የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አውሮፕላን ግዢ
ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከአሜሪካው ግዙፍ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ጋር ትናንት ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. አመሻሹን አዲስ አበባ ውስጥ ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ስምምነቱ አየር መንገዱ እስከ 20 የሚደርሱ B777X-9 አውሮፕላኖችን መግዛት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ስምምነት ነው ብለዋል፡፡
B777X-9 አውሮፕላን ምንነት
የዚህ ሞዴል አውሮፕላኑ በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ባለ ሁለት ሞተር ግዙፍ አውሮፕላን ስለመሆኑ ተገልጿል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተመረተና የላቀ ደረጃ ያለው የተባለው አውሮፕላን ለረጂም ጊዜ እንዲያገለግል ተደርጎ የተሠራና ጉዳት ቢገጥመው እንኳ በቀላሉ መጠገን የሚል ነው ተብሏል። ለተሳፋሪዎች ምቾት የሚሰጡ ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት የተባለው ይህ አውሮፕላን ባንዴ 50 የቢዝነስ እና 390 የኢኮኖሚ ባጠቃላይ 440 ተሳፋሪዎችን ማጓጓዝ የሚችል መሆኑም ተነግሯል። ይህም አውሮፕላኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ግዙፉ እንደሚያደርገው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው አስረድተዋል።
“የኢትዮጵያ አየር መንገድይህን አውሮፕላን ወደ ሥራ ሲያስገባ ኩራት ይሰማዋል። ይህን አልትራ የሆነው የአውሮፕላን ሞዴል በአፍሪካ አገልግሎት ላይ ለማዋል ቀዳሚ እንሆናለን። በርግጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደምም የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ላይ አዳዲስ የአውሮፕላን ሞዴሎችን በመጠቀም ቀዳሚነቱን ሲያረጋግጥ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ጊዜው ሌላኛውን ዘመናዊ አውሮፕላን ትሪፕል ሰቨን-9 (B777X-9) ወደ አፍሪካ አየር ትራንስፖርት አገልገሎት ማምጣታችንን የምናሳውቅበት ነው። በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኩራት ይሰማዋል።» ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው።
የአዲሱ አውሮፕላን ግዢ የአየር መንገዱን አገልግሎት የማሳደግ ብቃት
አየር መንገዱ እነዚህን 20 አውሮፕላኖች ወደ ገበያ ሲያስገባ ከቦይንግ ኩባንያ ያዘዛቸው አውሮፕላን ቁጥር 104 ይደርሳሉ። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደሚሉት ይህ ሂደት አየር መንገዱ በ2035 በአንዴ 271 አውሮፕላኖቸን ወደ አገልገሎት የማሰማራት ግቡን ለማሳካት የሚረዳ እርምጃ ነው። «B777X-9 65 ሺህ ቶን ጭነት መሸከም ይችላል። 440 ተሳፋሪዎችንም በአንዴ ማጓጓዝ ይችላል። ይህ ከፍተኛ የተሳፋሪዎች የጉዞ ፍላጎት መዳረሻ ወደ ሆኑ እንደ ዋሽንግተን እና የቻይና ጉዋንዡ ተሳፋሪዎችን ለማጓጓዝ ፋይዳው ትልቅ ነው። በስምምነታችን መሰረት ከሦስት ዓመታት በኋላ በ2027 ሦስት አውሮፕላኖችን ከቦይንግ እንረከባለን። ሦስቱን በ2029 እንዲሁም ሁለቱን በ2030 ነው የምንረከበው። ግን በስምምነቱ ቀሪዎቹ 12 አውሮፕላኖችንም በዚሁ ከ2027-2030 ባለው የጊዜ ገደብ የመረከብ አማራጭም አኑረናል። ስምምነቱን የተፈራረምነው በመነሻ ዋጋ ሲሆን ይህም 11 ቢሊየን ዶላር ይጠጋል» ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው። የአውሮፕላን ግዢው አየር መንገዱን በአገልግሎት ዘርፉ እጅግ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው ታምኗል።
የቦይንግ ኩባንያ አስተያየት
የቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያን ወክለው ስምምነቱን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያኖሩት የኩባንያው የንግድ ሽያጭ እና ገበያ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለን የአየር መንገዱን የረጂም ጊዜ ደንበኝነት አሞካሽተው አንስተውታል። «የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ለመግዛት ያዘዘው 20 B777X-9 አውሮፕላን ብቁና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ያመረትናቸው ናቸው። አየር መንገዱ ባዘዛቸው በእነዚህ አውሮፕላኖች እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርቱን ያቀላጥፍበታል የሚል እምነት አለን። በቦይንግ ኩባንያ ላይ ያላችሁ መተማመን በመቀጠሉ አመሰግናለሁ።» ሲሉ ከስምምነቱ በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለው የገበያ ትስስር ከ1945 መጀመሩ ይነገራል። ይህ ትስስር ከአውሮፕላን ግብይት ባሻገር በአውሮፕላን ጥገና፣ በአመራር እና ፓይሌቶች ስልጠናም መደገፉ ነው የተጠቆመው።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ