የአፍሪቃ ፖለቲካና ፈረንሳይ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 10 200318 04 11
ባለፈዉ ጥር ኒዠር ዉስጥ ላጭር ጊዜ ተዋግታ ነበር።በዚያዉ ወር የቱኒዚያን ሕዝባዊ አመፅ ለመደፍለቅ ይዉተረተር የነበረዉን የቤን ዓሊን ጦር ለማስታጠቅ ቃል ገብታ ነበር።ፈረንሳይ።ለሊቢያ ተቃዋሚዎች የመንግሥትነት እዉቅና ለመስጠት፥ሊቢያን ለመደብደብም የቀደማት የለም።የኮትዲቯሩን የቀድሞ ፕሬዝዳት ከመሸጉበት መዝቆ ያወጣዉ የፈረንሳይ ጦር ነዉ።ሮናልድ ማርሻልም ፈረንሳዊ ናቸዉ።የአፍሪቃ ፖለቲካዊ ጉዳይ ፕሮፌሰር።እናንት ፈረንሳዮች ዳግም አፍሪቃ መግባታችሁ ነዉ።ጠየኳቸዉ።እሳቸዉም ጠየቁ።«የጦር አዉሮፕላኖቻችንን ማለትሕ ነዉ? ታኮቻችሁም ጭምር» ፕሮፌሰር ማርሻል እንግዳችን።የአፍሪቃ እዉነታ፥ የፈረንሳይ ጥድፊያና ምክንያት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
የፈረንሳይ ቅኝ ገዢ ጦር ከ1954 እስከ 1962 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከአልጄሪያ የነፃነት ተፋላሚዎች ጋር የገጠመዉ ዉስብስብ፥ እልሕ አስጨራሽ ጦርነት ፍፃሜ-ለአልጄሪያዊ የነፃት ብሥራት የመሆኑን ያክል ለሐያሊቱ ሐገር የሽንፈት፥ዉድቀት-መርዶ ነበር።
ያ ጦርነት በርግጥ ዘግናኝ ነበር።ሚሊዮኖችን አርግፏል።ሁለቱንም ወገን አሸብሯል።አራተኛዉ ሪፐብሊክ የተሰኘዉን የፈረንሳይ መስተዳድርን ከሥልጣን አስወግዷል።እዉቁን ጄኔራል ሻርልስ ደጎልን ዳግም ወደ ሥልጣን አዉጥቷል።ደጎል ሰኔ 1958 አል-ጄሪያን ሲገበኙ ተፋላሚዎቹን «ተረድቼያችኋለሁ» ማለታቸዉ ለሁለቱም ሐይላት የአስተዋይ መሪ መልዕክት ሐያሊቱ ሐገር ሥለ አፍሪቃ ቅኝ ተገዢዎችዋ ለምትከተለዉ መርሕ ዘላቂ አስተምሕሮት መስሎ ነበር።
ከመምሰል ግን አላለፈም።አልጄሪያ ነፃነትዋን ከማወጅዋ ጥቂት ቀደም ብሎ ጋቦንን እንደ ነፃ ሐገር ከፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች የተረከቡት ፕሬዝዳንት ሌዮን ምባ በ1964 የሐገሪቱን ምክር ቤት አግደዉ ሥልጣኑን በሙሉ ጠቀለሉ።ምባ እርምጃዉን የወሰዱት በፓሪሶች ምክርና ይሁንታ መሆኑን ተቃዋሚዎቻቸዉ የሚያዉቁ፥ የሚያስተነትኑበት አቅም፥ብልጠት፥ ብልሐትም አልነበራቸዉም።
ከሩቋ ሐያል ሐገር ሴራ ይልቅ የቅርቡን ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት መሥረት ያደረጉት ተቃዋሚዎች የምባ የጀመሩትን የአምባገናናዊ የፈላጭ ቆራጭ ጉዞ ለማገድ ፕሬዝዳንቱን በመፈንቅለ መንግሥት አስወገዱ።ፈረንሳይ ሐያ-አራት ሰአት አልጠበቀችም።ልዩ ጦሯን አዝምታ የምባን ተቃዋሚዎች አስደምስሳ-ታማኝ አገልጋይዋን መልሳ ከመንበራቸዉ አስቀመጠች።
እስከ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ድረስ ከሰሜን ጫፍ ቱኒስ፥ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ጥግ ኪንሻሳ፥ ከአፍሪቃ ቀንድ ጠርዝ ጅቡቲ፥ እስከ ምዕራብ አፍሪቃ ጥግ ያምሱኩሩ፥ የአፍሪቃ ፖለቲካ የሚዘወረዉ በፓሪስ ይሁንታና ፍቃድ ነበር።
በ1994 የያኔዉ የሩዋንዳ ፕሬዝዳት ዦቪናል ሐብያሪማና ከብሩንዲ አቻቸዉ ጋር በአዉሮፕላን ሲጓዙ እንደተገደሉ ፈረንሳይ በቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን እንደለመደችዉ ጦሯን ለማዝመት አላመነታችም። «ዘመቻ ቱርኩዋስ» (የቀለም ሥም ነዉ) ላለችዉ ጥቃት ያዘመተችዉ ጦር የሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ ከመግታት ይልቅ ማባባሱ ትልቂቱ አዉሮጳዊት ሐገር የአልጄሪያዉን ትልቅ ጥፋትዋን ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በሕዋላም ለመደግሟ ትልቅ እማኝ ነበር።
በ2003 የዋሽንግተንና የለንደን ተጓዳኞች ኢራቅን ሲወሩ የፈረንሳይ መንግሥትና ሕዝብ እንደ አብዛኛዉ አለም ሁሉ ወረራዉን መቃወሙ ፓሪሶች በአዲሱ ዘመን አሮጌ ጥፋት ስሕተታቸዉን ለማረም የመፈለጋቸዉ ምልክት ነበር።
ግን አልቆዩም።የኢራቁን ወረራ የተቃወሙትን ፕሬዝዳት ዣክ ሲራክን በሁለት ሺሕ ሰባት የተኩት ኒካላይ ሳርኮዚ ሥልጣን በያዙ በመፈንቁ ቻድ የሰፈረ ጦራቸዉ በፕሬዝዳት የኢድሪስ ዴቢ ላይ ያመፁ ሐይላትን እንዲወጋ አዘዙ።ሁለት ሺሕ ስምንት።ዘንድሮ ጥር ኒዤር ዉስጥ የታገቱ ሁለት የፈረንሳይ ዜጎችን ለማስለቀቅ ሳርኮዚ እንደ ሌሎች የአዉሮጳና የአሜሪካ መሪዎች ተደራድሮ የታጋቾችን ይሕወት ለማትረፍ፥ ወይም አጋቾችን አዘናግቶ ለመያዝ አልፈቀዱም።
አጋች አሸባሪዎችችን ለመደምሰስ ጦር አዘመቱ።ከአጋቾቹ፥ ጥቂቱ፥ ከፈረንሳይ ጦር ጋር ከዘመቱት የኒዠር ወታደሮች የተወሰኑት፥ ታጋቾቹም ተገደሉ።በዚያዉ ወር የዓለምን ትኩረት የሳበዉ ከኒዠር በስተሰሜን የቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ቱኒዚያን ያጥለቀለቀዉ ሕዝባዊ አመፅ ነበር።ጨካኙ የቤን ዓሊ የፀጥታ ሐይል የሕዝባዊዉን አመፅ መሪ፥ አስተባባሪ፥ ግንባር ቀደም ተሳታፊዎችን በሚያስር፥በሚገርፍ፥ በሚገድልበት መሐል የሳርኮዚዋ ፈረንሳይ ለቤን ዓሊ የፀጥታ ሐይላት ተጨማሪ ትጥቅ ለመላክ ቃል ስትገባ ነበር።
ብዙዎች እንደሚሉት የቤን ዓሊ ጥፋት የቤን ዓሊ ብቻ እንዳልነበር ሁሉ ዉድቀታቸዉም የቤን ዓሊ ብቻ አልነበረም።የፈረንሳይም ጭምር እንጂ።የቱኒዚያዉ ሕዝባዊ ድል፥ ግብፅ የመደገሙ ብሥራት፥ የፓሪስና የዋሽንግተን ነባር መርሕ ዉድቀትነቱ በሚያነጋግርበት መሐል ሕዝባዊ አመፅ ሊቢያ ላይ ሲግም ሳርኮዚ እንደገና ብቅ አሉ።
«ካሁን ጀምሮ የጦር አዉሮፕላኖቻችን ቤንጋዚ በሚገኙ አማፂያን ላይ የሚፈፀመዉን ጥቃት ያስቆማሉ።ሌሎች የፈረንሳይ አዉሮፕላኖች ሠላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ ቆመዋል።»
የካቲት አስራ-ዘጠኝ።
በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ለበርካታ አመታት በአሸባሪነት፥ ወይም በአሸባሪዎች ደጋፊነት የሚወነጀሉት፥ በቦምብ ሚሳዬል ዱላ የተደደቡት፥ በማቀብ የተቀጡት ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የቆየ ቂም ቁሯሿቸዉን አስወግደዉ ከምዕራቡ ጋር መቀራረብ ሲጀምሩ ቃዛፊን ለመጋበዝ ፈረንሳይን የቀደመ አልነበረም።
ቃዛፊን ፓሪስ ድረስ የጋበዙ፥ በቀይ ምንጣፍ የተቀበሏቸዉ ፕሬዝዳት ሳርኮዚ ለጋዛፊ መንግሥት የኑክሌር ሐይል ማመንጫ ለመገንባት የአስር ቢሊዮን ዩሮ ዉል ተፈራርመዉም ነበር።ሁለት ሺሕ ሰባት።የወዳጅነቱ፥ ግብዣ፥ ዉል አራተኛ አመቱ ሲዘከር ዘንድሮ ቃዛፊን በተቀበሉበት ቤተ-መንግሥት የጋዳፊን ተቃዋሚ አማፂ መሪዎችን ልክ እንደ ቃዛፊ ሁሉ እንደ ሐገር መሪ እንደ ጥሩ ወዳጅ ተቀበሏችዉ።
የፖለቲካ መርሕ አቋሙ እንዴትነት፥ በሕዝብ ዘንድ ያለዉ ተቀባይነት እስከየትነት የማይታወቀዉን የወር እድሜ እንኳን ያላስቆጠረ አማፂ ሐይል እንደ ሐገር ተወካይ በይፋ እዉቅና በመስጠት በቅርብ ዘመኑ የአለም ታሪክ፥ አንድ አፍሪቃዊ ዲፕሎማት እንዳሉት ፈረንሳይ የመጀመሪያዋ ሳትሆን አትቀርም።
ሳርኮዚ የሊቢያ መንግሥት ሳይፈርስ ለሊቢያ አማፂያን የመንግሥትነት እዉቅና በሰጡ በሳምንቱ፥ የፈረንሳይ የጦር ጄቶች ሊቢያን እንዲደድቡ ባዘዙ በሰዓት እድሜ በሊቢያ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም አሉ።«የወደፊት እጣ ፈንታቸዉን መወሰን ያለባቸዉ ሊቢያዎች እራሳቸዉ ናቸዉ።እኛ በነሱ ጉዳይ መወሰን አንፈልግም።የነፃነቱ ዉጊያ የነሱ ነዉ።በአለም እዉቅና በራሱ ሕዝብ ላይ እንዲሕ አይነት በደል የሚፈፅምን ግን ልንቀበለዉ አንችልም።»
ፕሬዝዳንት ሳርኮዚ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን እንደ ጥሩ ወዳጅ ኤሊሴ ቤተ-መንግሥት ሲያተናግዱ፥ የአስር ቢሊዮን ዮሮ የንግድ ስምምነት ሲፈራረሙም የሊቢያ ሕዝብ በቃዛፊ አገዛዝ እንደማቀቀ ነበር።ሳርኮዚ የቃዛፊን አረመኔነት ለመገንዘብ አራባ ሁለት ዘመን፥ ይሕ ቢቀር የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ ወደ ነፍጥ ዉጊያ እስኪቀየር የጠበቁበትን ምክንያት ከሳቸዉ ወይም ካማካሪዎቻቸዉ ሌላ የሚያዉቅ በርግጥ ጥቂት ነዉ።ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት ግን የሳርኮዚ መንግሥት የቃዛፊን ሥርዓት በሐይል ለማስወገድ የተነሳዉ ለሊቢያ፥ ለፈረንሳይ ሕዝብ፥ ለአለምም ሠላም አስቦ አይደለም።
«ያሁኑ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሲበዛ ፈረንሳዊ ጠቀስ ፖለቲከኛ ናቸዉ።ይሕ ማለት እርምጃ የሚወስዱት የፈረንሳይ ሕዝብን የስሜት አቅጣጫ እየተከተሉ ነዉ።በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ካጡ ቆይቷል።እንዲያዉም በተለይ አነስተኛዉ የሕብረተሰብ ክፍል አባላት በ2012 በሚደረገዉ ምርጫ ለማሸነፍ እሳቸዉ የቀኝ ክንፉ ፓርቲ እጩ ሆነዉ ይወዳደራሉ እያሉ ነዉ።ሥለዚሕ አቅም እንዳላቸዉ።ወሳኝ መሆናቸዉንም ማሳየት ይፈልጋሉ።የፈረንሳይን ባንዲራ ከፍ አድርገዉ ማዉለብለብ እንደሚችሉ ሊያሳዩ ይፈልጋሉ።ለዚሕ ይመስለኛል አዉሮፕላኖቻችን በድብደባዉ የሚሳተፉት።»
የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ በተቀጣጠለ በሳምንት እድሜ የቃዛፊ መንግሥት ባለሥልጣናት፥ የጦር መኮንኖች፥ የጎሳና የሐይማኖት መሪዎች አመፁን መቀላቀላቸዉ የአመፁን ሕዝባዊነት ልክ፥ የጥንካሬዉን ደረጃ መስካሪ፥ የሊቢያዉያን ጉዳይ መሆኑንም የሚያረጋግጥ ነበር።
ፈረንሳዮች የመሩት ድብደባ ከተጀመረ በሕዋላ ግን ቃዛፊን በመቃወም ባንድ እያበረ የነበረዉ ሕዝብ እንዳጀማመሩ አልቀጠለም።ድብደባዉ ከተጀመረ ነገ-ወር ይደፍናል።በዉጊያ ድብደባዉ ብዙ ሰላማዊ ሰዉ አልቋል።ሌላ ቀርቶ የየሐገሩ ኑሮ፥ ፖለቲካዉ ሥርዓት አማሮት የተሰደደዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ በጣሙን አፍሪቃዊ ለዳግም ስደት ተዳርጓል።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ደግሞ ለዳግም ስዳት እንኳን ሳይበቁ ባሕር በልቷቸዋል።
ፕሮፌሰር ማርሻል እንዳሉት ሳርኮዚ የፈረንሳይን ባንዲራ ከፍ አድርገዉ ሰሜን አፍሪቃ ሰማይ ጥግ የሚያዉለበልቡት ያጡትን የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ብቻ አይደለም።ሁለተኛ ምክንያት አላቸዉ።
«ፕሬዝዳንት ሳርኮዚ ከሌሎቹ የደጎላዉያን ፖለቲከኞች በተለየ ሁኔታ ለአሜሪካ ለዩ ኤስ መንግሥት ምርጥ ተባባሪ መሆናቸዉን ለማረጋገጥ የቆረጡ ናቸዉ።በመጠኑም ቢሆን የዘመኑ ቶኒ ብሌር ናቸዉ ማለት እችላለሁ።ፈረንሳይ አሜሪካን ከምትፈልገዉ ይልቅ በተቃራኒዉ አሜሪካ ፈረንሳይን እንደምትፈልግ ለማረጋገጥ አበክረዉ እየጣሩ ነዉ።ለዚሕም ነዉ በሊቢያ ሁኔታ ዩናይትድ ስቴትስ በመጀመሪያዉ ረድፍ እንዳትታይ ለመርዳት (ሳርኮዚ) አለም አቀፉ ካርዳቸዉን የተጫወቱት።»
በ2002 ኮትዲቯርን ያደቀቀዉን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ግንባር ቀደሟ ተወናይ፥ ተፋላሚዎችን አደራዳሪ አስታራቂም ፈረንሳይ ነበረች።ድርድሩ ፕሬዝዳት ሎራ ባግቦ የፕሬዝዳትነት ሥልጣናቸዉን እንደያዙ እንዲቀጥሉ በሚፈቅድ ስምምነት እንዲያበቃ ያደረገችዉም ፈረንሳይ ነች።ስምምነቱን የሚያስከብር አለም አቀፍ ጦር እንዲዘምት አበክራ የጣረችዉም-ፈረንሳይ።
ወዲያዉ ግን ባግቦ ለፈረንሳይ ተልዕኳቸዉን የጨረሱ መሪ ሆኑ።የሰላም ዉሉ ዉጤት ለሕዳሩ ምርጫ፥ የምርጫዉ ዉጤት ዉዝግብ፥ ግጭት ሲቀሰቅስ ፈረንሳይ በሁለት ሺሕ-ሁለት እንዳደረገችዉ ድርድር አላለችም።ባግቦን በቃዎት አለች እንጂ።
«እኛ አሁን የምንመኘዉ ባግቦ ዳግም ሥልጣን ላይ እንዳይቀመጡ ነዉ።በሚቀጥሉት ቀናት ሥልጣናቸዉን የሚለቁ ከሆነ እንጠብቃለን።»
የፈረንሳዩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አላን ዡፔ።ሚዚያ ስድት።ዡፔ ያሉትን ሲሉ የባግቦን ተቀናቃኝ የአላሳኔ ዋታራን ሐይል ደግፎ የሚዋጋዉ የፈረንሳይ ጦር የባግቦን ሐይል እያሳደደ ነበር።ፕሮፌሰር ማርሻል እንደሚሉት ፈረንሳይ ድሮም ቢሆን ባግቦን ጊዜ ለመግዢያ እንጂ የዋታራን ያሕል አትፈልገዉም ነበር።ደግሞም ካለፈዉ የቀጠለ ነዉ።
«አይቮሪኮስትን በተመለከተ ያለፈዉ ቅሪት ነዉ።የግጭቱ ምክንያት ምንም ይሁን-ፕሬዝዳት ዋታራ የቅርብ ወዳጅ ናቸዉ።የቅርብ ወዳጅን ደግሞ መርዳት አለብሕ።የፈረንሳይ መንግሥት እንደሚለዉ ጣልቃ ገብነቱ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል ነዉ።በፈረንሳይ ጦር ጥቃት የተገደለዉን ሰላማዊ ሰዉ ቁጥር መጠየቅ ግን ተገቢ ጥያቄ ነዉ።ከዚሕም በላይ ሳርኮዚ አይቮሪኮስት የሚኖሩ የፈረንሳይ ዜጎችን ለማዳን የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ የፈረንሳይ ሕዝብ እንዲያቅላቸዉ ይፈልጋሉ።ወደፊት እዚያ በሚኖረዉ በፈረንሳዊና በሐገሪቱ ዜጋ መካካል የሚጎዳዉን የፈረንሳይ ዜጋ እንዴት የሚድንበት ሁኔታ ግን አይታወቅም።እና ሳርኮዚ ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሰርተዋል።ይሕን በማለቴ አዝናለሁ ግን መፍትሔ መሆኑን አላዉቅም።ለማንኛዉም እሳቸዉ እንደ ቡሽና እንደ ኩሽኔር አስቀድሞ የሐይል እርምጃ መዉሰድ መፍትሔ ነዉ ብለዉ የሚያምኑ ፖለቲከኛ ናቸዉ።እስከ መቼ? አይታወቅም።ለዛሬዉ ግን ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ