ቀርነት እንድትላቀቅ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የተንተራሰ ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ትልቁ መሠራት ያለበት ብለው እሳቸው የሚያምኑት በአነስተኛ ደረጃ የሚያመርቱትን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች አቅም ማጎልበት ነው። ከአርሶ አደሮች ጋራ በቅርበት መሥራትን መረጡ የአርሶ አደሩ እውቀት ከዘመናዊ እውቀት ጋራ ተቀናጅቶ ሀገራችን በዘላቂነት ከምግብ ልመና ራሷን ትችላለች የሚለው እምነት እንዲሰርጽ ነው እንግዲህ ሲታገሉ የነበረው ማለት ነው።»

ሃሳቡ መልካም ቢሆንም ሥራው ግን ቀላል እንዳልነበረ አቶ ግዛው ያስታውሳሉ።

«የተጀመረው ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የትግራይ ፕሮጀክት በሚል ነበር። ምክንያቱም የ17ቱን ዓመት የተካሄደውን በጣም ከፍተኛ በአካባቢ እና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ውድመትን ያስከተለውን ጦርነት ተከትሎ፤ እንደሚታወቀው አካባቢው የተራቆተ፤ አፈሩ ለምነቱን ያጣ፣ ኅብረተሰቡ ምግብ ፍለጋ ከተራቆተው አካባቢ ለቆ ለመሄድ የሚገደድበት ወቅት ስለነበር የአካባቢዉም ማኅበረሰብን በተመረጡ አካባቢዎች በማወያየት አካባቢዉ በመጀመሪያ መልሶ እንዲያገግም የተሸረሸረው አፈር እንዲያገግም እና አርሶ አደሮች ማምረት እንዲችሉ የአርሶ አደሮቹም እውቀት እንዲካከት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ነው ሀ ብለው የእርሻውን ሥራ ከአርሶ አደሮቹ ጋር መደገፉ ላይ ያነጣጠረ ሥራ መሥራት የጀመሩት ማለት ነው። »

ይህ የትግራይ ፕሮጀክት ስነምህዳርን የጠበቀ የአስተራረስ ስልትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ እና ይህም የአርሶ አደሩን ነባር እውቀት አካቶ አርሶ አደሩም አምኖበት ተቀብሎት ሥራ ላይ የዋለ እንደሆነም አቶ ግዛው ያስረዳሉ። ዓላማውም በዚሁ ተፈጥሯዊ ስልት ምርት እንዲጨምር እና የአካባቢ ጥበቃውንም ማበረታታት ነው። ይህ ስልት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን በአፍሪቃ ደረጃም እንዲስፋፋ መደረጉንም እንዲሁ።

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
እሳቸው በሚከተሉት የእርሻ ስልት የተመረተ የማሽላ ማሳን ሲመለከቱ፤ ምስል ISD

«ማኅበረሰቡ የራሱን የአካባቢ ሕግ አውጥቶ የወደመውን አካባቢ መልሶ እንዲያቋቁም መደገፍ አብሮ መሥራት የሚለውን ከክልሉ የግብርና እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ቢሮ ጋር በመሆን ነው የተጀመረው እና ቀስ እያለ ይኼ ፕሮግራም በዚህ ሃያ ዓመት ጉዞ ውስጥ ከፍተኛ እውቅናን በማግኘቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም ተመሳሳይ ድርጅቶች  የሚያከናዉኗቸው ይሄ የተፈጥሮ የእርሻ ዘዴን የማበረታታቱ ጉዳይ ተቀባይነት በማግኘቱ የኢትዮጵያዉን ምዕራፍ የሚመራው ዘላቂ ልማት በተለይም የወ/ሮ ሱ እና የዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ስለሆነ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጋራ ልምዱ ተቀናጅቶ በአፍሪቃ ደረጃ «ኤኮሎጂካል ኦርጋኒክ አግሪካልቸር አኒሺየቲቭ ፎር አፍሪካ» በአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቀርቦ እንደ አውሮጳዉያን አቆጣጠር በዲሴምበር 2011 ተቀባይነት እንዲኖረው ተደርጎ የጸደቀ ነው።»

ይህም የ20 ዓመታት የትግል ዉጤታቸው እንደሆነ ነው ለማስረዳት የሞከሩት። የክብር ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ትውልደ እንግሊዛዊቷ ወ/ሮ ሱዛን ኤድዋርድስ በኤኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እንዲመጣ ሳይታክቱ የሠሩ የአካባቢ ጥበቃ አቀንቃኝ እንደነበሩ በቅርበት የሚያዉቋቸው ይናገሩላቸዋል። በሥራ አጋጣሚ ከሚያዉቋቸው አንዱ በተለይ የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ አተኩሮ ይሠራ የነበረው ጋዜጠኛ አርጋዉ አሽኔ በግሉ ስለብዝሀ ሕይወት ምንነት በዝርዝር እንዲያዉቅ መንገድ ከከፈቱለት ምሁራን አንዷ ናቸው ይላቸዋል።

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
ሴት አርሶ አደሯን በማሳዋ ተገኝተው ሲያበረታቱምስል ISD

«ቢያንስ ለ10 እና 11 ዓመታት በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ውስጥ ያደርጉት የነበረውን አስተዋጽኦ በቅርብ መታዘብ ችያለሁ። እኔ ራሴም ከእሳቸው አንዳንድ ነገሮችን ለመማር ዕድል ያገኘሁበት ጊዜ ነበር። በተለይ ወደ አካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ዉስጥ በገባሁበት የመጀመሪያው ጊዜያት ላይ ይህንን የተለያይነት ወይም የባዮዳይቨርሲቲ ጉዳይ ፈፅሞ ብዙም የማላውቀው ርዕሰ ጉዳይ በነበረበት ጊዜ የመጀመሪያውን ስልጠና እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች አይፈቀድም ነበር በጊዜው ለክልል እና ለፌደራል መንግሥት የተወሰኑ የተመረጡ ሠራተኞች የሚሰጥ ስልጠና ነበር እና ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ደብዳቤ ጽፈውልኝ ሄጄ በዚህ ስልጠና እንድካፈል እና ነገሩ እንዲገባኝ በማድረግ በመጀመሪያ በዚህ ነው የምንተዋወቀው።»

እሳቸው በተገኙባቸው በሀገር ዉስጥም ሆነ ከሀገር ዉጭ በተለያዩ ስብሰባዎች የመሳተፍ አጋጣሚው እንደነበረው የሚናገረው ጋዜጠኛ አርጋው ወይዘሮዋ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል፤ በገጠርም ከአርሶ አደሮች ጋር ዝቅ ብለው እና ተቀራርበው መሥራት ይወዱ እንደነበረም አስታውሷል። በእነዚህ ሥራዎቻቸውም ጥሩ ዉጤት ተገኝቷል ባይ ነው።

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
በአንድ ትምህርት ቤት ተገኝተዉ ዛፍ ሲተክሉምስል ISD

«ለምሳሌ የጤፍ ተለያይነትን ወይም የጤፍ ባዮዳይቨርሲቲ አይነቶችን  ለመለየት እና ለማስተዋወቅ በተደረገው ጥረት ውስጥ በጣም ቁልፍ ሚና የነበራቸው ሴት ናቸው። በደብረዘይት ያለ የጤፍ ምርምር ተቋም ውስጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይካፈሉ የነበሩ ሰው ናቸው። ከዚያ ዉጭ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ አካባቢ አሁን የክልሉ መንግሥት እጅግ እንደ ትልቅ ስኬት አድርጎ የሚያነሳውን የተራቆተ አካባቢን መልሶ የማልማት ሥራ በተሠራበት ወቅትም ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አድርገዋል። ከዚህ በፊት በረሃማ የነበሩ ድንጋያማ የነበሩ እጽዋት በቅለውባቸው ዉኃ ምንጭ ፈልቆባቸው ለምለም አካባቢ እንዲሆኑ ሲደረግ በአጭር ጊዜዉ ዉስጥ በዓይናችን ያየንበትንም እንቅስቃሴ ዉስጥ ቀዳሚ ተሳታፊም ነበሩ። ይህንንም አውቃለሁ ከዚያ ዉጪ ወጣቶችን ወደአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በጣም ብዙ ብዙ ጥረቶችንም አድርገዋል። ይህንንም አይቻለሁ።»

እንደጋዜጠኛ አርጋዉ ሁሉ በርካቶች የአካባቢ ተፈጥሮን በሚመለከት ከእሳቸው የማያልቅ ዕውቀት ለመቅሰም ችለዋል። ከእሳቸው ጋር የጀመሩትን የአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ እንቅስቃሴ አሳድገው በየግል በዚሁ ተግባር ላይ የተሠማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንም ያቋቋሙም አሉ። ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ በሙያው ረገድ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ እና ድጋፍ በተጨማሪ በግል አኗኗራቸውም ይህንኑ ያንፀባርቁ እንደነበርም አርጋው ያስታዉሳል፤

«አንደኛው ነገራቸው የሚበሉት የሚጠጡት የሚጠቀሙባቸው ቅሳቁሶች በሙሉ ከሚያምኑበት ከአካባቢ ጋር የተስማማ ወይም ከእንደዚህ አይነት ነገሮች ጋር የተስማማ እንዲሆን ነው ለምሳሌ ወደሥራ ሲመጡ ዕቃዎቻቸውን የሚይዙበት ቦርሳ፤ በየስብሰባዎቹ ላይ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ እንደውም ከፍተኛ ተቃዉሞ ያቀርቡ የነበሩት በፕላስቲክ የታሸገ ውኃ መቅረቡ፤ ሌሎች ሌሎች ነገሮችም አያስደስቷቸውም ነበር አንዳንዶቹንም ነገሮች አይጠቀሙም ነበር። ምግብ ላይም እንደዚሁ ናቸው በጣም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ተመርቶ የመጣ ምግብ ነው መመገብ ያለብን የሚል አቋም ነበራቸው። ይህንን አቋም በሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ያሳዩ ነበረ።»

Susan Edwards Gründerin des Institute for Sustainable Development Ethiopia
ወ/ሮ ሱ ከባለቤታቸው ጋር የአረንጓዴ ጀግና ሽልማት ሲቀበሉምስል ISD

ይህንን የወይዘሮ ሶስና ኤድዋርድስን ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚደረግ ልዩ ጥንቃቄ የሥራ ባልደረባቸው አቶ ግዛው ገብረ ማርያምም በሚገባ አስተውለውታል። የወይዘሮ ሶስና ሰብዕና ለሰዎች በመራራት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለፍጥረታት ሁሉ የተረፈ እንደሆነም ምሳሌ ጠቅሰው ያብራራሉ።

የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት መሥራች እና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ወይዘሮ ሱዛን ኤድዋርድስ የበርካታ ሽልማቶችም ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከልም፤ በያዝነው ዓመት መስከረም ወር መቀመጫዉን እዚህ ጀርመን ሀገር ካደረገው ኢንተርናሽናል ፌደሬሽን ኦፍ ኦርጋኒክ አግሪካልቸራል ሙቭመንት፤ በተፈጥሮ ግብርና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከባለቤታቸው ጋር ዋን ዎርልድ የተሰኘ የሕይወት ዘመን ሽልማት አግኝተዋል፤ ለዘላቂ ልማት ላበረከቱት አስተዋፅኦም እንዲሁ በ2004ዓ,ም ከስዊድን ሀገር የጉተምበርግን ሽልማት ተቀብለዋል፤ በ1999ዓ,ም ደግሞ በኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ላበረከቱት የዓመቱ የአረንጓዴ ልማት ጀግና ተብለው ሽልማት ተቀብለዋል።  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ