የኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ትንተና በዓለም ባንክ ባለሙያዎች ጥያቄ ተነሳበት
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16 2017በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና በዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር (IDA) የጸደቀው የኢትዮጵያ የዕዳ ትንተና በዓለም ባንክ ባለሙያዎች ጥያቄ ተነስቶበታል። ሁለት የባንኩ ከፍተኛ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ የተዘጋጀው ትንታኔ “ስህተት” ሊሆን ይችላል የሚል ዕምነታቸውን እንደገለጹ ሬውተርስ ዘግቧል።
በዓለም ባንክ ባለሙያዎች ጥያቄ የተነሳበት የዕዳ ትንተና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ለመደጎም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር በተበደረበት ሥምምነት የተካተተ ነው።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ሥር የሚገኘው የዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር (IDA) በሐምሌ ወር ያጸደቁት ይኸ ሰነድ ኢትዮጵያ “የዕዳ ጫና” ውስጥ የምትገኝ እና ያለባት የብድር መጠንም “ዘላቂነት የሌለው” እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
ትንታኔው የተሠራው የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጪ አጠቃላይ ዕዳ 64.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በነበረበት ወቅት ነው። ከዚህ ውስጥ በወቅቱ 28.9 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ሀገሪቱ ከውጪ የተበደረችው እንደሆነ ሁለቱ ተቋማት ያዘጋጁት የዕዳ ዘላቂነት ትንተና ያሳያል።
ኢትዮጵያ ከሀገራት እና ቦንድ ሸጣ የተበደረችውን ዕዳ አከፋፈል በማሸጋሸግ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከዕዳ ክፍያ የማዳን ፍላጎት እንዳላት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ባለፈው ነሐሴ ተናግረው ነበር። “በዚህ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለዕዳ ልትክፈል የምትችለውን 4.9 ቢሊዮን ዶላር ታድናለች” ያሉት ኢዮብ “ይኸ ገንዘብ ለጠቃሚ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ይውላል” ብለው ነበር።
ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የጠበቀችው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር እንዲጠናቀቅ የሀገሪቱ ብድር የመክፈል አቅም ላይ የተሠራው ትንታኔ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። የዐቢይ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የተበደረበት የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተሰኘ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ዕዳ አከፋፈል ለማሸጋሸግ የሚያስፈልግ አንድ ቅድመ ሁኔታ ነው።
የኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ትንታኔ ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዙ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት የገንዘብ እጥረት (liquidity) እና ዕዳ የመክፈል ጫና (solvency pressures) እንዳለባት ድምዳሜ ላይ የደረሰ ነው። የሀገሪቱ ዕዳ የመክፈል ጫና ኢትዮጵያ በውጪ ገበያ የምትሸጠው ሸቀጥ ከውጪ ዕዳ አኳያ ያለው ምጣኔ ዝቅተኛ መሆኑን ጭምር የሚጠቁም ነው።
የዓለም ባንክ አማካሪ ብሪያን ፒንቶ እና የባንኩ ዋና ኤኮኖሚስት ኢንደርሚት ጊል ግን በዕዳ ዘላቂነት ትንተናው መሠረት ኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት እንጂ ዕዳ የመክፈል ችግር የለባትም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን ሰነዱን የተመለከተው የሬውተርስ ዘገባ ይጠቁማል።
“የቦንድ ባለቤቶች የኢትዮጵያን የዕዳ ዘላቂነት ትንተና በትክክል እንደተረጎሙት ደርሰንበታል” ያሉት የዓለም ባንክ ሁለቱ ባለሙያዎች ይሁንና “ትንታኔው በራሱ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል” የሚል ዕምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ “ሌሎች ሀገሮችም የዕዳ ጫና ውስጥ ሲገቡ በኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ይደገማሉ” የሚል ሥጋታቸውን ለባንኩ ባቀረቡት ጽሁፍ ገልጸዋል። ዓለም ባንክ ስለ ባለሙያዎቹ ዕይታ በሬውተርስ ተጠይቆ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ባለሙያዎች የሀገሪቱን የተራዘመ የብድር አቅርቦት በገመገሙበት ወቅት የዕዳ ዘላቂነት ትንተናውን መልሰው መመልከታቸውን እና የተደረገ ትልቅ የአቋም ለውጥ አለመኖሩን ለሬውተርስ ተናግረዋል።
በኅዳር ወር ባለሙያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው እንደነበረ ያረጋገጠው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአንጻሩ እያንዳንዱ ግምገማ በዕዳ ዘላቂነት ትንተና ላይ ያሉ ለውጦችን እንደሚያካትት ለሬውተርስ ቢገልጽም ስለ ይዘታቸው ግን ያለው ነገር የለም። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በጻፉት ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጡም።
ኢትዮጵያ ከኦፊሴያል ከአበዳሪዎቿ ጋር ባደረገችው ውይይት “ጊዜያዊ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሥምምነት” ላይ ባለፈው ኅዳር 2016 ደርሳለች። ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚደረገው ድርድር በአንጻሩ ገና በመካሔድ ላይ ይገኛል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በታኅሳስ 2016 ለቦንድ ባለቤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር መክፈል የነበረበት ቢሆንም “ሁሉንም አበዳሪዎች ዕኩል ለማስተናገድ” በሚል መከራከሪያ ክፍያውን ሳይፈጽም ቀርቷል።
ኢትዮጵያ ቦንድ ሸጣ የተበደረችው አንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መልሳ ስትከፍል 18 በመቶ እንዲቀነስላት ጥያቄ አቅርባለች። ጥያቄው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤት በሆኑ የግል አበዳሪዎች መካከል ውጥረት የፈጠረ ነው። የቦንዱን ባለቤቶች የሚወክል ኮሚቴ መንግሥት ያቀረበውን ምክረ-ሐሳብ ከሀገሪቱ የኤኮኖሚ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም ነው በሚል ሳይቀበለው ቀርቷል።
የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ሁለቱ የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የዕዳ ዘላቂነት ትንታኔ ላይ የሰነዘሩት ሐሳብ በመንግሥት እና በቦንድ ባለቤቶች መካከል እየተደረገ በሚገኘው ድርድር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በአጭር ጊዜ የመክፈል አቅሜ ተዳክሟል የሚል ከሆነ” የቦንድ ባለቤቶች አከፋፈሉን ሊያራዝሙ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዶክተር አብዱልመናን “የረዥም ጊዜ ዘላቂ ችግር ከሆነ ደግሞ ከዕዳው ላይ መቀነስ አለበት” ሲሉ አስረድተዋል። የባንኩ ባለሙያዎች ግምገማ የኢትዮጵያ ቦንድ በሚሸጥበት ገበያ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በጎርጎሮሳዊው 2023 የኢትዮጵያ የውጪ ዕዳ 33.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደደረሰ የዓለም ባንክ የቅርብ ሪፖርት ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት 48%፣ እንደ ቻይና ያሉ አበዳሪ ሀገራት 35% እንዲሁም የግል አበዳሪዎች 17 % ድርሻ አላቸው። ኢትዮጵያ ቦንድ ሸጣ የተበደረችው በአንጻሩ ከውጪ ዕዳ 3% ድርሻ የያዘ ነው።
ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ እንዲደረግላት ጥያቄ ያቀረበችው በሐምሌ 2013 ነበር። ቻይና እና ፈረንሳይ በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመሩት የአበዳሪዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ ከመስከረም 2014 ጀምሮ ተከታታይ ስብሰባዎች ቢደረጉም እስካሁን አልተጠናቀቀም።
ባለፈው ሣምንት ኢትዮጵያን የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ “በሚቀጥሉት ጥቂት ሣምንታት የ3 ቢሊዮን ዩሮ ዕዳ አከፋፈል ለማሸጋሸግ ዕቅድ አለን” ሲሉ ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በቡድን 20 ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ እና በጊዜ ገደብ በጥር አጋማሽ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር በሚደረገው ጠቃሚ ስብሰባ ሙሉ ድጋፍ እናደርግላችኋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማክሮ ስለጠቀሱት የ3 ቢሊዮን ዩሮ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግም ይሁን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ስለታቀደው ውይይት ምንም ያሉት ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባደረገቻቸው ድርድሮች ግን ፈረንሳይ እና ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው አመስግነዋል።
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሠ