የአፍሪቃ ኅብረት የተሃድሶ ጥያቄ
ረቡዕ፣ ጥር 24 2009ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም በእንግሊዝኛ ምህፃሩ ISS አማካሪ ሌዝል ሎ ቮልድሪን በተደጋጋሚ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤዎች ላይ ተገኝተዋል። የዘንድሮዉንና ለ28ኛ ጊዜ የተካሄደዉን የኅብረቱን ጉባኤም በአካል ተገኝተዉ ለመታዘብ ችለዋል። በየዓመቱ ኅብረቱ ትላልቅ ተግዳሮቶች ያጋጥሙታል። በተለይም ዉሳኔዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ አቅም እንደሌለዉ ተቺዎቹ ይናገራሉ። ሌዝል ሎ ቮልድሪን ትችቱ ሚዛናዊ እንደሆነ ነዉ የሚገልፁት። በእሳቸዉ ምዘናም የአፍሪቃ ኅብረት ብቃት የሚጎድለዉ፤ ለማስተዳደር የሚያዳግት እና ከፍተኛ ወጪ የሚያጠይቅ ነዉ። እንዲህ ይበሉ እንጂ ለ33 ዓመታት ከኅብረቱ ርቃ የኖረችዉ ሞሮኮን ዳግም በአባልነት የመቀበል ርምጃዉን አዎንታዊ ሲሉ፤ የሞሮኮ ወደ ኅብረቱ የመመለስ ዉሳኔም ተፈላጊነቱን እንደሚያጎላ ነዉ የገለፁት።
«ሞሮኮዎች ወደ አፍሪቃ ኅብረት ዳግም ለመመለስ ከፍተኛ ዘመቻ አካሂደዋል። እናም ይህ ኅብረቱ ከድሮዉ ይልቅ አሁን ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ያመለክታል። ምክንያቱም ሞሮኮዎች ዉሳኔዉ አዲስ አበባ ላይ እንደሚሰጥ፤ የዚህ አካል ካልሆኑም ሊወጡ እንደሚችሉ ያምናሉ። ለነገሩ ሞሮኮን ዳግም ከመቀበሉ አስቀድሞ የምዕራብ ሰሃራ ሉዓላዊነትና ነፃነት ዋስትና ማግኘት ይኖርበታል በሚል ከፍተኛ ክርክር ያነሱ ነበሩ። አብዛኞቹ ግን መመለሷን ደግፈዋል። አሁን ያለዉ ሃሳብ ሞሮኮ ወደ ኅብረቱ ተመልሳለች፣ ምዕራብ ሰሃራም አባል በመሆኗ የሁለቱ ጉዳይ ከዉጭ ይልቅ በድርጅቱ ዉስጥ መፍትሄ እንዲፈለግለት የሚል ነዉ።»
ለምዕራብ ሰሃራ ነፃነት የሚታገለዉ ግንባር የፖሊሳሪዮ ወኪል መሐመድ ኤል ማሙን አህመድ ብራሂሚም ሞሮኮ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ኅብረቱ አባልነት መመለሷን ይደግፋሉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1984ዓ,ም ነዉ ሞሮኮ ከቀድሞዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አባልነቷ የወጣችዉ። ድርጅቱ ያኔ ምዕራብ ሰሃራን በአባልነት ተቀበለ። ሆኖም ሞሮኮ አካባቢዉን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ እንደራሷ ግዛት ይዛዉ ቆይታለች። አህመድ ብራሂሚ የአሁኑ አጋጣሚ ሁለቱንም ወገኖች እኩል በሉዓላዊነት ማሸማገል ያስችላል ይላሉ።
«የፖሊሳሪዮ አቋም የሚከተለዉ ነዉ፤ ሞሮኮ ወደ አፍሪቃ ኅብረት አባልነት መመለሷን በደስታ እንቀበላለን። ሞሮኮ ምንም ቅድመ ሁኔታ አላስቀመጠችም። አጋጣሚዉ ሞሮኮ ጉዳዩን በአፍሪቃ ኅብረት ዉስጥ የማንሳት ዕድልን ይሰጣል ብለን እናምናለን። አሁን በተመሳሳይ ደረጃ በአፍሪቃ ቤተሰቦቻችን መካከል እንደራደራለን።»
ኅብረቱን በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን ትናንት ጉባኤዉን ካጠናቀቀዉ የአፍሪቃ ኅብረት አስደናቂ እና ድንገተኛ ርምጃ ጠብቀዋል። ከዚህ መካከልም ሌዝል ሎ ቮልድሪን እንደሚሉት ቀጣዩን የኅብረቱን ኮሚሽነር የመምረጡ ዉሳኔ አንዱ ነበር። ኬንያዊቱን ተፎካካሪያቸዉን አሚና መሀመድን ከሰባት ዙር የድምጽ አሰጣጥ በኋላ ያሸነፉት የ56 ዓመቱ የቻድ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳ ፋኪ መሐመት የአፍሪቃ ኅብረትን ዉስጥ በቅርብ ከሚያዉቁ አንዱ መሆናቸዉን ቮልድሪን ይናገራሉ።
«ከቻድ የመጡት አዲሱ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ሙሳ ፋኪ መሐመት በድርጅቱ ዉስጥ በርከት ያለ ልምድ ያላቸዉ ሰዉ ናቸዉ። ባለፈዉ ዓመት የኅብረቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን በሊቀመንበርነት መርተዋል፤ ምክንያቱም ቻድ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ነበረች። በዚያም ላይ በኅብረቱ የተለያዩ ተቋማት ዉስጥም አገልግለዋል። ስለዚህ ተቋሙን ያዉቁታል፤ ከዉጪ የመጡ ሰዉ አይደሉም።»
ቻድን በጠንካራ እጃቸዉ ለ27 ዓመታት የገዙት የፕሬዝደንት ኢድሪስ ዲቤ ቀኝ እጅ ፋኪ መሐመት ኅብረቱ ለረዥም ዓመታት የጠበቀዉን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ መሥራታቸዉ አይቀርም። ፋኪ መሐመት በሩዋንዳዉ የፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ኮሚሽን ያቀረበዉን ኅብረቱን በሙሉ ኃይሉ የማንቀሳቀስ ምክረ ሃሳብ ይደግፋሉ።
ባለፈዉ ዓመት የኅብረቱ ጉባኤ ላይ ፕሬዝደንት ካጋሜ ተጨባጭ የተሀድሶ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል። በኮሚሽኑ ካሰባሰቧቸዉ ምሁራን መካከል የቀድሞዉ የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶናልድ ካቤሩካ እንዲሁም የተመድ ዲፕሎማት ካርሎስ ሎፔዝ ይገኙበታል። በእርግጥ ይህ ለዚሁ ጉዳይ የተቋቋመ የመጀመሪያ ኮሚሽን አይደለም። የዛሬ 10 ዓመትም የኅብረቱ ጉባኤ ናይጀሪያዊዉ ፕሮፌሰር አደባዬ አዴዴጄ ተመሳሳይ የማሻሻያ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ሰጥቶ ነበር። የእሳቸዉ ቡድንም 172 ነጥቦችን ያካተተ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል። ችግሩን ግን የተለወጠ ነገር አለመኖሩ ነዉ። አሁንም ዋናዉ ነገር ይላሉ ሌዝል ሎ ቮልድሪን በአፋጣኝ ለኅብረቱ የእዉነት አቅም መፍጠር ነዉ።
«ዋናዉ አጣዳፊ ነገር ለምሳሌ ምርጫዎች በተሳሳተ አቅጣጫ ሲሄዱ ወይም ተቃዋሚዎችን ለማገድ ብላ አንድ ሀገር የኢንተርኔት አገልግሎትን ስታቋርጥ የአፍሪቃ ኅብረት ጣልቃ መግባት እንዲችል እዉነተኛ ኃይል እንዲኖረዉ ማስቻል ነዉ።»
ሸዋዬ ለገሠ/ አንቶኒዮ ካሽካሽ
ነጋሽ መሐመድ