1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለሥልጣናቱ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ግጭትን እንፈታለን አሉ

እሑድ፣ መስከረም 7 2010

የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ባለሥልጣናት በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉበትን ግጭት ለመፍታት ቃል-ገቡ።

https://p.dw.com/p/2k91c
Karte Äthiopien englisch

ባለ ሥልጣናቱ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ በቀሰቀሰው ግጭት የተፈጸመው ግድያ እና ማፈናቀል ሁለቱን ሕዝቦች አይወክልም ሲሉ ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ እና የሶማሌ ክልል አቻቸው አቶ አብዲሙሀመድ ኡመር ይኸን የተናገሩት ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።  ከዚህ ቀደምም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የድንበር  ግጭቶች ነበሩ ያሉት የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አብዲ ሙሀመድ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን ጎሳ ለይቶ ማፈናቀል ግን ታይቶ የማይታወቅ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱም ወገን የሰው ህይወት መጥፋቱን፤የአካል ጉዳት መድረሱን እና በርካቶች መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል። በደረሰው አሰቃቂ ግድያ "ሐዘናችን እጅግ በጣም ከባድ ነው" ያሉት አቶ ለማ ለግድያው ተጠያቂዎቹ ግለሰቦች እንጂ የኦሮሞ እና የሶማሌ ሕዝቦችን አይወክልም ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ለማ መገርሳም ይሁኑ አቶ አብዲመሀመድ ኡመር ችግሮቹን በጋራ ልንፈታ ይገባል ይበሉ እንጂ የደረሱበት ሥምምነት ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም። 

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ