የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በከንያ ስምጥ ሸለቆ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 22 2015
ዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ፍጥነት ለመግታት በሚል ድርድር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ጊዜያትም በተለይ በኢንዱስትሪ ያደጉት እና ለብክለቱ የታሪክ ተጠያቂነት አለባቸው የሚባሉት ባለሀብት መንግሥታት ተግባብተው ወሳኝ የሚባል እርምጃ መውሰድ አልቻሉም። በዚህ መሀል ግን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው በርካታ ሃገራትን እያዳረሰ ነው። ኬንያ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ሐይቆች ከመሬት ወለል ከፍታቸው እየጨመረ መምጣቱ ማሳሰብ ጀምሯል። ሳይንቲስቶች በኬንያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ጨዋማው ቦጎሪያ ሐይቅ አሁን በሚታየው ፍጥነት ከፍታውን እየጨመረ መቀጠሉ እንደማይቀር ነው የሚናገሩት። በመጠነኛ ተራሮች የተከበበው ሐይቅ ከፍታው መጨመሩን ውጦ ቁመታቸውን ባሳጠራቸው ዛፎች በቀላሉ መለየት ይቻላል። የአካባቢው ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት ያለማሰለስ ሲጨምር ያስተዋሉት ሐይቅ እያደር መንቀሳቀሻ መንገዶቻቸውን ሁሉ እንደሸፈነው ይናገራሉ። በአካባቢው የሐይቁ መጠን መጨመር ብቻ ሳይሆን ያልተለመደ አይነት ከባድ ዝናብም እንደሚደጋገም ነው የገለጹት። የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን ተጽዕኖ ለመመልከት ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሰችው የዶቼ ቬለ ዘጋቢ ኢዲዝ ኪማኒ ከነዋሪዎች እንደተረዳችው ሁኔታው በኑሯቸው ላይ ጫናውን አክብዷል። የሐይቁ ውኃ መጨመር የምግብ ቤቷን እንድዘጋ ያስገደዳት ወጣቷ ቼላጋት ኪፕቹምባ፤ የሐይቁ ከፍታ ድንገት የሆነ አይደለም ትላለች፤
«ይኽ ውኃ በአንድ ቀን አይደለም እንዲህ የሆነው ቀስ በቀስ እያደር ነው ከዚህ የደረሰው። እናም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ቤታችንን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ አፍርሰን መልቀቅ ነበረብን።»
ቼላጋት ኪፕቹምባ የንግድ ቤቷን አንዴ ብቻ ሳይሆን ዳግም ለማፍረስ የማትገደድበት ማረጋገጫ ለጊዜው የለም። ይኽን መሰሉ ድንገተኛ ክስተት ያጋጠማት እሷን ብቻም አይደለችም፤ ሌሎች በርካቶችም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሶባቸዋል። ከግለሰቦች ንብረት አልፎ የኬንያ መንግሥት የዱር እንስሳት አገልግሎት በዚህ ስፍራ የሚገኝ ጽሕፈት ቤቱን ከፍታው በጨመረው ሐይቅ ተቀምቶ ገሚሱ ሕንጻው በውኃ ተውጧል። ውኃው ከአካባቢው መኖሪያ ቤቶች ከሚወጣው የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ጋርም በመገናኘቱ ሽታው ሊቀርቡት እንደሚያስቸግር ነው ዘጋቢዋ ያመለከተችው።
ሐይቁ ላለፉት ሰባት ዓመታት ከፍታውንም ሆነ ወርዱን በ60 በመቶ መጨመሩን ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የውኃው መጨመር ዘንድሮ ደግሞ ይበልጡን ከፍ እንዳለ ነው በአካባቢው ሀገር ጎብኚዎችን በማስተናገድ ላይ የነበሩ ወገኖች የሚገልጹት። የቱሪስት መስህብ በሆነው የኬንያ ስምጥ ሸለቆ ሐይቆችን ከበው የሚታዩት አብዛኞቹ ሆቴሎች በውኃ በመዋጣቸው ሥራው ተቀዛቅዟል። ሀገር አስጎብኚ የሆነው ፎክስ ኦቴምቦ
« እዚህ ነው ያደኩት፣ የሕይወቴን የመጀመሪያ 20 ዓመታት ያሳለፍኩበት ስፍራ ነው። ይኽ በልጅነቴ እየቦረቅኩ የተጫወትኩበት ሜዳ ነበር። እንዲህ ተበላሽቶ ማየት በጣም ያሳዝናል። ለልጆቼ ምን ልነግራቸው ነው?»
የሚለው ከፍታውን ጨምሮ አካባቢውን ያጥለቀለቀው ሐይቅ ላይ በታንኳ እየተመላለሰ ነው። ለወትሮው እሱ ሀገር ጎብኚዎቺን እያመጣ ያሳርፍባቸው የነበሩ ማራኪ የጎጆ ሆቴሎች በውኃው ተውጠው ጣራቸው ብቻ ይታያል፤ የአካባቢውን ትምህርት ቤት ሕንጻ ከፊሉን ውኃው ሸርሽሮት ፈራርሷል።
ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ?
መንገዶችን ጨምሮ ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም እየሰመጡ ነው። የኬንያ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውኃ ዕለት በዕለት እየጨመረ ሲታይ እየባሰ በሚሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ያሰጋል። ተመራማሪዎች አሁን በኬንያ ስምጥ ሸለቆ ስነምህዳር አደጋ ማንዣበቡን እያሳሰቡ ነው። ውኃው መጨመሩ በዚሁ ከቀጠለም ንጹሕ ውኃ ያለው ባሪንጎ ሐይቅ እና ጨዋማው ቦጎሪያ ሐይቅ ሊዋሀዱ ይችላሉ፤ በሁለቱ መቀየጥ የሚፈጠረው ብክለት ደግሞ የአካባቢውን የስነምህዳር ሚዛን ሊያጠፋው ይችላል ባይ ናቸው።
የሐይቆቹ ውኃ መጋቢዎች ከማው ተራራ ውስጥ የሚመነጩ ወንዞች ናቸው። ተራራው በቅርቡ ነው በደን ጭፍጨፋ ከደረሰበት መራቆት ያገገመው። በስፍራው ከ50 ዓመታት በላይ የእጸዋት እና ተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ ላይ የቆዩት ዴቪድ ዌስተርን ለተፈጠረው መዛባት የደን መራቆት ከበርካታ ምክንያቶች ትልቁን ሚና እንደሚወስድ ይናገራሉ።
«አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በአንድ ስፍራ የሚኖር አይደለም፤ ይኽ ማለት በእያንዳንዷ ቀን ከፍተኛ የሆነ ግጦሽ በየቦታው ይኖራል ማለት ነው። ይኽም በባሪንጎ ሐይቅ አካባቢና ከላይ በተራራው ላይ ሁሉ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል። በቋሚነትም ውኃ እና ነፋስ አፈሩን ያጥባል፣ በ2018 የነበረው ዝናብ በ1998 ከነበረው ከባድ የዝናብ ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፤ ባለፈው ዓመት ደግሞ ባልተለመደ መልኩ እጅግ ከባድ ዝናብ ዓመቱን ሙሉ ጥሏል። ይኽ ማለት የአካባቢ ተፈጥሮ መራቆት፣ ከፍተኛ የሆነ ፍሰት፤ እንዲሁም የውኃው ጨዋማነትን አንድ ላይ ሆነው ነው በዚህ በስምጥ ሸለቆ ብቻ ሳይሆን በሌላም ስፍራ እንደ አምባሳሌ ያለው ማለት ነው የውኃው ከፍታ 10 እና 15 ሜትር እንዲጨምር ያደረጉት ባይ ነኝ።»
ሄነሪ ሌፓሪዮ በአካባቢው የእርሻ ቦታ የነበረው አርሶ አደር ነው። አሁን የእርሻ ማሳው በውኃ ተውጧል።
«በእውነቱ ለበርካታ ጊዜያት ችግሮች እየገጠሙን ነበር፤ እንዲህ ያለው የመሬት ችግርም ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ነው፤ ይኽ ውኃ ከዚህ በሰባት ሜትር ርቀት ላይ ጀምሮ ነው አካባቢውን ያጥለቀለቀው በርካታ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።»
አርሶ አደሩ ሌፓሪዮ እንደሚለው ውኃው በፊት ከእርሻው 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። አሁን ግን የእርሻ ቦታውን ሸፍኖበታል፤ እሱ በሚኖርበት አካባቢ የነበረው ትምህርት ቤትም አሁን በውኃው ተወርሷል፤ ውኃው አካባቢው ላይ ይዞታውን በማስፋፋቱ ወደ አራት ሺህ ሕዝብ ከዚህ ስፍራ ለመልቀቅ መገደዱንም ይናገራል። በውኃው ከተዋጠው እርሻው ለኑሮው መደጎሚያ ከዘራው በቆሎ የተወሰነውን ምርት እስከ ጉልበቱ በውኃው ውስጥ ገብቶ መሰብሰብ መቻሉንም ነው የተናገረው።
ሄነሪ ሌፓሪዮ እንደሚለው መጀመሪያ ከብቶች ነበር የሚያረባው፤ ከቦታ ቦታ ለግጦሽ መዟዟሩ፣ በግጦሽ ቦታ ግጭቱ እና ተያያዥ ችግሮች ሲከብዱት፤ እህል ወደ መዝራት ፊቱን አዞረ። ለተወሰኑ ዓመታት ኑሮውን በዚህ ሲደጉም ቢቆይም በኬንያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ የውኃ አካላት መጠናቸው እየጨመረ መምጣት የእርሻ ማሳውን በውኃ አልብሶ ኑሮውን ሲፈታተነው ፊቱን ወደ ዓሣ አጥማጅነት ለማዞር ዳርዳር እያለ ነው።
«አየሽ እንደ ማኅበረሰብ አርብቶ አደሮች ነበርን፤ አሁን ግን እንደምታይው እዚህ ሐይቅ ውስጥ በርካታ ዓሣዎች አሉ፤ በዚያም ላይ ሌሎች እንደ ጉማኤ፣ አዞ እና የመሳሰሉ እንሳስትም አሉ። አሁን በድርቁ ምክንያት ሰዎች ለብዙ ችግር ተዳርገዋል። ምግብ የላቸውም፤ መጠለያ የላቸውም፤ አሁን እዚህ ልናገኝ የምንችለው እነዚህን ዓሣዎች ብቻ ነው። እናም ሰዎች ዓሣ ለማስገር ይሞክራሉ፤ ግን ሁሉም አይደሉም ምንም እንኳን ዓሣ ማስገር ባንፈልግም በችግር ምክንያት የተወሰኑት ናቸው ይኽን የሚሠሩት።»
እንዲህ ላለው ችግር የተዳረገው እሱ ብቻም አይደለም፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዚህ ስፍራ ነዋሪዎችም በአየር ንብረት ለውጥ መዘዘዝ የኑሮ መሠረታቸው ተናግቷል።
ኬንያ የአየር ንብረት ለውጡን ተጽዕኖ በተግባር እየኖሩት ካሉ ሃገራት አንዷ መሆኗን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምታስተናግደው የተፈጥሮ ቁጣ እንደ ዋነኛ ማሳያ ይጠቀሳል። የሙቀቱ መጨመር በኬንያ ስምጥ ሸለቆ የሚገኙ ሐይቆችን ከፍታ መጨመሩ በአንድ ወገን ሲነገር በሌላ ወገን ደግሞ የድርቀቱ መባባስ አርብቶ አደሮች አማራች የኑሮ ስልት እንዲፈልጉ አስገድዷል። ከስምጥ ሸለቆ በስደቡብ ናሮክ በተባለው የኬንያ ግዛት የሚኖረው የማሳይ ማኅበረሰብ በአርብቶ አደርነቱ ይታወቃል። የድርቁ መራዘም አርብቶ አደሮቹ ላይ ያስከተለውን ቀውስ ያስተዋለችው ወጣቷ ሳሊና እንኮይሌ ወገኖቿ የአየር ንብረት ለውጥ ላስከተለባቸው ችግር መፍትሄ የሚገኙበትን መንገድ ለማሳየት በመሥራት ላይ ናት።
«የአየር ንብረት ለውጥ ከበፊቱ የረዘመ የድርቅ ወራት እንዲመጣ እያደረገ ነው። አሁን ጭራሽ ዝናብም ሆነ የአየር ጠባዩን መገመት አዳጋች ሆኗል። የግጦሽ መሬት እያነሰ በመሄድ ላይ ነው፤ ይኽ ደግሞ ማሳዮች የከብቶቻቸውን ቁጥር እንዲቀንሱ እያደረጋቸው ነው። እናም የአየር ንብረት ለውጥ ማሳዮችን ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚኖሩ ከብት አርቢዎች ሳይሆን ሌላ የኑሮ መንገድ እና የገቢ ምንጭ እንዲፈልጉ እያስገደዳቸው ነው።»
ወትሮ ከብቶችን በማርባር ኑሯቸውን ይደጉሙ የነበሩት ለእነዚህ ወገኖች ያገኙት የኑሮ አማራጭ ዘላቂነት ባለው መንግድ የሚበሉትን ለማምረት መሥራት ነው። ይኽ የኑሮ ስልት ለእነሱ እንግዳ ቢሆንም ለመኖር ግን የግድ ከለውጡ ጋር መላመድ ይኖርባቸዋል።
«እንደ ማሳይ ማኅበረሰብ አማራጭ የኑሮ ስልት እንዲሁም ምግብ እና የተመጣጠነ አመጋገብ መፈለግ እንደሚኖርብን አስባለሁ። እናም ለምን ዝም ብለን ከብቶችን ብቻ ከምናረባ እህል ማምረት አንጀምርም በሚል አሰብኩ። ስለዚህ የምንመገበውን አይነት ምንጩን ማብዛት እንዳለብን በመወሰን፤ በዚህም የምግብ አማራጭን ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጭ አማራጭም እንዲኖረን ለማድረግ ነው የምንሠራው። ምክንያቱን እህልን በየትኛውም ጊዜ ዘርቶ ማምረት ይቻላል።»
ሸዋዬ ለገሠ/ ኢዲዝ ኪማኒ
ማንተጋፍቶት ስለሺ