1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ክርስትያን ታደለና ዮሐንስ ቧያሌው ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወር

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16 2017

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4oZag
የእስር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውን ጠበቃቸው ተናገሩ። ፎቶ ከማኅደርምስል Ritzau Scanpix/imago images

ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወር

 ሁለቱ ተከሳሾች በገጠማቸው የአንጀት ቁስለት ኅመም ምክንያት አሁንም ከፍተኛ ደም እየፈሰሳቸው በብርቱ ሕመም ላይ መሆናቸውን ጠበቃቸው ሰለሞን ገዛኸኝ ዛሬ ረቡዕ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት 41 ተከሰሾች መዛወራቸውን የገለፁት ጠበቃው፣ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው ለእሥረኞች አስቸጋሪ ነው ወዳሉት ዞን አምስት መዛወራቸው ሥጋት እንደፈጠረበቸው እና ወደ ሌላ ዞን እንዲቀየሩ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል። የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ ተከሰሾቹን መረከቡን አረጋግጦ ሰዎቹን «ተቀብለን በሥነ - ሥርዓት እያስተናገድን ነው» የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

«ሁለቱም ተከሳሾች በጠና ኅመም ላይ ናቸው» ጠበቃቸው

ከሁለት ሳምንት በፊት በመቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል የቅድመ ካንሰር ምርመራ የተደረገላቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱት አቶ ክርስትያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያሌው የምርመራ ውጤታቸውን ለመስማት ባለፈው ሐሙስ ቢቀጠሩም፤ በወቅቱ ታሥረውበት የነበረው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት «አጃቢ የለኝም» በሚል ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ ሳይወስዳቸው መቅረቱን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ተናግረው ነበር። ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ተከሳሾቹ ዓርብ ዕለት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተዛውረዋል።

«ዓርብ ዕለት ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ትዛወራላችሁ የሚል ነገር የደረሳቸው መሆኑን አቶ ክርስትያን ታደለ በማረሚያ ቤት ስልክ ደውሎ ነግሮኝ ነበር። አቶ ክርስትያን ታደለ መቆም አይችልም» ሲሉም ያሉበትን የኅመም ሁኔታ ገልፀዋል።

አቶ ዮሐንስ ገቡበት የተባለው ዞን ለተከሳሽ አስቸጋሪ ነው ስለመባሉ

ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ እንደሚሉት አሁን አቶ ዮሐንስ ቧያለው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ገቡበት የተባለው ዞን ለጊዜ ቀጠሮ ታራሚዎች አስቸጋሪ ቦታ ነው። 

«ወደ ቂሊንጦ ከተዛወሩ በኋላ አቶ ዮሐንስን ዞን አምስት ውስጥ ሲያደርጓቸው አቶ ክርስትያን ታደለን እና አብዛኞችን ተከሳሾችን ግን ዞን አራት ውስጥ ነው ያደረጓቸው»። 

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰጠው ምላሽ 

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተከሳሾቹን ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለማዘዋወሩ ያቀረበው የተገለፀላቸው ምክንያት ስለመኖሩ የጠየቅናቸው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ «ምንም የቀረበ ምክንያት የለም» ነው ያሉት። የቂሊንጦ ቀጠሮ ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክተር ኮማንደር ዓለምሰገድ አስገዶም ለዶቼ ቬለ በሰጡት ምላሽ ደግሞ «ሰዎቹን ተቀብለን በሥነ-ሥርዓት እያስተናገድን ነው» ብለዋል።

«ከማረሚያ ቤት ማረሚያ ቤት ዝውውር ነው የተደረገው። የተደረገውን ዝውውር መሠረት አድርገን፣ የውስጥ አሠራራችንን መሠረት አድርገን ሰዎቹን አስገብተናል። ተቀብለን በሥነ-ሥርዓት እያስተናገድን ነው። ምንም የተፈጠረ ችግር የለም። ማንኛውም ተጠርጣሪ የሚገባበት ግቢ ውስጥ ነው የገቡት የምንቀይረውም የለም» ብለዋል።

የተከሳሾቹ የመብት ጥያቄ እንዲመለስ በጠበቃቸው የቀረበ ጥያቄ

የሁለቱ ተከሳሾች የህክምና ጉዳይ ሦስተኛ ወሩን ይዟል የሚሉት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ትናንት ለፍርድ ቤት ሁለት አቤቱታዎችን ማቅረባቸውን ገልፀዋል። የቅድመ ካንሰር ምርመራ በተደረገላቸው መቅርረዝ ሆስፒታል ክትትሉን የሚያደርገው ባለሙያ አንድ በመሆኑ እና የሚገባው ሐሙስ በመሆኑ ነገ ይህ እንዳያልፋቸውም ጠይቀናል ብለዋል።

የሽብር ድርጊቶችን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176 አንቀጽ 45 በሽብር የተከሰሱ ሰዎች ለሚያቀርቡት የመብት ጥያቄ ፍርድ ቤት ቅድሚያ ሰጥቶ ጉዳዩን መፍታት አለብት እንደሚል የጠቀሱት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ የሁለቱ ተከሳሽ የምክር ቤት አባላት ጉዳይ በዚሁ ረገድ ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ