1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ በሽታ በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ!

ረቡዕ፣ መስከረም 25 2015

በአንድ ሳምንት ብቻ 200 የወባ ታማሚዎች በምርመራ እንደሚገኙ ያስረዱት የጤና ባለሙያው ፣የባለሙያ፣ የወባ መመርመሪያ መርፌዎች፣ የወባ ማከሚያ መድኃኒቶች፣ የሙቀትና የህመም ማስታገሻ የመሳሰሉ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረቶች እንዳሉባቸው ጠቁመው እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡

https://p.dw.com/p/4HmRU
Äthiopien | Jara Flüchtlingslager
ምስል Zinabu Melese/DW

የወባ ወረርሽኝ

ከአንድ ዓመት በፊት ተፈናቅለው ሰሜን ወሎ ሀርቡ ወረዳ በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን ተናገሩ፣ የመጠለያ ጣቢያው የህክምና ባለሙያ በበሽታው የሚያዙ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል የመድሀኒትና የባለሙያ እጥረትም እንዳጋጠመ አመልክተዋል፣ የዞኑ ጤና መምሪያ በበኩሉ የባለሙያም ሆነ የመድኃኒት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብሏል፡፡

የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የወባ በሽታ እየተስፋፋ እንደሆነ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎችና ኃፊዎች ባዘጋጀው ውይይት ላይ ገልጧል፡፡ የወባ በሽታ ከታየባቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ወሎ ዞን ቆላማ አካባቢዎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በሰኔ 2014 ዓ ም የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አላማጣና አካባቢውን እንደገና በተቆጣጠረበት ወቅት ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ሀርቡ ወረዳ ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በወባ በሽታ እየታመሙ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አመልክተዋል፡፡

የጣቢያው አስተባባሪ አቶ ዝናቡ መለሰ እስካሁን ሞት ባይመዘገብም በመጠለያ ጣቢያው በርካቶች የወባ ምልክቶች እንደታዩባቸው ተናግረዋል፡፡  ከ200 በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንደታመሙ ከጤና ባለሙያዎች ሪፖርት እንደተደረገላቸው ገልጠዋል፡፡

“በአንድ ሳምንት ወደ 400 ነው የደረሰብን የወባ ምልክት፣ በወባ ቴዘው ደግሞ በ5 እና በ6 ቀን ወደ 220 በቀን እስከ 45 ሰው ማለት ነው ከዚ በፊት በ3 እና በ 4 ቀን 2 እና 3 ሰው ነበር ሪፖርቱ በወረርሽን ደረጃ ለዞኑ አሳውቀናል” ብለዋል፡፡

የመጠለያ ጣቢያው የጤና መኮንን አዳነ ጉሼ በበኩላቸው ሁሉም  የወባ ዓይነቶች በበርካታ ተፈናቃዮች በምርመራ መገኘቱን ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት፡፡

“ወርርሽኑ አለ፣ ዞኑም ይመታል፣ … በሽታውና የሚመጣው መድኃኒትጋ በጣም በሽታው አለ፣ በቀን እስከ 200፣ 300 ሰው ነው እየን ያለነው ከዚህም RDT የሚባል የወባ መመርመሪያ በዚያ ስንመረምር የጭንቅላት ወባና ቫይባክስ ዝርያዎች በብዛት በህብረተሰቡ ደም በምርመራ እያሳዩና ቋርተም የተባለውን መድኃኒት እሰጠን ነው አሁን የሚያግዘን አካል ካለ በጣም ፈልጋል ህብረተሰቡ፡፡”

በአንድ ሳምንት ብቻ 200 የወባ ታማሚዎች በምርመራ እንደሚገኙ ያስረዱት የጤና ባለሙያው ፣የባለሙያ፣ የወባ መመርመሪያ መርፌዎች፣ የወባ ማከሚያ መድኃኒቶች፣ የሙቀትና የህመም ማስታገሻ የመሳሰሉ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረቶች እንዳሉባቸው ጠቁመው እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

Äthiopien | Logo World Malaria Day
ምስል Southern Regional Health Bureau

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ሲሰተር ፈለቁ መኮንን ወቅቱ የወባ ወቅት መሆኑን በመሆኑ በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በወባ የታመሙ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንት የአካባቢ ፅዳት ሳይሰራ በመቆየቱ የወባ አስተላላፊ ትንኝ በብዛት መራባቱን ገልጠዋል፤ ሆኖም አሁን የመከላከል ስራ መሰራቱንና የባለሙያም ሆነ የመድኃኒት እገዛ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል፡፡

መምሪያ ኃላፊዋ፣  “ጃራ ሰዎቹ ወጣ ገባ የማለት ነገር ስለነበረ የመከላከል ስራው ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ወደ ኃላ ወደ ፊትም ሲሉ ስለነበረ ከዚያ አካባቢ የነበረው የመከላከል ስራ አልተሰራም ነበር ትተውትም ወጥተው ስለነበርና የወባ መድኃኒትም፣ የወባ ምርመራም ክፍያ የማይፈፀምበት ነፃ አገልግሎት ነው ሚሰጠው ከዚያ አንፃር በወባ የሚጠረጠሩ ሰዎች ወደ ህክምና ሰዳሉ፣ እዛው ክሊኒክ አለን  ሰርተናል፣ ባለሙያዎችም እዛው አሉ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው እዛው ምርመራ ይሰራል እዛው ክሊኒኩ ላይ ህክምና ይደረጋል፣ የሚያስፈልጋቸውን ግብኣት በባለሙያዎቹ ከወባ ጋር ተያይዞ ሰጥተናል፣ ከዞንም ባለሙያ መድበናል እዛው የሚከታተል፣ እለት የሚጠቀሙበትን ፍጆታቸውን እወሰድን ሲያልቅ በሶስትና አራት ቀን ነው ማስገባት የምንፈልገው፣ ለምን? ወታ ገባ የማለቱ ነገር ስላለ ብክነት ስለሚገጥመን በጣም ብዙ መድኃነት፣ ብዙ ግብዓት ወስደን እዛ አናስቀምትም፡፡” በመለት ለዶቼ ቬሌ ገልፀዋል፡፡

በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ባለፈው ኣመት በአካባቢው በነበረው ጦርነት ከአላማጣና ከአካባቢው  ከ30ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ የመጠለያ ጣቢያው አስተባባሪ አቶ ዝናቡ ተናግረዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

እሸቱ በቀለ