የኢሰመጉ እና የመብት ተሟጋች ተቋማት ጥሪ
ሰኞ፣ ሰኔ 27 2014
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ እሥር በጋዜጠኞች፣ በማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ እርምት እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ምብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጠየቀ። ጉዳዩን አስመልክቶ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ ዜጎች በበኩላቸው ብዙዎች እንደሚታሰሩ እና ጥቂት የማይባሉትም ያሉበት እንደማይታወቅ በማመልከት ይኽ አካሄድ ዝም ተብሎ እንደማይታለፍ አመልክተዋል። ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ባወጣው ዘገባ የትግራይ ጦርነት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የቀጠለውን የቀውስ አዙሪት እየከለለው መሆኑን ገልጿል።
ብዙውን ጊዜ ሕገ - ወጥ የሆነ አስገድዶ የመሰወር ድርጊት ወይም እሥር በፌደራል እና በተለያዩ የክልል መንግሥታት እየተፈፀመ መሆኑን ያስታወቀው ኢሰመጉ ይህ ድርጊት በሀገሪቱ እያንሰራራ የነበረውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የፕሬስ ነጻነትን እና የፖለቲካ ምህዳሩን እጅጉን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህ ሕገ-ወጥ ያለው ድርጊት እንዲቆም በተደጋጋሚ ሲወተውት መቆየቱን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ተያያዥ የሕግ ግዴታዎችን ጠቅሶ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትንና አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዲከበር፣ እያንዳንዱ ሰው በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነቱ የመጠበቅ እና ሰው በሕግ ከተደነገገው ስርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር እንደማይገባ ጠቅሶ ድርጊቶች እንዲታረሙ አሳስቧል።
ቪዥን ኢትዮጵያ ፎር ዴሞክራሲ የተባለው የሲቪክ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ «ማንም ሰው ሊያጠፋ ይችላል። ማንም ሰው ካጠፋ ደግሞ በሕግ ሊዳኝ ይችላል። ነገር ግን የሕግ የበላይነት ከሌለ ፍትሕም ስለማይኖር ሰዎችን ዝም ብሎ መያዙ ከሕግ ውጪ ነው» ብለዋል።
«ዛሬ የሕግ የበላይነት ሳይሆን የፖለቲካ የበላይነት ጎልቶ እየታያ ነው። ይህ መታረም አለበት ። ሰው ከመንገድ ላይ እንደ ከብት እየተያዘ ወደ እሥር ቤት ይሂድ ማለት ሙሉ በሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ መታረም መቻል አለበት» ብለዋል።
መንግሥት ይህንን ምን ሲሆን ነው የሚያደርገው ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያንን የሚያደርጉት « አንደኛ በራስ መተማመን ሲያጡ ፣ ሁለተኛ በአማካሪዎች ብቃት ማነስ፤ ሦስተኛ በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎች ሲያሳስቷቸው» በማለት መልሰዋል።
የመንግሥት ኮሙኒካሽን አገልግሎት ከቀናት በፊት በሰጠው መግለጫ ከ «የፖለቲካ ለውጥ» የመነጩ ባላቸው «የጽንፈኝነት እና የመገፋፋት የፖለቲካ አመለካከቶች» ምክንያት «ግጭቶች ፣ የሰው ሕይወት መጥፋት ፣ የንብረት ውድመት» መኖራቸውን ጠቅሶ ይህንን ለመመከት « የተቀናጀ ሕግ የማስከበር እርምጃ » እየተወሰደ መሆኑን ገልጿል። በወለጋ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በሽብርተኛ ኃይሎች ቢፈፀምም በሕግ ማስከበር እርምጃው በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይሄው እርምጃ ውጤታማ መሆኑን እና በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም እየተፈጠረ መሆኑንም አመልክቷል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች የትግራዩ ጦርነት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየቀጠለ ያለውን የቀውስ አዙሪት እየከለለው መሆኑን ጠቅሶ ዛሬ ባወጣው ዘገባ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት በኦሮሚያ ክልል በሚፈጸሙ የተባባሱ ያላቸው የመብት ጥሰቶች ላይ ያለመከሰስና ተጠያቂነት ያለመኖር ሁኔታዎች እንደነበሩ ፣ አሁንም መቀጠላቸውን ጠቅሶ አፋጣኝ ዓለምአቀፍ ትኩረት የሚሹ ናቸው ብሏል። የሂውማን ራይትስ ዎች ዘገባ መንግሥት እና አጋሮቹ በኦሮሚያ ክልል እያደገ የመጣውንና ብዙዎችን እየጎዳ ያለውን አሳዛኝ ክስተት ከዚህ በላይ በቸልታ ሊመለከቱ እንደማይገባም አሳስቧል። በሕዝብ ዘንድ የፀጥታ መዋቅር ማሻሻያ እና የመልሶ መቋቋም ፍላጎት እንዳለ የዘረዘረው ይሄው ድርጅት መንግሥት በክልሉ ነዎሪዎች ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆም ፣ በራሱ የፀጥታ ኃይላት እና በታጣቂ ቡድኖች የሚፈፀመውን ግፍ ለማጣራት የሚረዳውን ገለልተኛ እና ታማኝ የምርመራ ሥራዎች ማመቻቸት እንደሚችልም አመልክቷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ