የጀርመኑ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት በአውሮጳ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅን አገኘ
ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016የአውሮጳ ህብረት 27 አባል አገሮች ካለፈዉ ሃሙስ ጀምሮ እስከ ትናንት እሁድ ድረስ የፓርላማ ወኪሎቻቸውን ሲመርጡ ዉለዋል። በአራት ቀናቱ የአዉሮጳ ህብረት ሃገራት ምርጫ ከ 370 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለመምረጥ መመዝገቡ ተነግሯል። ከየሃገራቱ የሚወጡ የምርጫ ዉጤቶች እንደሚያሳዩት በአብዛኛዉ የህብረቱ አባል ሃገራት ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ምርጫዉን እንዳሸነፉ ነዉ። በፌዴራል ጀርመን የምርጫ ጉዳይ ዋና ተጠሪ ዛሬ ማለዳ እንዳስታወቁት በጀርመን ምርጫ ቆጠራ መሰረት በሃገሪቱ ዉስጥ ከነበሩት 400 የምርጫ ጣብያዎች የተሰጠዉ ድምፅ ቆጠራ ዉጤት፤ የክሪስትያን ዲሞክራቲክ ህብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት በጋራ 30፤ በመቶ ድምፅን በማግኘት ከፍተኛዉን ድምፅ አስመዝግበዋል። በፖለቲካ ስደተኞችና የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በሚሰጣቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች የሚታወቀዉ አማራጭ ለጀርመን በምህጻሩ AFD የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ በጀርመን በተካሄደዉ የአዉሮጳ ምርጫ ዉጤት ሰንጠረዥ 15,9 በመቶ ድምፅን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ጀርመን መንግሥት የሆነዉ የሶሻል ዲሞክራቶች (SPD) የአረንጓዴዎቹ (die Grünen) እና ሊበራል (FDP) ፓርቲዎች ናቸዉ። የሶሻል ዲሞክራቶች (SPD) 13,9፤ አረንጓዴዎቹ (die Grünen) 11,9 እንዲሁም፤ ሊበራል ፓርቲዉ (FDP) 5,2 በመቶ ድምፅን አግኝተዋል።
የኑሮ ውድነት እና ስራ አጥነት፣ የዩክሬን-ራሽያ ጦርነት፣ የስደተኞች እና ፍላሲያን ጉዳይ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ዋና ዋና አጀንዳዎች በነበሩበት የአውሮጳ ፓርላማ ምርጫ፣ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ የሚመሩት የጀርመን ጥምር መንግስት በአውሮጳ ፓርላማ ምርጫ ደካማ ውጤት አስመዝግቧል። በአንጻሩ፣ የመሀል ቀኙ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት (CDU) በአውሮጳ ፓርላማ ምርጫ አብዝሃ ድምጽ (30%) በማግኘት ቀዳሚ ሆኗል።
አሁን ላይ በተቃዋሚ ጎራ ያለው CDU መሪ ፍሬድሪክ ሜርስ፣ የፌደራሉ መንግስት ቆም ብሎ እንዲያስብ እና ፖሊሲውን እንዲያስተካክል መራጩ ሕዝብ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል ብለዋል። ሁኔታዎች አሁን ባሉበት እንደማይቀጥሉም ጥምሩ መንግስት ሊያውቅ ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
ቀኝ አክራሪው ኤ.ኤፍ.ዲ (AfD) ፓርቲ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ነው ያጠናቀቀው። ከአጠቃላይ መራጭ ከ16 በመቶ ገደማ ድምጽ አግኝቷል። ፓርቲው በተለይ በምስራቃዊ ጀርመን አካባቢዎች ከሁሉም ፓርቲዎች የላቀ ድምጽ ነው ያገኘው። ከኒዮ-ናዚ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው በሚል እና በከረረ ፀረ-ስደተኛ አቋሙ ሰበብ ኤ.ኤፍ.ዲ (AfD) የምርጫ ዘመቻ ጅማሮ ጥሩ አልነበረም።
ከአስርት ዓመታት ወዲህ ዝቅተኛ ድምጽ ያገኘው የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (SPD) “በተገኘው ውጤት አንገታችንን አንደፋም፤ ይልቁኑ ከከዚህ በፊቱ በላቀ እንበረታለን” ሲል በመሪው ላርስ ክሊንግባይል በኩል አስታውቋል። SPD 14 በመቶ ገደማ ድምጽ ነው ያገኘው።
የጥምር መንግስቱ አባል አረንጓዴ ፓርቲም ከግምት ዝቅ ያለ ውጤት ነው ያገኘው። ውጤቱን ተከትሎ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት (CDU) እህት ፓርቲ ክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን (CSU) መሪ እና የባቫሪያን ፌዴራል ግዛት ፕሬዚዳንት ማርኩስ ዞውደር እንደ ፈረንሳይ ሁሉ በጀርመንም አስቸኳይ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ይሁንና የጀርመን መንግስት ግን የአስቸኳይ ምርጫ እቅድ የለኝም ሲል በቃል-አቀባዩ በኩል አስታውቋል።
ለምርጫ ከተመዘገበው መራጭ 64.8 በመቶው ድምጹን የሰጠበት እና ከጀርመን ውህደት ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ የተሳተፈበት የትናንትናው ምርጫ ውጤት አገሬው በመንግስቱ የአስተዳደር ላይ ያለውን ቅዋሜ ያሳየበት ነው ተብሏል። በአውሮጳ ኅብረት ባለተጽዕዋ ጀርመን እና በሌሎቹም የኅብረቱ አገራት የተመዘገበው አህጉራዊ ምርጫ ውጤት በኅብረቱ ቀጣይ የፖለቲካ እና የፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተንታኞች ይናገራሉ። ከ720 የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ወንበሮች 96ቱ በጀርመን የተያዘ ነው።
በዘብድሮዉ ማለትም በ 2024 የአውሮጳ የፓርላማ ምርጫ በህብረቱ አባል አገራት ውስጥየሚንቀሳቀሱ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ብዙ ወንበር እያገኙ ነዉ። በጀርመን አማራጭ ለጀርመን በምህጻሩ AFDን ጨምሮ፤ በግሪክ፤ በፖላንድ፤ በስፔን፤ ኦስትሪያ፤በፈረንሳይ፤ በጣልያን እንዲሁም በሃንጋሪ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ብዙ ድምጽ አግኝተዋል። በጀርመን የምርጫዉ ሂደት፤ እና በቅድምያ በወጡ ዉጤቶች ላይ የተሰጡ የህዝብ አስተያየቶች ምን ይመስላሉ። ይህ በጀርመን የተገኘዉ የምርጫ ዉጤት በቀጣይ የአዉሮጳ ህብረት ጉዙ ምን አንደምታ ይኖረዉ ይሆን? በፍራንክፈርት ከሚገኝ ወኪላችን ጋር ተወያይተናል።
አዜብ ታደሰ
መሳይ ወንድሜነህ