የአዉሮጳ ሕብረት ሚንስትሮች ለዩክሬን ተጨማሪ ድጋፍ ሰጡ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2015
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ለዩክሬን ተጨማሪ ጦር መሳሪያና ወታደራዊ ቁሳቁስ መግዢያ 3.5 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ወሰኑ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ ትናንት ሉክዘምበርግ ዉስጥ ባደረጉት ስብሰባ ለዩክሬን የሚሰጠዉ ወታደራዊ ድጋፍ ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ መሆን እንዳለበት አዉስተዋል።ሚንስትሮቹ የተለያዩ ርዕሶችን ቢያነሱም አብይ ትኩረታቸዉ ግን ቫግነር የተሰኘዉ የሩሲያ የቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን የቀሰቀሰዉ አመፅ፣ የአመፁ መክሸፍና በዩክሬን ጦርነት ላይ የሚያሳድረዉ ተፅዕኖ ነበር።
አመጹ ከሰላሳ ስድስት ሰአት እንዳልበለጠና እንደበረደ፤ የሚነገር ቢሆንም ክስተቱ ግን በተለይ በዩክሬን ምክኒያት ከሩሲያ ጋር ግብ ግብ በገጠሙ ምራባውያን ዘንድ በክፍተኛ ደረጃ እያነጋገረ ነው። የትናንቱ የሉክዘምበርጉ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባም ለዩኪሬን ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ ለማጽደቅ፣ በህብረቱና ላቲን አሜሪካ ግንኙነትና በሌሎች ቀደም ብሎ በተያዙ አጀንዳዎች ለመወያየትና ለመወሰን ታስቦ የተጠራ ቢሆንም፤ ሚኒስትሮቹ ግን በሩሲያው ወታደራዊ አመጽ ትኩረት ስተው ሲወያዩ እንደዋሉ ነው የተገለጸው። የህብረቱ የውጭ ጉድይ ሀላፊና የስብሰባው መሪ ሚስተር ቦሪየል ይህንኑ ሚኒስትሮቹ በሰፊው የተወያዩበትን የሩሲያውን ክስተት፤ ‘ እነዚህ ባለፉት ቀናት የታዩት ክስተቶች የሩሲያ መንግስትና የፕሬዝዳንት ፑቲን ተአማኒንነት የተዳከመ መሆኑ የታየበት፤ የፖለቲካ ስራቱ ስንጥቅም ግልጽ የወጣበት ነው በማለት ገልጸውታል። ሚስተር ቦርየል አክለውም ሩሲያ ባላት ሀይልና አቅም አሁን እንዳደረገችው ሰላማዊ ጎረብቶቿን እንዳትወር ስጋት እንዳለን ሁሉ፤ የኒውክለር ሀይል ባለቤት በመሆኗም የውስጥ ፖለቲካዋ አልመረጋትና ተገማች አለመሆኗም አሳስቢ ነው ብለዋል።
በስብሰባው ሚኒስትሮቹ የተደባላለቁ ስሜቶች የታዩባቸው መሆኑን ስብሰባውይን የተክታተሉ ምንጮ ገልጸዋል፡፤ ምንም ይሁን ምን በሩሲያ ሀይሎች መካከል ልዩነት መፈጠሩ ከሩሲያ አንጻር ለሚደረገው ትግል ጠቃሚ የሆነ ክስትት ነው የሚሉት ወገኖች፤ ሁኒታው ለዩክሬን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ጥሩ እድል ሊፈጥር እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ሌሎች ደግሞ ሁኔታው እንደውም ሩሲያ በቀላሉ ደንበሮችን በማለፍ ጥቃት ልትፈጽም የምትችል መሆኑን የሚያመላክት ነው በማለት ህብረቱ በተለይ በምስራቁ በኩል ሀይሉን ማጠናከር እንዳለበት ሲያሳስቡ ተስምተዋል ። ሁሉም ግን ሩሲያ አሁን ለገጠማት ቀውስ ምክኒያቱ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት መሆኑን ይስማማሉ። ሚስተር ቦርየል በስብሰባው ከነበረው ክርክር አንጻር የተደረበትን ድምዳሜ ሲገልጹ፤ ‘ በውይይታችን የድረስንበት መደምደሚያ \ ለዩክሬን የሚደረገው ወታደራዊ እርዳታ ከመቼውም ግዜ አሁን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ነው በማለት ሚኒስትሮቹ ተጨማሪ የ3.5 ቢዮን ኢሮ እርዳታ ያጸደቁ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ እንደተጠበቀው እየገፋ አለመሆኑ እየተገለጸ ቢሆንም፤ ይህ የሩሲያ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ግን፤ ለዩክሬኖች ትልቅ ሞራል ሊሰጥና ጦርነቱንም ሊለውጥ ይችላል በማለት ነው በተለይ ምራባውያኑ ተስፋ የሚያደርጉትና ድጋፋቸውንም እያደርጉ ያሉት። ሌሎች ግን ይህ 36 ሰአት የዘለቀው ወታደራዊ አመጽ ይልቁንም ፕሬዝዳንት ፑቲን በሰራዊትቸው ውስጥ የነበረውን የእዝና አመራር ጉድለቶችን በመሙላት የዩክሬንን የመልሶ ማጥቃት ዘምቻ ለመቁቋም የሚያስችል አደራእጃጀትና ብቃት እንዲመሰረቱ ሊረዳቸው ይችላል ባይ ናቸው።
በሩሲያ የሚፈጠር የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት ከዩክሬን ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት ላይ ሊፈጥር ከሚችለው ተጽኖ አንጻር ብቻ ማየት እንደማይገባ የሚከራከሩ ባለሙያዎች፤ ሩሲያ ሀያል ሁና ከምትፈጥረው ስጋት ባላነሰ የኑክለር ሀይል ባለቤት በመሆኗ ቀውስ ውስጥ ብትገባና የፖለቲካ አለመረጋጋ ቢፈጠር ችግሩ ከዩኪረን አልፎ ለሎችንም በተለይም ለጎረቤት ያውሮፓ አገሮች ሊተርፍ ይችላል በማለት ያሳስብሉ።
ቪክቶር ኦሌቪች የተብሉ በሞስኮ የወቅዊ ፖለቲክ ማዕከል መንግስትዊ ያልሆነ ድርጅት ተመራማሪ እንደሚሉት፤ በሩሲያ የሚፈጠር የፖለቲካ ቀውስ ለማንም አይጠቅምም ወይም ድልም አይሆንም። ሩሲያ በታሪኳ የተለያዩ የጦርነትና የአብዮት ግዚያት እንዳሳለፈች የሚናገሩት ኦሌቪቺ፤ እ እ በ1991 ዓም የሶቭየት ህብረት ሲፈርስ የነበረው የኒውክለር ሀይል በአሚርካ አስተባባሪነት ወደ ሩሲያ እንዲሰበሰብና ባስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅ ተደርጎ ነበር በማለት አሁን የዚህ አይነት ሁኒታ ቢፈጠር ግን ማንም ሀላፊነቱን የሚወስድ እንደሌለና በሩሲያ ሁከትና ስራተአልብኝነት መመኘት ከሩሲያ አልፎ ለሎችም አደገኛ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
በአሁኑ ወቅት ጦርነትን በአሸናፊነት መወጣት አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ሲሆን፤ በተለይም የኒውክለር ሀይል ባለቤት ከሆን ሀይል ጋር የሚደረግ ጦርነት አጠቃላይ ውድመት ሊያስከትል እንደሚችልም የሚታወቅ በመሆኑ፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የገጠመችውን ጦርነት በድል ብቻ እንድትወጣ ግፋ በለው የሚሉ የምራብ ሀይሎች ቆም ብለው እንዲያሱብ ሚስተር ቪክቶር ኦሌቪች ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት አስተያየት አጽነኦት ሲያሳሱቡም ተደምጠዋል።
ገበያው ንጉሴ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገዘ