1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጸረ-አሸባብ አዲስ ዘመቻ

ሰኞ፣ ሐምሌ 13 2007

በሶማልያ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአሸባብ ታጣቂ ቡድን ላይ አዲስ የጥቃት ዘመቻ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። የጁባ መተላለፊያ ተልዕኮ የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘመቻ በሶማልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊ ይፋ የተደረገው ባለፈው አርብ ቢሆንም ገና ካሁኑ ከአሸባብ ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ ጥቃት እየገጠመው ነው።

https://p.dw.com/p/1G1o3
Somalia Armee Soldat Somali Armed Forces SAF
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

[No title]

የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች ከአሸባብ ተከታታይ የሰርጎ ገብ ጥቃቶች በኋላ አዲስ የጥቃት ዘመቻ መክፈቱን አስታወቀ። የአሸባብ ታጣቂ ቡድኑ ትናንት በአህጉራዊው የሰላም አስከባሪ ሃይል ላይ በፈጸመው ጥቃት አስራ ሁለት ወታደሮች መገደላቸውን የጀርመን ዜና ወኪል ወታደራዊ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል። ማናስ በተባለ አካባቢ ቦምብ በተጫነ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የብሩንዲ ወታደሮች መሞታቸውን በሶማሊያ የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ ሞሀመድ ኦማር ሁሴን ተናግሯል።

«በመኪና የተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የተፈጸመው ከሞቅዲሹ በስተምዕራብ 140 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኝ ሌጎ የተባለ ቦታ ላይ ነው። በጥቃቱ 16 የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪዎች በተለይም የብሩንዲ ወታደሮች ተገድለዋል። ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ቦታ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይም ጥቃት ተፈጽሞ ነበር። በዚህ ጥቃት የአሸባብ ታጣቂዎች የኢትዮጵያ ወታደሮችን መኪና ከመማረካቸውም ባሻገር ጥቂት ወታደሮች ገድለዋል።ቢሆንም ከብሩንዲ ወታደሮች በተሻለ የኢትዮጵያ ወታደሮች ራሳቸውን መከላከል ችለዋል።»

Al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab

የጀርመን ዜና አገልግሎት በአሸባብ ጥቃት 20 የሶማልያ መንግስትና በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ስር የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን የሰርጎገቦቹ ደጋፊ የሚባለውን አናዱሉስ ራዲዮ ጠቅሶ ዘግቧል። በተኩስ ልውውጡ 10 የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ አባላት ተገድለዋልም ተብሏል።

የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በአሸባብ ላይ አዲስ የጥቃት ዘመቻ መክፈቱን አስታውቋል። የዚህ እቅድ አካል ይሁን አይሁን ባይታወቅም ከ3000 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች የአሸባብ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነ ወደሚነገርለት የባርድሬ ከተማ ተጉዘዋል ተብሏል።

በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ስር ወታደሮቿን ያሰማራችው ኡጋንዳም ተዋጊና የትራንስፖርት ሄሊኮፕተሮችን ወደ ሶማልያ ልትልክ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬዝ ዘግቧል። የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ፓንዲ አኩንዳ ሄሊኮፕተሮቹ ከአሸባብ ጋር የሚካሄደውን ውጊያ እንደሚያጠናክሩት ተናግረዋል።

የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር የጁባ መተላለፊያ ተልዕኮ(Operation Jubba Corridor) ሲል የሰየመው አዲስ የጦር ጥቃት አሸባብን ከሶማሊያ ገጠራማ አካባቢዎች ጠራርጎ ለማስወጣት የታቀደ ነው ተብሏል። ከሶማልያ ዋና ከተማ ሞቅዲሹ በስተደቡብ የሚገኙ የቤይና ጌዶ ግዛቶችን ነጻ ለማውጣት ያለመውን ይህን ዘመቻ የሶማሊያ መንግስት ወታደሮችም ይቀላቀሉታል የሚለው ሞሀመድ ኦማር ሁሴን ተልዕኮው በሃገሪቱ መንግስት ተስፋ ተጥሎበታ ይላል።

«ይህ በቅርብ የሚጀምር ተልዕኮ ነው። የሶማሊያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊ በይፋ መጀመሩን ያበሰሩ ሲሆን አሸባብን ለመግታትና አሁን ካለበት ቦታም ለማጥፋት የታለመ እንደሆነም ተናግረዋል።»

አሁን የተጀመረው አዲስ ተልዕኮ የአሜሪካ ሰው ሰው አልባ አውሮፕላኖች በፈጸሙት የአየር ድብደባ 30 የአሸባብ ታጣቂዎችና መሪዎች መገደላቸው በተሰማ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጣ ነው። ሞቅዲሹ የሚገኘው የዶይቼ ቨሌ ተባባሪ ዘጋቢ ሞሀመድ ኦማር ሁሴን በሶማልያ ዜጎች ላይ በሚፈጽማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተቀባይነት በማጣቱ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ አዲስ ተልዕኮ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግሯል። ተደጋጋሚ የአጥፍቶ መጥፋትና የሰርጎ ገብ ጥቃቶች የሚፈጽመውን አልሸባብን ደግሞ ለሞት ከቀረበ ፈረስ ጋር አመሳስሎታል።

Somalia Soldaten
ምስል dapd

«አሸባብ በመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ማለት ይቻላል። አሁን የሚያደርጋቸውን ድርጊቶች የሚሞት ፈረስ የመጨረሻ እርግጫ ልንለው እንችላለን። አሸባብ በሶማልያ በርካታ ቁልፍ ቦታዎች አጥቷል። በቅርብ ጊዜም ከሌሎች አካባቢዎች ይጠፋል ብዬ አስባለሁ።»

ከአልቃዒዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባልለት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን በሶማልያ መንግስት ጦርና የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ከምድር በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ደግሞ ከሰማይ ተደጋጋሚ ጥቃት ተወስዶበት ሊጠፋ ደረሰ ቢባልም አሁንም በቀጣናው የደህንነት ስጋት ከመሆን አልዳነም። ታጣቂ ቡድኑ እስካሁን ለአልቃዒዳ የነበረውን ታማኝነት በመተው ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ለመወዳጀት ቆርጧል የሚል ጭምጭምታም ተሰምቷል። በእስልምና ተከታዮች የቅዱስ ረመዳን የጾም ወር መጠናቀቂያ የታጣቂ ቡድኑ መሪ አህመድ ዲርዬ ከሶማልያ ውጪ በኬንያና ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛቱ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሠ