1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18 2017

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እየታገዱ ያሉትን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች "የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር" ባለሥልጣኑ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቋል።

https://p.dw.com/p/4ocjm
ኢሰመኮ በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች ምኅዳሩን እንዳያጠቡ ጠየቀ
ኢሰመኮ በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች ምኅዳሩን እንዳያጠቡ ጠየቀምስል Solomon Muchie/DW

በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች ምኅዳሩን እንዳያጠቡ ተጠየቀ

በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች ምኅዳሩን እንዳያጠቡ ተጠየቀ

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን እንዳያጠቡ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አደረገ።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በተከታታይ እየታገዱ ያሉ ድርጅቶችን በተመለከተ ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ እርምጃው በማኅበር የመደራጀት መብት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ሥጋቱን ገልጿል።

ባለሥልጣኑ የድርጅቶቹን "የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች" ሲልም ኢሰመኮ ጠይቋል።

ዶቼ ቬለ የድርጅቶቹን መታገድ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልተሳከም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እየታገዱ ያሉትን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተመለከተ ዛሬ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው አጭር መግለጫ ከዚህ በፊት የታገዱ ድርጅቶችን ጉዳይ እየተከታተለ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ባለበት ወቅት በዚሁ ሳምንት አጋማሽ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ጉልህ ተግባር ያከናውናሉ የሚባሉ ሁለት ድርጅቶች መታገዳቸውን መገንዘቡን በመግለጽ፤ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች "የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር" ባለሥልጣኑ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ዲሬክተር ወይዘሮ ራኬብ መለሰ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ እርምጃው "በአጠቃላይ የሲቪል ምህዳሩ መጥበብ ላይ እና በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ነው በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረብነው" ብለዋል።

(ኢሰመጉ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ቢያግደውም ድርጅቱ "ሁል ጊዜም ቢሆን ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ፣ ነፃና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅት" ስለመሆኑ አስታውቋል
(ኢሰመጉ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ቢያግደውም ድርጅቱ "ሁል ጊዜም ቢሆን ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ፣ ነፃና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅት" ስለመሆኑ አስታውቋልምስል Ethiopian Human Rights Council

ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ የሲቪል ድርጅቶች ፈቃድ ይሰጣል፣ ይከታተላል፣ አልፎም የማረም፣ የማስተካከል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ ተሰጥቶታል።

ባለሥልጣኑ በተከታታይ እየወሰዳቸው ስላሉት የእግድ እርምጃዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ወደ ኃላፊዎቹ ብንደውልም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም። 

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላሦስቱ የሲቪክ ድርጅቶች የታገዱ ሰሞን በሰጡት መግለጫ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ "በአሁኑ ጊዜ 5300 ሲቪል ድርጅቶች አሉ" ብለው ነበር። 

"ባለፉት ዓምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሕግን ያልተከተለ ሥራ ሠርታችኋል፣ ገለልተኝነት የሌለው ሥራ ሠርታችኋል በሚል የታገዱ ድርጅቶች በቁጥር ስድስት ወይም ሰባት ቢሆኑ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
እግድ ማለት ምን እንደሆነ እና መሰል ዕጣ የገጠማቸው ድርጅቶች የቀጣይ ሂደታቸውን በተመለከተም በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰው ነበር።

"ጥቆማዎች ይመጣሉ። በጥቆማዎች መሠረት አስፈላጊው ማጣራት ይደረጋል። የመስክ ክትትልም ይደረጋል። በሚገኘው ግኝት መሠረት የሚሻሻል ከሆነ ምላሽ ይሰጣል፣ ቀላል ጥፋት ከሆነ ቀላል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፣ ከባድ ጥፋት ነው ተብሎ እምነት ከተያዘበት ደግሞ ወደ ማገድ ደረጃ ሊደርስ ይችላል"።

"ጥቆማዎች ይመጣሉ። በጥቆማዎች መሠረት አስፈላጊው ማጣራት ይደረጋል።"  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣ
"ጥቆማዎች ይመጣሉ። በጥቆማዎች መሠረት አስፈላጊው ማጣራት ይደረጋል።" የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንምስል olomon Muchie/DW

እግድ የተጣለባቸው ኢሰመጉ እና ካርድ ትናንት ያወጧቸው መግለጫዎች
የ33 ዓመታት አገልግሎት ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከማንኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ቢያግደውም ድርጅቱ "ሁል ጊዜም ቢሆን ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ፣ ነፃና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅት" ስለመሆኑ አስታውቋል።

ድርጅቱ "ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለሕግ የበላይነት" የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት በመከተል በገለልተኝነትና በኃላፊነት መንፈስ ሥራውን  እንደሚወጣ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ከሳምንታት በፊት በተቆጣጣሪው አካል ታግዶ ሲያበቃ እግዱ እንደተነሳለት ከተገለፀ በኋላ ዳግም የእግድ እርምጃ ተወስዶበታል። ካርድ ይህ በመሆኑ ድርጅቱ ላይ "ከፍተኛ ተጽዕኖ" ደርሶብኛል ብሏል። የሀገሪቱን ሕጎች አክብሮ መንቀሳቀሱን ያስታወቀው ካርድ "ያለምንም ተጨባጭ ጥፋት ለተደጋጋሚ ጫና እየተዳረገ መሆኑ እጅጉን ያሳስበናል" ሲል በመግለጫው ጠቅሷል። 
ሶሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ