1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአርብ ታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017

የአርብ ታኅሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት «ቴክኒካዊ ውይይት» ለማድረግ መስማማታቸውን የአፍሪቃ ኅብረት ፣ኢጋድ ፣ዩናይትድ ስቴትስና የተመድ አወደሱ ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሱዳን ጦር ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት የገበያ ስፍራ የፈጸመው የአየር ጥቃት ግልፅ የጦር ወንጀል ነው አለ። ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩክሬን ዩናይትድ ስቴትስ በሰጠቻት የጦር መሣሪያዎች በሩስያ ምድር የሚገኙ ዒላማዎችን እንድትመታ እንደማይፈቅዱ ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4o87Z

አዲስ አበባ        የአፍሪቃ ኅብረት አሜሪካና የተመድ የኢትዮጵያና የሶማሊያን ስምምነት አወደሱ

የአፍሪቃ ኅብረት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ለማስቆም ከትናንት በስተያ የደረሱበትን ስምምነት ሳያዘገዩ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአፍሪቃ ኅብረት ጥሪ አቀረበ። የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት የስምምነቱን ጠቃሚነት አጽንኦት ሰጥተው በስምምነቱ የተካተቱትን አስፈላጊ እርምጃዎች ያለምንም ማዘግየት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በምህጻሩ ኢጋድም ስምምነቱን በደስታ መቀበሉን አስታውቋል። የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ፣ስምምነቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ አወድሰዋል። ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን ከፍጻሜ እንዲያደርሱ ጠይቀዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ስምምነቱን «የእያንዳንዱን ሀገር ሉዓላዊነት አንድነት እና ነጻነት እንዲሁም የግዛት አንድነት የሚያረጋግጥ ሲሉት ፣ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሬክ ደግሞ ሸምጋዩን የቱርክ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻንን አመስግነው ውጤቱንም በጎ ብለውታል።

ሁለቱን ሀገራት የሸመገሉት ኤርዶኻን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ጋር በዚህ ሳምንት ረቡዕ በተናጠል ከተነጋገሩ በኋላ ነበር ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት “ቴክኒካዊ ውይይት” ለማድረግ መስማማታቸውን ያሳወቁት። ከስምምነቱ በኋላ በወጣ የጋራ መግለጫ መሠረት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ቱርክ በመጪው የካቲት ወር ውይይት ለማድረግ ተስማምተዋል። በአራት ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ታቅዷል።

አምነስቲ      አምነስቲ የሱዳን መንግሥትን የአየር ጥቃት የጦር ወንጀል ሲል ከሰሰ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሱዳን ጦር ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት የገበያ ስፍራ የፈጸመው የአየር ጥቃት ግልፅ የጦር ወንጀል ነው አለ። በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ሥር በሆነችው በሰሜን ዳርፉር ግዛት ካብካብያ በተባለችው ከተማ ላይ በደረሰው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት በርካታ ሰዎች መካከል ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ካብካብያ የተጠለሉ ሲቭሎች ይገኙበታል።አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወታደራዊ አውሮፕላኖች በካብካቢያ ሳምንታዊ የገበያ ቀን ባሳለፍነው ሰኞ  በርካታ ሲቪሎች በተሰበሰቡበት ሰዓት ባዘነቡት ቦምብ በርካቶች መገደላቸውን ከከተማዋ የዐይን ምስክሮች መረጃዎች እንደደረሱትም አስታውቋል። ከሟቾቹ 15ቱ ጥቃት ሸሽተው ከቤት ንብረታቸው ሸሽተው ካብካብያ የተሰደዱ ሲቪሎች መሆናቸውንም ገልጿል።    የድርጅቱ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪቃ ሃገራት ዳይሬክተር ታይገር ቻጊታ ሲቪሎች የተሰባሰቡበትን የገበያ ስፍራን በቦምብ ማጋየት በሀገሪቱ ያለውን የጦር ወንጀል ማሳያ ነው ብለዋል።

የሱዳን ጦር ኃይል እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንዲሁም በሱዳን ግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ሌሎች ኃይሎች ሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ባስቸኳይ እንዲያቆሙም አምነስቲ ጠይቋል። በዚህ ጥቃትም ሆነ በሌሎች ሲቪል ሱዳናውያን ላይ ጥቃት የፈጸሙ  ለፍርድ እንዲቀርቡም አሳስቧል።

አንካራ      ኤርዶኻን ሱዳንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ለማስታረቅ  ጠየቁ

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረቸብ ጠይብ ኤርዶኻን በሱዳንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በሽምግልና ለመፍታት የሱዳን ጦር ኃይል መሪን በስልክ ጠየቁ። በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ቴክኒካዊ ውይይት እንዲያደርጉ ካስማሙት ከኤርዶኻን ቢሮ በወጣው መግለጫ መሠረት ኤርዶኻን ቱርክ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ በሽምግልና ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ለሱዳን ጦር ኃይሎች መሪ አብዱል ፈታህ አል ቡኽራን በስልክ ነግረዋቸዋል። በዚህም ሊሳኩ ካሰቧቸው ጉዳዮች መካከል  በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ማስፈንና ሀገሪቱን ከውጭ ጣልቃ ገብነት መከላከል መሆኑንም ገልጸዋል። የሱዳን መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለተቀናቃኛቸው ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል የጦር መሣሪያ ትሰጣለች ሲል ይከሳል።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበኩልዋ ክሱን አስተባብላ የሱዳን መንግሥት ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋር ሰላም ለማውረድ ለመደራደር ፈቃደኛ  አልሆነም ስትልም ከሳለች ። በሚያዚያ 2015 ዓም በዋና ከተማዋ ኻርቱም የተጀመረው የሱዳን ጦርነት ወደ ዳርፉርና ሌሎች ግዛቶች ተስፋፍቷል። ጦርነቱ ከገደላቸው በተጨማሪ 13 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቸው አፈናቅሏል።

ኪቭ      በትራምፕ ዘመነ-ሥልጣን የሩስያ ዩክሬን ጦርነት እጣ ፈንታ

ሩስያ ዛሬ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰነዘረች። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እንደተናገሩት ሩስያ ዛሬ 93 ክሩዝ እና ረዥም ርቀት ተወንጫዊ ሚሳይሎች ወደ ዩክሬን ተኩሳለች። ቁጥራቸው 200 የሚደርስ ድሮኖችንም አሰማርታ ነበር። ይህም እንደ ዜሌንስኪ ሩስያ የዛሬ ሦስት ዓመት ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ የኃይል ዘርፍ ላይ ያካሄደችው ከባድ ድብደባ ነው። የይክሬን ኃይሎች በአፀፋው ሀገሪቱ ከምዕራባውያን በተሰጣት F-16 ተዋጊ ጀቶች 11 ክሩዝ ሚሳይሎችን  ጨምሮ በአጠቃላይ 81 ሚሳይሎችን  መጥተው መጣላቸውeን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ  ጥላለች። ሞስኮ እንዳለችው የዛሬው ጥቃት ዩክሬን ረቡዕ ዩናይትድ ስቴትስ በሰጠቻት የሚሳኤል ስርዓት ዩክሬን በሩስያ ጦር ሰፈር ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ ነው። ዜሌንስኪ ዛሬ በቴሌግራም ገጻቸው ፣ዓለም በሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ በኅብረት እንዲነሳ ዳግም ተማጽነዋል። ይሁንና በመጪው ጎርጎሮሳዊው ጥር ወር በይፋ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በሚሆኑት በዶናልድ ትራምፕ ዘመነ-ሥልጣን ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን አስፈላጊ የሆነውን ወታደራዊ ድጋፍ መቀጠሏ አጠራጥሯል። ትራምፕ «የዓመቱ ታላቅ» ሰው ሲል ለሰየማቸው «ለታይም መጽሔት» በሰጡት ቃለ ምልልስ ዩክሬን ዩናይትድ ስቴትስ በሰጠቻት የጦር መሣሪያዎች በሩስያ ምድር የሚገኙ ዒላማዎችን እንድትመታ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የትራምፕ አቋም "ከእኛ አቋም ጋር ይስማማል." በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ትራምፕ ግጭቱን የሚያባብሰውን ይገነዘባሉ ብለዋል።

 

ብራሰልስ   የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪ ደላላዎችን ለመከላከል ያስችላል ያሉትን ረቂቅ ሕግ ላይ ተስማሙ

 

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋወሩ ደላሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ላይ ተስማሙ። በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ከተካተቱት ውስጥ ጥፋተኛ  የበሚባሉ ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ላይ የሚበየነው እሥርና የገንዘብ ቅጣት ይገኝበታል። 380 ሺህ ያልተፈቀዱ መሻገሪያዎች እንደሚገኙ ባለፈው ዓመት ተደርሶበታል። የአውሮጳ የፖሊስ ድርጅት ዩሮ ፖል እንዳለው ከስደተኞች 90 በመቶው ወደ ተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት በነዚህ መስመሮች የሚሻገሩት ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች በሚሰጡዋቸው አገልግሎት ነው።  በረቂቅ ሕጉ እንደተመለከተው አንድ ስደተኛ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኅብረቱ አባል አገር እንዲገባ ወይም እንዲቆይ የሚረዳ በምትኩም ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስ የሚቀበል ሰው እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እሥራት ይቀጣል። ስደተኛው በመንገድ ላይ ከሞተ ደግሞ እስራቱ ከ10 ዓመት በላይ ይሆናል። በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ማዘወራቸው የተረጋገጠ ድርጅቶች ደግሞ እስከ 40 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።  ረቂቁ ችግር ላይ የሚገኙ ስደተኞችን የሚረዱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ዒላማ ውስጥ ለማስገባት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

 

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።