በደን ምንጣሮ የሚመረተውን ምርት ያገደው የአውሮፓ ህግ እና ስጋቱ
ረቡዕ፣ ጥር 22 2016በደን ምንጣሮ የሚመረተውን ምርት ያገደው የአውሮፓ ህግ እና ስጋቱ
“እኛ ያለ ቡና የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ቡና ልብሳችን፣ ምግባችን እና ብንታመም ህክምናችን ነው” የጅማው ቡና አምራች አርሶ አደር አስተያየት ነው፡፡
በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ከአጋሮ ከተማ ወጣ ብላ ነገር ግን በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው በሻሻ ቀበሌ ውስጥ ለአይን ታይቶ የማይዘለቅ ጫካ ይስተዋላል፡፡ ቦታው 18 ሄክታር የሚሸፍን ነው ተብለናል፡፡ ጫካውም በቡና ተክል የተፈጠረ ሲሆን ጥቅጥቅ ደን መስሏል፡፡ በዚህ መሃል አንድ አርሶ አደር ቆመዋል፡፡ ሙስጠፋ አባቀኖ አባዲጋ ይሰኛሉ፡፡
በዚህ በስፋት የሚታይ ደን ቡና ነው፡፡ ደግሞ ቡና ያለ ደን ደንም ያለ ቡና የማይኖሩበት፤ አንዱ ከሌላው የማይነጣጠልበት ስፍራ ይመስላል፡፡ አርሶ አደር ሙስጣፋም ይህንኑን ይመሰክራሉ፡፡ “ቡና ከልሰራን መኖር አንችልም፡፡ ሌላ እርሻ የለንም፡፡ መተዳደሪያችን ው ቡና ነውና ለዚያም ነው በቡና ተከበን ያለነው” ይላሉ፡፡
የጅማ አርሶ አደርች የቡና ጥገኝነት
በዚሁ በበሻሻ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሌላው መተዳሪያቸው የሆነውን የቡናን ማምረት ስራ ከወላጆቻቸው የወረሱት የቡና አምራች ገበሬ አሚኖ አባቀኖ አባጊቤ እሳቸውን ጨምሮ የአከባቢው ህዝብ በብዛት ህይወታቸው ምን ያህል በብርቱ ከቡና ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ለማስረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ “እንደው ለእና ቡና አይሸጥም የሚል ነገር ብንሰማ በጣም አደጋ ነው፡፡ ስጀመር እኛ ህይወታችን በሙሉ ከቡና ጋር የተሳሰረ ነው” ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ለጊዜው ቡናን እንደ ሌሎች ውስን ገበሬዎች ከማምረት ተሻግረው ወደ መላኩ ባይገቡም አሚኖም መላውን ቤተሰባቸውን ከዚሁ ምርት ከሚያገኙት ዓመታዊ ሽያጩ ቤተሰባቸውን ይመሩበታል፤ ህይወታቸውንም ይገፉበታል፡፡
የቡና አምራቾች በላኪነት መሳተፋቸው
የቡና አምራች አርሶ አደሩ ሙስጠፋ አባቀኖ ቡናን እያመረቱ “ፋልከን ኮፊ” ለተሰኘው ለእግሊዝ ኩባንያ ቀጥታ መላክ ከጀመሩም ወደ አምስተኛ ዓመታቸው እያኮበኮቡ ነው፡፡ “ኩባንያው ከኔ ገዝቶ ለብዙ ኩባንያዎች ነው ቡና የሚያከፋፍለው፡፡ እኔን ጨምሮ በአከባቢያችን ያለው አርሶ አደር በሙሉ አሁን ውጥኑ የቡናን ምርታማነት ማሳደግ የሚቻልበት አግባብ ላይ መስራት ነው፡፡ ከሌላ ቡና ብስባሾችን አምጥተን እዚህ መድፋት ቡናችንን መንከባከብ ነው ስራችን፡፡ ከሰራን ደህና ብር እኛገኝበታለን፡፡ ገቢያውም ምንም እንኳ ከአምና አንጻር ብቀዘቅዝም ቆንጆ ዋጋ እናገኝበታለን” ብለዋል፡፡
ታታሪው የቡና አምራች አርሶ አደር እና ላኪ ሆነው ያለመታከት የሚሰሩቱ አርሶ አደር ሙስጠፋ በማህበራቸው በኩል ከጢቂት ወራት በፊት ተለቅሞ የተሰናዳውን ስፔሻሊቱቲ ቡና ለውጪ ገቢያ ለማቅረብ ላይ ታች ይላሉ፡፡ በተለያየ መልክ ለውጪ ገበያ የሚዘጋጀው ስፔሻሊቲ ቡናም በርካታ ሰራተኞች በተገኙበት ይሰናዳል፡፡ ሙስጠፋ ዘንድሮ በራሳቸው ከሚያመርቱት በተጨማሪ ከአከባቢቸው የሰበሰቡትን ስምንት ኮንተይነር ቡና ወደ ውጪ ገበያ ለመላክ አሰናድተዋል፡፡ አንድ ኮንተይነር 19 ሺህ 200 ኪ.ግ. ቡናን ነው የሚይዘው፡፡ በብዛት በያመቱ ሶስት ኮንተይነር ቡና ይልኩ የነበሩት ሙስጠፋ ከፍተኛውን ሰባት ኮንተይነር ለውጪ ገበያ ያቀረቡትም አምና ነበር፡፡
“ለራሴ የማመርተውን አምርቼ ቀሪውን ከአከባቢው ቡና አምራች አርሶ አደሮች በማሰባሰብ ነው ከራሴ ቡና ጋር በመላክ ሽጬ ድርሻቸውን የማከፋፍላቸው” የሚሉት የቡና አምራች አርሶ አደሩ ሙስጠፋ አባቀኖ አባገሮ፤ ለራሳቸው ከሚያሳዩት ብርታት በተጨማሪ የአከባቢው አርሶአደሮችም በቡና ምርቱ እንድበረቱ እንደሚያነሷሷቸው አይሸሽጉምም፡፡
በዚያው በጎማ ወረዳ ከአጋሮ ደግሞ በሌላኛው አቅጣጫ ወደ በደሌ በሚያቀናው ጎዳና ወጣ ብለን ገደመሳ በተባለ ቀበሌ ቡናን አምርተው ወደ ውጪ ገቢያ የሚልኩትን ሌላኛውን አርሶ አደር ተዋወቅናቸው፡፡ ሙስጠፋ መሃመድ አሊ ይባላሉ፡፡ አቶ ሙስጠፋ መሃመድ በወረዳቸው በ2010 ዓ.ም. ለ300 ገደማ አርሶ አደሮች የቡና ላኪ ፈቃድ ሲሰጥ በእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ካላቅማሙትም ናቸው፡፡ አቶ ሙስጠፋን በቀዳሚነት የጠየቅናቸው ቡናን አምርቶ ለአገር ውስጥ ገቢያ አሊያም ለነጋዴዎች አሳልፎ ከመሸጥ እና በቀጥታ ወደ ውጪ ገቢያ መላክ መካክል ያለውን ልዩነት እንዲያስረዱን ነው፡፡ “በፊት ቡናን ወደ ውጪ በማንልክበት ወቅት ዓመቱን ሙሉ የለፋንበትን ቡና ሰብስበን ስንሸጥ የዓመት ቀለባችን እንኳን በሰቀቀን ነበር የምንቋቋመው፡፡ ልጆቻችንን በቡናችን ማስተማር የማንችልበት ደረጃ ላይም ነበርን፡፡ አሁን ግን የቡና ላኪነት ፈቃዱን በ2009 አግኝተን በ2010 ዓ.ም. ቡናችንን ቀጥታ መላክ ከጀመርን ወዲህ የምትመለከተውን ድርጅት ማቋቋም ችለናል፡፡ ከቡና መፈልፈያ ማሽን እስከ የተለያዩ በርካታ ጠቃሚ ነገሮች አፍርተናል፡፡ ድሮ ቀለብ የማይችለው ቡና ወደ ውጪ ሲላክ የዚህ ሁሉ ድርጅት ባለቤት ያደርግሃል ማለት ነው” በማለት በሁለቱ መሃል ያለውን ልዩነት በአግራሞትም ጭምር ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ገቢያ ወሳኝነት
እንደ ሙስጠፋ አባቀኖ ሁሉ የአቶ ሙስጠፋ መሃመድም የቡና ገዢ ደንበኞች ሙሉ በሙሉ ያሉት አውሮፓ ላይ ነው፡፡ ለፈረንሳዩ “ቤልኮ” ኩባንያ ቡናን በገፍ ይላኩ እንጂ ጀርመንን ጨምሮ በርካታ አገራትም የቡናቸው መዳረሻ ናቸው፡፡ “ቤልኮ የሚባል የፈረንሳይ ድርጅት ነው ቡናችንን የሚገዛው፡፡ ከዚያን ወደ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ሌሎችም ቤልኮ ያከፋፍላል” ይላሉ፡፡
አቶ ሙስጠፋ ቡናውን በሚያመርቱበት ጊዜ እነዚህ ገዢ ድርጅቶች ሂደቱን ሁሉ እንደሚከታተሉም ነው የሚስረዱት፡፡ “ከመሰረቱ የቡናን አመራረት ይቆጣጠሩናል፡፡ እንዴት እንደሚለቀምና እንዴት እንደምናደርቅ ይከታተሉናል፡፡ በዚያ መንገድ ያሰባሰብነውን ቡና አሰናድተን እስከ ጅቡቲ ሸንተን ወደ መርከባቸው ሲተላለፍ ይከፍሉናል፡፡ ደንበኞቻችን ቡናን የሚረከቡን በተለያየ መንገድ ነው፡፡ በደረቁ የሚረከቡን እንዳሉ የታጠበንም የሚፈልጉ አሉ፡፡ በዚያ በፍላጎታቸው መሰረት አዘጋጅተንላቸው ነው የምናስረክበው” ብለዋል፡፡
በቡና መላኩ ሂደት ውስጥ የእነዚህ ቡና አምራች ገበሬዎች ተጠቃሚነት ከዚህ አንጻር አጠያያቂም አይደለም፡፡ አቶ ሙስጠፋም ይህንኑን ነው የሚመሰክሩት፡፡ “እዚህ ውስጥ ከእኛም ተጨማሪ መንግስትም ዶላር ስገባ ተጠቃሚ ነው፡፡ እኔ አሁን በአንድ ምርት እስከ 10 ሚሊየን ብር ገቢ አገኛሉ በኣመት” ይላሉ፡፡
አዲሱ የአውሮፓ ህግ ማዕቀፍ እና የቡና አምራቾችና ላኪዎች ስጋት
በዚህ ደረጃ ህይወታቸው በሙሉ በቡና ላይ የተንጠለጠለውን የጅማ ቡና አምራች ገበሬዎች ምናልባትም በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ቡናን ጨምሮ ደን ተጨፍጭፎ የሚመረቱትን ምርቶች ወደ አውሮፓ ገቢያ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ህግ ተግባራዊ ሲያደርግ ጉዳዩ እነሱንም ይመለከት ይሆን የሚለውን መልሰን አቅርበንላቸው ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ 2015 ዓ.ም. የጸደቀው ይህ የአውሮፓ ህበረት ረቂቅ ህግ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ማገባደጃ ላይ ገቢራዊ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
ስለጉዳዩ ጠንቅቀው የሚያውቁት የጅማ ቡና አምራች ገበሬዎቹ ስለዚሁ ተጠይቀው የተደበላለቀ ስሜታቸውን አስተጋብተዋል፡፡ ቡናን እያመረቱ በቀጥታ ለአውሮፓው ገቢያ የሚያቀርቡት ሙስጠፋ መሃመድ ቡናን ለማምረት ደን መጨፍጨፍ አስፈላጊ በማይሆንበት በነሱ አከባቢ እንዲህ ያለ ነገር ስጋት እንደማሆን ነው የሚስረዱት፡፡ “ምንም ስጋት የለብንም፡፡ ደብዳቤ በአካል በግሌ ደርሶኛል፡፡ የደረሰንም ቡናን በሚረከበኝ በቤልኮ በኩል ነው፡፡ እንደ ግሌ ከሆነ ነገሩ የማይመለከተን፤ እኔ ቡናን ሳመርት ሜዳን ወደ ደን ቀየርኩ እንጂ ደን ጨፍጭፌ ቡና አልተከልኩም፡፡ በደጋ አከባቢም ምንም ምንጣሮ ሳናካህድ በደኑ ውስጥ ቡና ያመረትንበት አለ፡፡ ደብዳቤው ብግል ስለሆነ እየተላከ ያለው ስጋቱ ደን ለጨፈጨፉት ብቻ ይመስለኛል፡፡ መሬት ላይም መጥተን እናጠናለን ብለውኛል፡፡ ከዚን በኔ ላይ የተለየ ነገር እስካልተገኘ ድረስ ስጋት የሚሆንበት ምክኒያት አይታየኝም” ይላሉ፡፡
ምንም እንኳ በጅማ ቡና እና ደን አብሮ የሚኖሩ፤ አንዱን ለማልማት ሌላውን ማውደም እምብዛም ያልተለመደ ብሆንም፤ ይህ የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ በእጅጉ እንዳስደነገጣቸው እና ስጋትም ውስጥ እንደከተታቸው ሌላኛው የቡና አምራች እና ላኪው ገበሬ ሙስጠፋ አባቀኖ አልሸሸጉም፡፡ “ውሳኔውን ሰምቻለሁ፡፡ ነገሩን ሁሉም የቡና አምራች ገበሬዎች ይስሙት አይስሙት አላውቅም፡፡ ነገሩ ከማዛዘንም አልፎ በእጅጉ አስግቶኛል፡፡ በርግጥ በኛ አከባቢ አስቀድሞም የቡና አመራረት እነሱ ከኒያስቀምጡት አቅጣጫ ውጪ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ምናልባት ሌሎች አከባቢ ደን ጨፍጭፈው ቡና የሚያመርቱ ካሉ ቶሎ ለነሱም ግንዛቤ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ያልሰሙ እንዲሰሙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ቡናችንን እየሸትን ላንቀጥል እንችላለን ማለት ነው” በማለት ጥልቅ ስጋታቸውን አጋርተውናል፡፡
ቡናን አምርተው ለላኪዎች የሚቀርቡትና በዚሁ በዓመት አንዴ በሚያገኙት ገቢ የቤተሰቦቻቸውን ጉሮሮ የሚደፍኑት የቡናው ገበሬ አሚኖ አባቀኖም ይህንኑን ሃሳብ አጠናክረዋል፡፡ “በእኛ ዘንድ ቡና እና ደን አይነጣጠሉም፡፡ ሁለቱም አንድ ላይ ነው የሚኖሩ” ብለዋል፡፡
ገበሬዎቹ አመራራች ሃሳብስ ኖራቸው ይሆን?
አይበለውና መሰል ጠቃሚ የቡናቸው መዳረሻ ገቢያ ከተስተጓጎሌ የቡናው አምራች ገበሬዎቹ ሌላ ምርት ላይ ፊታቸውን ማዞር አሊያም ለቡናቸው አዲስ ገቢያን መፈለግ ግድ ይላቸዋል፡፡ የጅማዎቹ ቡና አምራች ገበሬዎች ይህ ሁለቱም ቀላል አይሆንም ባይ ናቸው፡፡ ከማያውቁት አዲስ ምርት ጋር መተዋወቅም ሆነ አዲስ ገቢያ ለቡናቸው መፈለግ ብርቱ ጥረት ከመፈለግም አልፎ አታካችም ጭምር ነው፡፡ “እንደኔ ውጤታማ ያደርጋል ብዬ የማምነው ቡናን ነው፡፡ በርግጥ ስንዴ አሁን መዳ ላይ ትዘራለህ በተወሰነ ጊዜ ትሰበስባለህ፡፡ የእኛ መሬት ግን ለዚያም የሰጠ አይደለም፡፡ ቡናን ነው የለመድነው፤ መሬታችንም ያንኑን ነው የሚሰጠን፡፡ ለእኛ አማራጭም አይሆንም፡፡ ተስፋ የምናደርገው የአውሮፓው ገቢ እንደማዘጋብን ነው፡፡ ብዘጋ እንኳ ኢሲያም ቢሆን አዲስ ገቢያ ከመፈለግ አንቦዝንም” ብለዋል፡፡
በዚሁ በጎማ ወረዳ አጋሮ ከተማ መቀመጫውን ያደረገው ከታ-ሙዱጋ የተባለ የቡና ላኪ ዩኒየን በአከባቢው ካሉ አምስት ወረዳዎች ቡናን ሰብስቦ ወደ ውጪ ይልካል፡፡ ቡናን አጫርቶ ከመግዛት እስካ ወደ አዲስ አበባ መላክ፤ በዚያም መጋዘን ተከራይቶ የትራንስፖርት ሁኔታን አመቻችቶ ጅቡቲ እስከማድረስ ብርቱ ውስብስብ ውጣወረዶች አሉት የሚሉት የዩኒየኑ ኃላፊ አሚን አባፊጣ አሁን በርካቶችን እየሰጋ ያለው የአውሮፓ ገቢያን የማጣቱ ጉዳይ እምብዛም ስጋት ሆኖ አይሰማቸውም፡፡ “እኛ ጋ ምንጣሮ ብሎ ነገር የለም፡፡ ይህ ብዙም የሚሰጋን አይደለም፡፡ ቡና ተቀባቻችንም በያመቱ በመኪድሱልን ሰርቲፊከት ህን እውነታ ስለሚውቁ በደን ምንጣሮ የሚመጣ መዘዝ እኛ አከባቢ ስጋት አይሆንም” ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ትንሽ ገቢ ያላቸው በመቶ ሺዎች ሚቆጠሩ ገበሬዎች በቡና ብቻ ቤተሰቦቻቸውን ይመራሉ፡፡ ድርቅ እና የጸጥታ ችግሩ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚያማርራቸው የኢትዮጵያ ቡና አምራች ገበሬዎች ይህ የመዳረሻ ገቢያ ፈተና ከታከለበት ነገሩ ከባድ ነው፡፡ ለድርቅ የማይበገረው የጅማ አከባቢ ግን ከጸጥታውም ረገድ ቢንስ እስካሁን ብርቱ ፈተና ያለበት አይመስልም፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ