የአፍሪቃ ህብረት
ሰኞ፣ ሐምሌ 11 2008
በርዋንዳ መዲና ኪጋሊ የተካሄደው 27ኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ተተኪ ለመምረጥ ያደረገው ጥረቱ ሳይሳካ መቅረቱን አንድ የኅብረቱ ባለስልጣን አስታወቁ። ስልጣናቸውን መልቀቅ የነበረባቸውን የወቅቱ የኮሚሽኑ ፕሬዚደንት ድላሚኒ ዙማን ለመተካት በእጩነት የቀረቡት የቦትስዋና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔሎኖሚ ቬንሶን ሞይቶይ፣ የኢኳቶርያል ጊኒ አቻቸው አጋፒቶ ምባ ሞኩይ እና የዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚደንት ስፔስዮዛ ካዚብዌ ፣ አንዳቸውም በኅቡዕ በተካሄደው የምርጫ ሂደት ላይ አስፈላጊውን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ባለማግኘታቸው ምርጫ የፊታችን ጥር ወር ለሚካሄደው ለቀጣዩ ጉባዔ መተላለፉን የድላሚኒ ዙማ ቃል አቀባይ ጄኮብ ኤኖህ ኤብን አስረድተዋል።
አንዳንድ የኅብረቱ ባለስልጣናት ብዙም በማይታወቁት በሦስቱ እጩዎች ፈንታ የአልጀርያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና የቀድሞው የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ ራምታን ላማምራ በእጩነት እንዲወዳደሩ ሀሳብ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል። ይሁንና፣ አልጀሪያዊው እዝማየል ቸርግዊ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ ሆነው ስለሚመረጡ ሁለት አልጀሪያውያን የኅብረቱን ሁለት ከፍተኛ ስልጣን የሚይዙበት አሰራር በአባል ሃገራት ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ አልሆነም። ከላማምራ ጎን ሌሎች የቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ እና የተመድ ልዩ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ልዑክ አብዱላይ ባቲሊም በእጩነት እንዲቀርቡ ሀሳብ ሰንዝረዋል።
በተያያዘ ዜና፣ ሞሮኮ ከ32 ዓመታት በኋላ የአፍሪቃ ኅብረትን እንደገና በአባልነት ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላት የሞሮኮ ንጉሥ መሀመድ ሳድሳይ አስታውቀዋል። ሞሮኮ እጎአ በ1984 ዓም የኅብረቱን አባልነትዋን የተወችው ኅብረቱ ሞሮኮ በ1975 ዓም በኃይል ከግዛቷ የጠቀለለቻትን ምዕራባዊ ሰሀራን እንደ ሀገር በአባልነት በመቀበሉ ነበር። ንጉሥ መሀመድ ሳድሳይ ለመሪዎቹ ጉባዔ በላኩት መልዕክት ፣ የምዕራባዊ ሰሀራ ጥያቄ በተመድ ሸምጋይነት መፍትሔ እየተፈለገለት በመሆኑ ኅብረቱ ይህን አቋሙን መልሶ እንዲያስብበት ጠይቀዋል።
አርያም ተክሌ
ሸዋዬ ለገሠ