1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢ የወባ ወረርሽኝ በዎላይታ ዞን

ሰኞ፣ ጥር 6 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያንዣበበው የሞት ጥላ በቀላሉ የሚገፈፍ አይመስልም ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በወረዳው እየተባባሰ የመጣው የወባ ወረርሽኝ አሁን ላይ የብዙዎችን በር እያንኳኳ ፤ በርካቶችንም የአልጋ ቁራኛ እያደረገ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/4bGCj
የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝምስል pzAxe/IMAGO

በዞኑ 48 ሰዎች በወባ በሽታ መሞታቸው እየተነገረ ነዉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን  ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያንዣበበው የሞት ጥላ በቀላሉ የሚገፈፍ አይመስልም ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በወረዳው እየተባባሰ የመጣው የወባ ወረርሽኝ አሁን ላይ የብዙዎችን በር እያንኳኳ ፤ በርካቶችንም የአልጋ ቁራኛ እያደረገ ይገኛል ፡፡

አቶ ጌታሁን አላሮ በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ሼላ ሳዴ በተባለች ቀበሌ ነዋሪ ናቸው  ፡፡  አቶ ጌታሁን በቀበሌው ወላጅ አባታቸውን ጨምሮ 48 ሰዎች በወባ በሽታ መሞታቸውን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

“ አባቴ የወባ በሽታ አለብህ ተብሎ ሁለት ጊዜ ነው ሆስፒታል ያስተኛሁት “ የሚሉት አቶ ጌታሁን “ ነገር ግን አባቴ  ህክምና ቢደረግለትም ሊድን አልቻለም ፡፡ ባለፍው ታህሳስ 1 2016 ዓም ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል ፡፡ በመንደሩ ባለፍው ጥቅምት እና ታህሳስ ወር አባቴን ጨምሮ 48 ሰዎች በወባ በሽታ ሞተዋል፡፡ አሁንም ታመው የሚገኙ ሰዎች አሉ “ ብለዋል ፡፡

“ የታመመ እንጂ የሞተ የለም “

በወላይታ ዞን 23 ለወባ ተጋላጭ ወረዳዎች  መኖራቸውን የጠቀሱት የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ  ኪንዶ ዲዳዬ በተባለው ወረዳ ወባ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ለዶቼ ቬለ  አረጋግጠዋል ፡፡ በተለይም በወረዳው ሼላ ሳዴ ቀበሌ እስከ ትናንት ታመው ምርመራ ከተደረገላቸው 1 ሺህ 997 ሰዎች መካከል 1ሺህ 419ኙ የወባ በሽታ እንደተገኘባቸው ሃላፊው ተናግረዋል ፡፡ አሁን ላይ ተማሚዎቹ በወረዳው በሚገኙ ጤና ጣቢዎችና ሆስፒታሎች የፈውስ ህክምና እየተሰጣቸው እንደሚገኝ የጠቀሱት የመምሪያ ሃላፊው “ ነገር ግን በበሽታው የታመመ አንጂ የሞተ የለም “ብለዋል ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንተስኖት መልካ “በእኛ ደረጃ የገመገምነው የሞት መረጃ የለንም” ብለዋል ምስል privat

ኀሃዞቹ

ዶቼ ቬለ  በዞኑ “ በበሽታው የሞተ የለም “ የሚለውን የዞኑን ጤና መምሪያ ሃላፊ ምላሽ ለማረጋገጥ  በወረዳው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ላይ ማጣራት አድርጓል ፡፡ ከአነኝሁ ጤና ጣቢያዎች በወባ በሽታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በሳምንታዊና በወርሃዊ ሪፖርት ለዞኑ የሚገለጽ ቢሆንም ተጠያቂነት ለማስቀረት ሲባል ግን ኀሃዞችን የመሠወር ሥራ እንደሚከናወን ከውስጥ አዋቂዎች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ  ፡፡ ከአነኝሁ ጤና ጣቢያዎች በአንዱ በማገልገል ላይ የሚገኙትና ሥሜ  አይጠቀስ ያሉ የህክምና ባለሙያ “ በጤናው ዘርፍ መረጃ በየጊዜው ሪፖርት ይደረጋል ፡፡ ነገር ግን መንግሥት አሥፈላጊውን የጤና ግበዓት እያቀረበ ወረርሽኑ ለምን ተከሰተ የሚል ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል ኀሃዞች በበላይ አካላት እንዲሠወሩ ተደርጓል  “ ብለዋል ፡፡

የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት  በጉዳዩ ላይ ምን ይላል ?

በወባ ወረርሽኝ ዙሪያ በህብረተሰቡ የተነሳውና በአናንተ የተሰጠው  ምላሽ  አይጣረዝም ወይ በሚል ዶቼ ቬለ የተጠየቁት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንተስኖት መልካን ጠይቋል፡፡ “ እኛ ለማህበረሰቡ ነው የምንሠራው የሞተ ሰው ካለ አልሞተም ብለን የምንከላከልበት ምክንያት የለም “ ያሉት አቶ መንተስኖት “ ለዛም ነው ወረርሽኝ ተከስቷል ፡፡ ብዙ ሰው ታሟል ፡፡ ርብርብ እያደረግን ነው ብለን እየገለጸን ያለነው ፡፡ ነገር ግን በእኛ ደረጃ የገመገምነው የሞት መረጃ የለንም “ ብለዋል ፡፡

በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች  በወባ በሽታ እንደሚያዙ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ያወጣው ኀሃዛዊ መረጃ ያመለክታል ፡፡ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ  የአገሪቱ አካባቢዎች የወባ በሽታ ሥርጭት እያንሠራራ እንደሚገኝ የአገሪቱ የጤና ሚንስቴርት ባለስልጣናት  ሰሞኑን በአዳማ ከተማ በተካሄደው የጤና ጉባዔ ላይ መግለጻቸው ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ   

አዜብ ታደሰ 
ታምራት ዲንሳ