የአካል ጉዳተኞችን ተግዳሮትና ተስፋ
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017
የዓለም ባንክ በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎች የአካል ጉዳተኝነት እንደሚያጋጥማቸው ያመለክታል። በዚህ ረገድ በተለይ በአዳጊ ሃገራት የእነዚህ ወገኖች ቁጥር ከፍ እንደሚልም ይገልጻል። የዓለም ባንክ አክሎም አካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው ውሱን እንደሆነ ነው የሚገልጸው። በአዳጊ ሃገራት የሚገኙት ትምህርት፣ ተገቢ የጤና አገልግሎት፣ እና የሥራ ቅጥር እድሎች ስለማያገኙ ለከፍተኛ ድህነት መጋለጣቸውንም አመልክቷል። ድህነት ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ ስለሚያደርግም ለአካል ጉዳተኝነት የመጋለጥ አጋጣሚን ሊያስከትል ይችላልም ባይ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንደማይታወቅ ነው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጊጆ የገለጹልን። ሆኖም ግን ከ13 ዓመታት በፊት የዓለም ባንክ እና የዓለም የጤና ድርጅት በጋራ ያወጡት መረጃ ከመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር 17,6 በመቶው አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን ይህም ማለት ከ20 ሚሊየን በላይ እንደማለት መሆኑንም አቶ አባይነህ አመልክተዋል።
በዚህ ስሌት መሠረት ወደ 20 ሚሊየን የሚሆን የአካል ጉዳተኛ ባለባት ኢትዮጵያ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ የተለያዩ አገልግሎቶች ምን ያህል እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው የሚለው በየጊዜው ዋነኛ መነጋገሪያ እንደሆነ ነው ያነጋገርናቸው ወገኖች የገለጹልን። ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተገናኘ ጥሩ ጥሩ ሕጎች እንዳሉ የገለጹልን ዓይነስውር መምህርት ተግባራዊነቱ ግን አሁንም ይቀራል ባይ ናቸው።
ቅጥርን በሚመለከት በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በይፋ የሚነገር ሆኖም አካል ጉዳተኞችን ወደጎን የሚገፋ አሰራር እንደሚያጋጥም ሁሉ አንዳንዶቹ እንደውም ቅድሚያ የሚሰጡ መኖራቸውንም አንስተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት ለምሳሌ ሕንጻዎች የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንደሚገነቡ እየተነገረ፤ የእግር ጉዳት ያላቸው ወገኖች የሚንቀሳቀሱባቸውን ተሽከርካሪዎች ይዘው በአንዳንድ ወሳኝ ቦታዎች ካሰቡበት ለመድረስ የሚቸገሩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በየመንገዱ ያለማመላከቻና መከለያ የሚከናወኑ ቁፋሮዎችም ለዓይነስውሮች ፈተናዎች መሆናቸው አልቀረም።
የአካል ጉዳተኞች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ሊገነዘብ የሚችለው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን በሚመለከት የወጡት ሕጎች የቆዩ መሆናቸውን ሆኖም አሁን የተሻሻለ ሕግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይናገራሉ ።
ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ነው ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ,ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የታሰበውን የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት ይፋ የሆኑ የተመድ ዘገባዎች ያመለከቱት ነው። በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆናቸውም ተገልጿል። በጎርጎሪዮሳዊው 1992 ዓ,ም የተመድ በወሰነው መሠረት የአካል ጉዳተኞች ቀን በየዓመቱ ይታሰባል። የዘንድሮው መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ አቅም አጎልብተን የመሪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ በማስቻል ዘላቂ የልማት ግብን እናሳካለን የሚል ነው።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ