የአውሮጳ ኅብረት ለኢትዮጵያ የልማት ዕርዳታ የሚሰጥበትን ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን ገለጸ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2015የአውሮጳ ኅብረት ለኢትዮጵያ የልማት እርዳታ የሚሰጥበትን "መልቲ አንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" የተባለ ማዕቀፍ ዳግም ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። በጆሴፕ ቦሬል የሚመራው የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ ባካሔደው ስብሰባ ያሳለፈው ውሳኔ "በመላው ኢትዮጵያ ሰላማዊ የግጭት አፈታት፣ ዕርቅ፣ መረጋጋት እና መልሶ ግንባታ እንዲሁም የማክሮ ኤኮኖሚውን መረጋጋት" ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ነው።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ማዘጋጀት በጀመሩበት ወቅት ከአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል የተሰማው ዜና በጎ ቢሆንም ሒደቱ በደቡብ አፍሪቃ በተፈረመው ግጭትን በማቆም ሥምምነት አተገባበር ላይ የተንጠለጠለ ነው። ማዕቀፉ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ሥምምነት "ዘላቂ አተገባበር መሠረት" እንደሚጀመር የአውሮጳ ኅብረት ቃል አቀባይ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ጠቀም ያለ የገንዘብ ዕገዛ ያገኘችበት "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" ዳግም ሊጀመር የሚችለው ከጎርጎሮሳዊው 2024 እስከ 2027 የመካከለኛ ጊዜ የግምገማ ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚሆን የኅብረቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል። በዚህ ማዕቀፍ የአውሮጳ ኅብረት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ለመግለጽ የኅብረቱ ቃል አቀባይ እንዳሉት "ጊዜው ገና ነው።"
ይኸ ውሳኔ "እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው" እንደሆነ በጀርመኑ ሔለባ ባንክ የኤኮኖሚ ትንተና ባለሙያው ፓትሪክ ሐይኒሽ ያምናሉ። ሐይኒሽ የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመሰብሰቡም በፊት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሻከረውን ግንኙነት የሚያድስ ውሳኔ ይጠብቁ እንደነበር ገልጸዋል።
በብሪታኒያው የልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ "ምንአልባት ከአገሪቱ ኤኮኖሚ ግዝፈት አንጻር ትልቅ ላይመስል ይችላል። ነገር ግን ይኸ እርዳታ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጣም ያተኮረ ስለሆነ ትልቅ ተጽዕኖ አለው። መንግሥት በወጪው ብዙ ጊዜ መሠረተ-ልማት ላይ ነው የሚያተኩረው። ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ምዕራባውያን ወይም ያደጉት አገሮች አጋሮች የሚሰሩት ሥራ ትልቅ ተጽዕኖ አለው" ሲሉ ፋይዳው ላቅ ያለ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
የአውሮጳ ኮሚሽን ከዚሕ ቀደም በጎርጎሮሳዊው ከ2021 እስከ 2027 ባሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ የሚሰጥበት "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" አዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ሳይጸድቅ ቀርቷል። ኅብረቱ የልማት ዕርዳታውን በቀጥታ ለኢትዮጵያ ከመስጠት ይልቅ ለሰባት ዓመታት ለአገሪቱ ከተዘጋጀው ዕቅድ ውጪ ለነበሩ ሥራዎች እየቀነጨበ መጠቀምን መርጦ ነበር።
የአውሮጳ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ባለፈው ሐምሌ 2014 ባካሔደው ስብሰባ ላይ የተገኙት በአውሮጳ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ክፍል የምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዘርፍ ኃላፊ ዲዴየር ቬርሰ ማዕቀፉ ሳይጸድቅ የቀረው ኅብረቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም በሚያደርገው ግፊት በተከተለው መርኅ ሳቢያ እንደሆነ አስረድተዋል።
ይኸ "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" እንዲቀጥል በኅብረቱ ከተወሰነ የከባቢ አየር ለውጥን ለመቋቋም በሚከወኑ ሥራዎች፣ ዘላቂ ግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት አገልግሎቶች፤ የስደተኞች እና ፈላሲያን ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል። ማዕቀፉ የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላም ግንባታ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ጭምር ያካትታል። ይሁንና ዲዴየር ቬርሰ እንዳሉት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት የተዘጋጀው ዕቅድ "ጊዜው ሲደርስ" መሻሻሉ አይቀርም።
"የአውሮጳ ኅብረት እነዚህን እርዳታዎች ብዙ ጊዜ እንደ ካሮት እና ዱላ ይጠቀምባቸዋል። ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ጥሰት በሚፈጸምበት ወቅት እነዚህ ፕሮግራሞች ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ይኖራል" የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ተፈጽመዋል ለሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ያስታውሳሉ።
"አሁን ያለው የግጭት ማቆም ሥምምነት አጀማመሩ ጥሩ ቢሆንም ዘላቂነት እንደሚኖረው እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ። ሁለቱም አካላት፤ መንግሥትም እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች [ሥምምነቱን] የሚያከብሩበት ሁኔታ ዘላቂነት እንዲኖረው ይፈልጋሉ" የሚሉት ዶክተር ቀልቤሳ ለኢትዮጵያ የሚዘጋጀው "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" "ይጸድቃል" የሚል እምነት አላቸው።
ኢትዮጵያ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ያላት ግንኙነት ሲሻክር የተቋረጠው "መልቲአንዋል ኢንዲኬቲቭ ፕሮግራም" ብቻ ሳይሆን ዓመታዊ የበጀት ድጎማ ጭምር ነው። ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው 88 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ የተቋረጠው ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በጥቂት ወራት ልዩነት ውስጥ ነበር። ሶስት ክልሎች አዳርሶ ብርቱ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ የፈጠረው ጦርነት በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት ከቆመ ከስድስት ወራት ገደማም በኋላ የአውሮጳ ኅብረት ያቋረጠውን የበጀት ድጋፍ ለመጀመር ቅድመ-ሁኔታዎች አስቀምጧል።
ኅብረቱ የተቋረጠውን የበጀት ድጋፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት መስጠት የሚጀምረው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ቀስ በቀስ ወደ መደበኛነት ሲመለስ እንደሆነ የኅብረቱ ቃል አቀባይ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። ይኸ ሒደት ኅብረቱ ባስቀመጣቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ የሚመረኮዝ ነው። የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ለቅቆ መውጣትን ጨምሮ ግጭት ማቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ ኅብረቱ ያስቀመጣቸው ቅድመ-ሁኔታዎች ናቸው።
በአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ የጸደቀው ውሳኔ የግጭት ማቆም ሥምምነት አተገባበር የታዩ መሻሻሎችን በአዎንታ እንደሚመለከት ለዶይቼ ቬለ የገለጹት የኅብረቱ ቃል አቀባይ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና የሽግግር ፍትኅን ጨምሮ ቀሪ ጉዳዮችን መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት "በኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ለሀገሪቱ አሳሳቢ ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታ" መፍትሔ ለማበጀት የሚያደርገውን ጥረት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እንዲደግፉ የአውሮጳ ኅብረት በውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ምክር ቤት በኩል አበረታቷል። የኢትዮጵያ አበዳሪ ሀገራት በቡድን 20 በኩል የታቀደውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ በፍጥነት እንዲያጠናቅቁም ጥሪ አቅርቧል።ለዕዳ አከፋፈል ሽግሽጉ የሚያስፈልገው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ፕሮግራም እየተገባደደ መሆኑን ፓትሪክ ሐይኒሽ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ሐይኒሽ በሚቀጥሉት ስምንት ወራት ኢትዮጵያ በቡድን 20 በኩል የጀመረችው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ይጠናቀቃል ብለው ይጠብቃሉ።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ