የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኦሮሚያ አጀንዳን አሰባሰብ ማጠናቀቁ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16 2017በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች ወደ ምክክር እንዲመጡ ለማድረግ ያለውን ተደጋጋሚ ዝግጅት ተከትሎ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር በቅርቡ የሰላም ስምምነት ላይ የደረሱት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች በመድረኩ ተሳትፎ ማድረጋቸው በቀላሉ የማይታይ ስኬት ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዚህ መድረክ 10 የተለያዩ የኅብረተሰብ መሠረቶችን የወከሉ 7,000 ተሳታፊዎች ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል ያሉዋቸውን በርካታ ነጥቦች አንስተዋል ነው ያለው። የመጀመሪያ ግብ የሆነው አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ የክልሉን አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር አጥጋቢ በሆነ መልኩ መከናወኑን አመልክቷል።
የተሳትፎ ጉዳይ
የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በምክክር መድረኩ የመዝጊያ ስነስርኣት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ «ኮሚሽኑ በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሥራውን ሲጀምር ሊያሳካቸው ያቀዳቸው ሦስት አበይት ግቦች ነበሩት። የመጀመሪያው አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ አጀንዳ ማሰባሰብ ነው። ከዚህ አኳያ 10 ተለያየ የኅብረተሰብ መሠረቶችን የወከሉ ከ7,000 የሚልቁ ወገኖች እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል። በአራት ሰፋፊ ክላስተሮች የተካሄደው ምክክሩ 640 የምክክር ቡድኖች ተዋቅረው ነጻና ግልጽ ምክክር አድርገዋል» ብለዋል። ፕሮፈሰር መስፍን «በመጨረሻም በየቡድኑ ያሉት አጀንዳዎች ተጠናቅረው የክልሉን አጀንዳዎች ኮሚሽኑ ተረክቧል» ነው ያሉት።
የኮሚሽኑ ሁለተኛ ግብ የሆነውም በቀጣይ ለሚካሄደው ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን ግልጽና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማስመረጥ ነው ያሉት ፕሮፈሰር መስፍን ዓርዓያ በኮሚሽኑ አሰራር መሠረት 320 የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ 12 የሃሳብ መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ተወካዮች፣ 31 የመንግሥት አካላት ተወካዮች እና ሌሎችም መመረጣቸውን ገልጸዋል።
በሦስተኛ ግብነት የተያዘው የተደረሰውን ምክክር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው ያለው ኮሚሽኑ ይህም በስኬት መጠናቀቁን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ላይ የተነሳው የገለልተኝነት ጥያቄና እልባቱ
በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለውን ብሔራዊ ምክክርበአሳታፊነቱና ገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ በማንሳት በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ እንደ ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሂደቱም ቢያንስ እስካሁን ተሳታፊ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በትናንት ንግግራቸው ይህን አስመልክተው፤ «አሁን ያልወከሉ እንደ የሃይማኖትና ፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ተቋማት በኮሚሽኑ አሰራር መሠረት በቀጣይ በተቋማቸው በኩል እንዲያሳውቁ ይጠበቃል» ነው ያሉት።
ተሳታፊዎች ያነሱዋቸው አጀንዳዎች
ተሳታፊዎችም ከሳምንት በላይ ቆይተው የመከሩባቸው የክልሉ አበይት አጀንዳዎች ያሏቸውን ሲያነሱ «የአዲስ አበባ አስተዳደር ወሰን እና ሀረር ብሎም የድሬዳዋ ጉዳዮች እንዲመከርባቸውና እንዲሻሻል ይቀናል። አዲስ አበባ ከስሟ ጀምሮ ፊንፊኔ እንድትባልና ተጠሪነቷም ለኦሮሚያ ክልል እንዲሆን ሃሳብ አቅርበናል። አፋን ኦሮሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፌዴራል ቋንቋ እንዲሆንም እንዲመከርበት ብለናል። የኦሮሚያ አስተዳደር ወሰንም ተከብሮ ተከባብረን እንኑር ብለን ጠይቀናል» ብለዋል።
ሌላው ሃሳባቸውን ያጋሩን የአካል ጉዳተኞችን ወክለው በምክክሩ የተሳተፉ በበኩላቸው፤ «አካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ውስጥና በተለያዩ ተሳትፎዎች የሚኖራቸው ቦታ መሻሻል ይገባዋል በሚል ሃሳብ አንስተናል። ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ እና አካል ጉዳተኞችን የሚጠብቅ የሕግ ከለላ መጠናከር እንዳለበትም እንዲመከርበት ጠይቀናል» ነው ያሉት።
የተደረገው ምክክር ውጤታማ ነበር ያለው ኮሚሽኑ ሴቶችን 30 በመቶ ማሳተፍ መቻሉንና አካል ጉዳተኞችም መሳተፋቸውን አመልክቷል። ኮሚሽኑ በተለያዩ መንገዶች የሚያሰባስባቸውን አጀንዳዎች እንደ አገር ላሉ ልዩነቶች መንስኤ የሆነውን በአገራዊ ምክክር መግባባት ላይ እንዲደረስባቸው እንደሚያደርግ አሳውቋል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ