1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤች አይቪ/ኤድስ ይዞታ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 28 2014

በመላው ዓለም የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ 40 ዓመታት ተቆጥረዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የብዙዎች ትኩረት የኮሮና ተሐዋሲ ላይ ቢሆን ዛሬም የብዙዎች ስጋት ነው ኤች አይቪ ኤይድስ። በተለይ አፍሪቃ ውስጥ ከ25 ሚሊየን ሕዝብ በላይ የዚህ ተጠቂ ነው። የዓለም ኤች አይቪ ኤድስ ቀን ባለፈው ሳምንት  ታስቧል።

https://p.dw.com/p/43xDe
Lesotho Mobile Gesundheitsversorgung: Bluttests
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

የኤድስ ስርጭት ይዞታ በኢትዮጵያ

በዓለም ደረጃ የኤችአይቪ ተሐዋሲ ስርጭትን ለመግታት በተጀመረው ጥረት ብዙ ስኬቶች ቢገኙም አሁንም ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ፀረ ኤችአይቪ ህክምናው በመስፋፋቱ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ መነገር ጀምሯል።

በጎርጎሪዮሳዊው 1981 ዓ,ም ነበር አሜሪካውያን ዶክተሮች ምንነቱ ያልታወቀ ህመም በተወሰኑ ወጣት ወንዶች ላይ አገኙ። በሽታው ምንነቱ ሳይታወቅ በፊት ለየት ያለ የሳንባ መቆጣት ተደርጎ ነበር የተወሰደው። ስሙ ባልታወቀው በሽታ የሚያዙ ታማሚዎች ትኩሳት የሚያጠቃቸው ሲሆን የዕጢዎች መቆጣትም እንደሚታይባቸው ቆየት ያሉ ጥናቶች ያሳያሉ። በበሽታው ብዙ ወንዶች እና ሴቶች ከሞቱ በኋላ በዓመቱ አኳየርድ ኢሚዩን ዲፊሸንሲ ሲንድሮም በምህጻሩ ኤድስ የሚል ስያሜ አገኘ። የሰውን በሽታ የመቋቋም አቅም የሚያጠቃው HIV ተሐዋሲ ተገቢውን የህክምና ክትትል ካላገኘ ወደ ኤድስ እንሚሸጋገር የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። የዓለም የኤድስ ቀንን በጎርጎሪዮሳዊው 1988 ዓ,ም የተመድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲታሰብ ሲያደርግ ተሐዋሲው በዚህ ጊዜ ከ100 በሚበልጡ ሃገራት ተዳርሶ ነበር። ከዚህ ጊዜ አንስቶም በየዓለመቱ ኅዳር 22 ቀን ዕለቱ ይዘከር ጀመር። የዘንድሮው መሪ ቃል «የፀረ-ኤች አይ ቪ አገልግሎቶችን በእኩልነት ማዳረስ፤ ወረርሽኙንም መግታት» የሚል ነው። መላውን ዓለም ያዳረሰው ኤች አይቪ በተለይ አፍሪቃን ክፉኛ መጉዳቱ ተመዝግቧል። 25,5 ሚሊየን ሕዝብ ተይዟል። የተሐዋሲው በተስፋባቸው ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት በተለይ ደቡብ አፍሪቃ፣ ስዋዚላንድ፣ ቦትስዋና፣ ሌሴቶ፤ ማላዊ፣ ናሚቢያ፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያ እና ዚምባቡዌ ክፉኛ ተጎድተዋል። ጎርጎሪዮሳዊው 1996 ዓ,ም ለዚህ በሽታ መከላከያ የተገኘበት የተስፋ ዓመት ነው። ተመራማሪዎች የተለያዩ ሆኖም በአንድነት የሚወሰዱ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተሐዋሲው በደማቸው ለሚገኝ ወገኖች በመስጠት በዚህ ምክንያት ሞትን ለመቀነስ እንደሚቻል አመለከቱ። በእርግጥም ለውጥ መታየት ጀመረ። በዘርፉ ለረዥም ዓመታት የሠሩት የህክምና ባለሙያ ዶክተር አስቴር ሸዋአማረበአዲስ አበባ ዘውዲቱ መታሰቢያ ሀኪም ቤት የበሽታዎች መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለህክምና ዘግይቶ የመጣ ካልሆነ በስተቀር በኤችአይቪ የሚሞት ቁጥሩ ቀንሷል ነው የሚሉት። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ።

Symbolbild Aids
ምስል Colourbox

ሸዋዬ ለገሠ