1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሾልስ የኢትዮጵያና የኬንያ ጉብኝት ፋይዳ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2015

ሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳይታሰብ በሰላም ስምምነት ማብቃቱ የሾልስን ትኩረት የሳበ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም። ሾልስ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ የሚጓዙት የጀርመን ኩባንያዎች ባለቤቶችንም አስከትለው ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ባለወረቶችን ለመሳብ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ የሚሳካው ኢትዮጵያ ተዘጋጅታ ስትጠብቃቸው ብቻ ነው

https://p.dw.com/p/4QoKp
Hannover Messe 2023 Eröffnung | Kanzler Scholz
ምስል FABIAN BIMMER/REUTERS

የሾልስ የኢትዮጵያና የኬንያ ጉብኝት ፋይዳ

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ከሚያዚያ 26 እስከ ሚያዚያ 28 2015ዓ.ም. ኢትዮጵያንና ኬንያን ይጎበኛሉ። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ክርስቲን ሆፍማን በሰጡት መግለጫ ፣ የሾልዝ የኢትዮጵያና ኬንያ ጉብኝት ትኩረት፣ ረሀብን መከላከል፣የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምጣኔ ሀብት ትብብር፣ ሰላም ማስከበርና የሱዳንን ግጭት  እንደሚሆን ተናግረዋል። ሾልስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ይመክራሉ።በአዲስ አበባ ከአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ መሀመት ፋኪ ጋርም ይነጋግራሉ። ዶቼቬለ ስለ ጉብኝቱ የጠየቃቸው  ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የመራኄ መንግሥት ሾልስ የዚህ ሳምንት የኢትዮጵያና የኬንያ ጉብኝት ምክንያታዊ ነው ይላሉ። ዶክተር ለማ  እንደሚሉት ሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳይታሰብ በሰላም ስምምነት ማብቃቱ የሾልስን ትኩረት የሳበ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም። ሾልስ በሁለቱ ሀገራት በሚያደርጉት ጉብኝት ከሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ የኤኮኖሚ ትብብር፣የአየር ንብረት ለውጥ እና ረሀብን መከላከል  ይገኙበታል። ዶክተር ለማ እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች የሾልዝ ትኩረት የሆኑባቸውን ምክንያቶች ተንትነዋል። 
ሾልስ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ከሚጎበኙዋት ከኬንያ የኃይልና የአካባቢ ጥበቃ አጋርነት ይሻሉ። ከምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት ዋነኛዋ የጀርመን የንግድ አጋር ኬንያ ከኃይል ፍላጎትዋ  90 በመቶውን የምትሸፍነው ከታዳሽ የኅይል የኃይል ምንጮች ነው። በተለይ በኬንያ የጂኦተርማል ኃይል በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል። ሾልዝ ቅዳሜ ናይባሻ ኃይቅ ላይ የሚገኘውን የኬንያ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ይጎበኛሉ። ሾልስ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ የሚጓዙት የጀርመን  ኩባንያዎች ባለቤቶችንም አስከትለው ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ባለወረቶችን ለመሳብ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።ይሁንና ይህ ሊሳካ የሚችለው ኢትዮጵያ የባለወረቶችን ፍላጎት ለማሟላት የበኩልዋን ዝግጅት አድርጋ ስትጠበቅ ብቻ ነው ይላሉ ዶክተር ለማ ።
ኦላፍ ሾልስ  የጀርመን መራኄ መንግሥት ከሆኑ ወዲህ  በአፍሪቃ ጉብኝት ሲያደርጉ የዚህ ሳምንቱ የመጀመሪያቸው አይደለም። ስልጣን ከያዙ 6 ወር ሳይሞላቸው የዛሬ ዓመት ኒዠር የሚገኙ የጀርመን ወታደሮችን ጎብኝተው ነበር። ያኔ ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪቃም ሄደው ነበር። ባለፈው ህዳርም ግብጽ  በተካሄደው የዓለም የዓየር ንብረት ጥበቃ ጉባኤ ላይም ተካፍለዋል።

 Workneh Gebeyahu mit Abdel Fattah al-Burhan und Abiy Ahmed
ምስል Tony Karumba/AFP
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር