የአውሮፓ ኅብረት ለስምንት ኢትዮጵያዊያን የመብት ተሟጋቾች ሽልማት ሰጠ
ዓርብ፣ ግንቦት 23 2016የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ በኢትዮጵያ "ሹማን" የተባለውን ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ለስምንት ኢትዮጵያዊያን የመብት ተሟጓች ግለሰቦች እና ድርጅቶች ሸለመ።
ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በማስፋፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ ያበረከቱ በሚል ከተሸለሙት ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይገኙበታል። ሽልማቱ በሰብዓዊ መብት ሥራዎቻቸው ምክንያት በእሥር ወይም በስደት ላይ ለሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ተበርክቷል።
የአውሮፓ ኅብረት የሽልማት ማጠንጠኛ ይዘት
የአውሮፓ ኅብረቱ ልዑክ በኢትዮጵያ ለመብት ተቆርቋሪዎች ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጠው ሽልማት፤ ኅብረቱም ሆነ በተናጠል አባል ሀገራቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጥረት እያደረጉ መሆኑ፣ ሂደቱ የማያቋርጥና ቋሚ እንደሆነ የልዑኩ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተናግረዋል። ኅብረቱ ግለሰቦችን በመጠበቅና በማብቃት፣ አካታች ፣ ጠንካራ እና ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ በመገንባት እና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ እየሠራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰሞኑን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማጣራት ጀምሯል
"በአለም ላይ እንደምናየው ሰብአዊ መብቶች ለአንዳንዶች ሁሉም ነገር ላይሆኑ ይችላሉ። ግን ያለ ሰብዓዊ መብት፣ ያለ የሕግ የበላይነት፣ ያለ ፍትሕ ሁሉም ነገር በፍጥነት ከንቱ ይሆናል። መብታችን፣ ነጻነታችን፣ ብልጽግናችንን በጽኑ መሰረት ለመምራት ብርታት የሚሆነን ዛሬ እየተወያየንበት ያለውን የሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳይ ነው።"
ከተሸላሚዎች የሁለቱ አስተያየት
ሽልማቱ "ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ሰብዓዊ መብቶችን፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በማስፋፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎች" የሚሰጥ ሲሆን ይህ ሽልማት ከተበረከተላቸው መካከል ዶክተር ዳንኤል በቀለ እና አቶ ያሬድ ኃይለማርያምን እውቅናው ስለሚኖረው ፋይዳ ዶቼ ቬለ ጠይቋቸዋል።
"ሰብዓዊ መብቶች የተከበረባት፣ ሰብዓዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ሀገር በኢትዮጵያችን ውስጥ ለማየት እንድንችል ለሰብዓዊ መብቶች ሥራ እና ለሰብዓዊ መብቶች ሠራተኞች ድጋፍ እና እውቅና መስጠት ጥሩ እርምጃ ነው" - የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል በቀለ
"እዚህ ቦታ ላይ በአካል ላልተገኙ ነገር ግን ለሰብዓዊ መብቶች ሲታገሉ ከሚወዷት ሀገራቸው በየስደት ላሉ፣ በየ እሥር ቤቱ ለሚገኙ ፣ ስለ ዕውነት፣ ስለ ፍትሕ ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት ድብደባ፣ ወከባ ለተፈፀመበቸው ሰዎች ሁሉ ስም ያልተሰጠው ለሁሉም የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች የተበረከተው ስጦታ ከሁሉም ከተሸለምነው ሁሉ በጣም ስሜት የሚነካ ነው" -ብለዋል፤አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማእከል ዋና ዳይሬክተር።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ
የሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ብቸኛ የሰላም መንገዶች ናቸው ያሉት ዶክተር ዳንኤል በቀለ፣ በእነዚህ ሂደቶች ከቀውስ ውስጥ እንወጣለን ብየ አምናለሁ፣" ስለሆነም ሁሉም በሂደቶቹ ሊሳተፍ ይገበል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ፈተና እንደሆነ ቀጥሏል። ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ሥጋቶች አሉ። ዋነኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን የሚከሰተው በግጭት ዐውድ ውስጥ ነው።"
ይህን ሽልማት "ለሰብዓዊ መብት ሲታገሉ ለታሰሩ፣ ለተሰደዱ፣ ለተዋከቡ ሁሉ የተሰጠ አድርጌ እወስደዋለሁ" ያሉት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ሰላም የማይኖር ከሆነ የሚደርሱ ቀውሶች ይቀጥላሉ ብለዋል።
"በአብዛኛው የሀገሪቷ ክፍሎች የማያቆሙ ግጭቶች እየተካሄዱ ነው። በጣም አስከፊ የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው። ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ሁኔታ ቶሎ ካልመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደርሱ ሰብዓዊ ቀውሶች እየጨመሩ፣ እየከፉ ነው የሚመጡት።"
ሽልማቱ ለማን ለማን ተበረከተ ?
የአውሮፓ ኅብረት ትናንት ምሽት "ሹማን" የተባለውን ሽልማት ለዶክተር ዳንኤል በቀለ፣ ለአቶ ያሬድ ኃይለማርያም፣ ለአቶ ጋሪ ኢስማኤል ዩሱፍ ፣ ለአቶ ጌቱ ሳቀታ፣ ለባህል ተወዛዋዥ መላኩ በላይ፣ ለጠበቃ መልካሙ ኦጎ፣ ለኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እንዲሁም በሰብአዊ መብት ሥራቸው ምክንያት በእሥር ቤት ውስጥ ወይም በስደት ላይ ለሚገኙ ሁሉ አበርክቷል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሰለሞን ሙጨ
ፀሐይ ጫኔ
እሽቴ በቀለ