1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር የተደረሰ ስምምነት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 2017

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) መካከል የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡ የክልሉ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በኦሮሚያ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/4nch1
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ከፍተኛ አመራር አቶ ሰኚ ነጋሳ
የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመራር ጋር የተደረሰ ስምምነት ምስል Oromia communication

በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በኦነሰ መካከል የተደረገ ስምምነት

በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሞ  ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) መካከል የሰላም ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በኦሮሚያ የነበረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ በይፋዊ ገጹ ባወጣው መግለጫ ላይ በኦሮሚያ የሚስተዋለው የፖለቲካ  አለመግባባት በአፈሙዝ ብቻ እልባት ያገኛል በሚል ስንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በብዛት ወደ ሰላም እየተመለሱ ነው ይላል፡፡

መንግስት የነበረውን ልዩነት በማጥበብ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ከኦነሰ አመራሮችና አባላት ጥሪውን ከተቀበሉት ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት እየሰመረ ይገኛልም ነው የተባለው፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) አመራር መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ነው የክልሉ መንግስት መግለጫ ያመለከተው፡፡

የኦሮሚው የሰላም ድርድር

Äthiopien OLA Friegensabkommen in Oromia
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳምስል Oromia communication

በክልሉ መንግስት በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰላማዊ መንገድ ትግልን ለመረጡ ምስጋና አለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ “የህዝቡን ጥሪ በመቀበል በዚህ የላቀ ውሳኔ ላይ የደረሰውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በራሴና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስም አመሰግናለሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ባለፉት ዓመታት ህዝባችን በቃል የማይገለጽ ከባድ መስዋእትነት ከፍሏል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ይህ ነው ለማይባል ከባድ ችግር የተዳረገውም የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ሚናቸውን መጨወት ያለባቸው ፖለቲከኞች ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ነው፡፡ በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የኦሮሞ ህዝብ ቀዬ የደም መሬት ነው የሆነው፡፡ ከባድ ጠባሳም ፈጥሯል፡፡ ስንጎዳዳ የነበርነው ወንድማማቾች ነን፡፡ ይህ ኦሮሞ ታግሎ የመጣውን የትግል ፍሬ ወደ ኋላ እንደሚመልስ ጥርጥር የለውም፡፡ ኦሮሞን ለመስበር ሌሎች እጃቸውን እንዲያስገቡም ክፍተት ፈጥሯል፡፡ አሁን ይህ ምዕራፍ መዘጋቱ የኦሮሞን እድል ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ አፈሙዝ በመዝጋት የሃሳብ ልዩነትን በፖለቲካዊ መንገድ መምራት መዘመን ነው፡፡ ዛሬ የተደረሰው ስምምነት በህዝባችን ቀዬ ሰላም ለመመለስ ትርጉሙ ትልቅ ነው፡፡ እናም ዛሬ ለዚህ ወስናችሁ የመጣሁ ጀግኖች ናችሁና እናከብራችኋለን” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ የጸጥታ ሁኔታ እና ዘላቂ መፍትሄው

Äthiopien OLA Friegensabkommen in Oromia
ምስል Oromia communication

በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ መግለጫ መሰረት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በኩል ደግሞ ስምምነቱን የፈረሙት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ከፍተኛ አመራር አቶ ሰኚ ነጋሳ ናቸው ተብሏል፡፡ አቶ ሰኚም በዚህ ወቅት ለዚህ ስምምነት ያበቃን የህዝቡ ጥሪና እየደረሰበት ያለው ስቃይ ነው ብለዋል፡፡ “ያመጣኝ ነገር ብኖር የኦሮሞ ህዝብ በየቀኑ እየሳለፈ የሚገኘው ችግርና ሰቆቃ ነው፡፡ የደሃ እናት ትልቅ ትንሹ የሚያነቡት እንባ ሰው ሆኖ መፈጠርን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሰቆቃን ይፈጥራል፡፡ በአካል ያገኘን በአካል ጠይቆናል፡፡ ያላገኘን ደግሞ እንደምታስታውሱት ትንሽ ትልቁ አደባባይ ወጥቶ ፈረስ ለጉሞ በሬም ጠምደው የጠየቁን ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የፖለቲካ አተያይ ልዩነት ልኖራችሁ ይችላል፡፡ ግን ለኛ ብላችሁ ያላችሁን ልዩነት ተቀምጣችሁ ፍቱ ማለታቸው ለሚያውቅ ትልቅ አደራ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኦሮሚያውን ግጭት ማስቆሚያ መፍትሄው ምንድነው ?

ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት ጅሬኛ ጉደታ የዛሬውን የሰላም ስምምነት በተመለከተ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የወል አመራር ምንም መረጃ እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ “የኦነግ-ኦነሰ ተወካይ ከመንግስት ጋር የተነጋገረው ምንም ነገር የለም፡፡ የወል ከፍተኛ አመራርም ስለዚህ የሚያውቀው ነገር የለም” ሲሉ ስለዛሬው ስምምነት የሚያውቁት እንደሌሌ ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለፈው ዓርብ ባወጣው ዘለግ ባለ መግለጫ እንዳስታወቀውም ከኦነሰ ወደ ሰላም ስምምነት ለመምጣት ከወሰኑት የምናደርገው ውይይት ወደ ውጤታማነት እየተሸጋገረ ነው ብሎ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ትናንት በአማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል በትጥቅ ለሚንቀሳቀሱ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ