የአፋርና ሶማሌ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የሰላም ችግር
ረቡዕ፣ ጥቅምት 5 2012ለወራት መልኩን እየቀያየረ ዛሬ ላይ በደረሰው የአፋር እና ሶማሌ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ግጭት በርካታ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ ፣ በርካቶች ቆስለዋል ፤ ሀብት ንብረትም ወድሟል ፡፡በሁለቱ ክልሎች ሲካሄድ ነበር የተባለ የሰላም ጥረትን ጨምሮ የፌደራል መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ያላበጀለት የአካባቢው ግጭት ሰሞኑን በአፋር ክልል በታጣቂዎች ተፈፅሟል የተባለ ጥቃት አስራ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ውጥረቱን አባብሶታል ፡፡ በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዑመር አብዲ ለDW እንደገለፁት ከተጀመረ አስራ አንድ ወራት ላስቆጠረው የሁለቱ ክልል አርብቶ አደር መኖርያ አካባቢዎች ግጭት ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው ፡፡አንደኛው ህዝብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ያነሳው የማንነት ጥያቄ በአፋር ክልል በኩል መልስ አለማጝኘቱ ነው ፡፡ዋና አስተዳዳሪው እንደሚሉት ሁለተኛው ምክንያት ግን "ለውጡ ያልተዋጠላቸው ፣ ቀደም ሲል የሶማሌ ክልልን ሀብት የጨረሱ ዛሬ ሰመራ የተቀመጡ የጦር ጀነራሎች እጅ መኖሩ ነው" እንዱፎ በተባለው ቀበሌ የተነሳው ግጭት ወደ አዴይቲ እና አፍደም አካባቢዎች እንዲዛመት ተደርጓል ያሉት ግጭት ከዚያ በኃላ በአፋር ልዩ ኃይል እና በሌሎች ኃይሎች ታግዞ እስካሁን ድረስ በሶማሌ ክልል ይዞታ ወረራ እያካሄደ ነው ብለዋል ፡፡የዞን አስተዳዳደሪው እንደሚሉት እስካሁን አስራ አንድ ወራት አስቆጥሯል ባሉት ግጭት ከሶማሌ ማህበረሰብ ወገን ሁለት መቶ ሰባ ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች በርካታ ጉዳቶች ደርሷል ፡፡አቶ ዑመር ሰሞኑን በአፋር ክልል ታጣቂዎች አድርሰውታል በተባለ ጥቃት ሳቢያ ሰዎች በመሞታቸው እና በመጎዳታቸው ሶማሌ የሆኑ ከጂቡቲ የመጡ አካላት ጥቃቱን ፈፀመዋል በሚል በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨውን መረጃ አውግዘዋል ፡፡የሰላም ሚንስትርን ጨምሮ የፌደራል መንግስቱ ያውቀዋል ባሉት የአካበቢው የሰላም ችግር መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አስካሁን ችግሩ እንዳይፈታ ይፈልጋሉ ባሏቸው አካለት ተሳትፎ መፍትሄ አላገኘም ፡፡ለሰላማዊ መፍትሄ አሁንም በሩ ክፍተ ነው ያሉት የሶማሌ ክልሉ መስተዳድር እልባት ባልተበጀለት ችግር ሳቢያ በክልሉ ህዝብ ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆም መወሰኑን ተናግረዋል ፡፡በአካባቢው ግጭት እጃቸው አለበት ያሏቸው የተቃዋሚ ኃይሎችን በሚመለከት ያላቸውን መረጃ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ዑመር በተለያየ መልኩ መረጋገጡን ተናግረዋል ፡፡
መሳይ ተክሉ
ኂሩት መለሰ
መሳይ ተክሉ