1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የኤርትራ መንግሥት ደጋፊና ተቃዋሚዎች በእስራኤል ተጋጭተው ሁለት ሰዎች ተገደሉ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2016

በእስራኤል የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት በሚደግፉ እና በሚቃወሙ ሁለት ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሁለት ኤርትራውያን መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። በቴል አቪብ በሚገኘው ሐሓጋና ጎዳና ሁለቱ ቡድኖች አንዳቸው በሌላው ላይ ድንጋይ እየተወራወሩ በመጋጨታቸው ከሞቱት በተጨማሪ ስምንት ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4jsss
Israel Tel Aviv
ምስል picture alliance/DUMONT Bildarchiv/E. Wrba

በእስራኤል የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን መንግሥት በሚደግፉ እና በሚቃወሙ ሁለት ቡድኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሁለት ኤርትራውያን መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። ዛሬ ቅዳሜ በቴል አቪብ በሚገኘው ሐሓጋና ጎዳና ሁለቱ ቡድኖች አንዳቸው በሌላው ላይ ድንጋይ እየተወራወሩ በመጋጨታቸው ከሞቱት በተጨማሪ ስምንት ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

የሕክምና ተቋማትን ዋቢ ያደረገው የፖሊስ መግለጫ “ሁለት ኤርትራውያን ወንዶች በግጭቱ ተገድለዋል” ብሏል።

 እረብሻ ያደፈረሰው የደን ሃጉ የኤርትራውያን ፌስቲቫል

ፖሊስ በመግለጫው ሁለቱ ወንዶች እንዴት ሕይወታቸውን እንዳጡ ያለው ነገር ባይኖርም የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በስለት ተወግተው በደረሰባቸው ጉዳት መሆኑን ዘግበዋል። 

ግጭቱ በተፈጠረበት ጎዳና የእግር መንገድ ላይ በነጭ ልብስ የተሸፈነ አስከሬን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ፎቶግራፈር መመልከቱን የዜና ወኪሉ ዘግቧል። ፖሊስ በግጭቱ ላይ ምርመራ መጀመሩን በመግለጫው አስታውቋል።

በሽቱትጋርቱ የኤርትራውያን ድግስ የተነሳው ረብሻና መዘዙ

በጎርጎሪዮሱ መስከረም 2023 በሁለት ተቀናቃኝ የኤርትራ ቡድኖች መካከል በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ግጭት ለመገላገል የሞከሩ እስራኤላውያን ፖሊሶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተጎድተው ነበር። 

በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች በእስራኤል የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ በሕገ-ወጥ መንገድ ከዓመታት በፊት የግብጽ ሳይናይ በረሐን ያቋረጡ መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

ኤርትራውያኑ ከሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ በምትገኘው የቴል አቪቭ ከተማ በርካታ የድሀ ሰፈሮች ይኖራሉ።