የወባና ሌሎች ወረርሽኞች ስጋት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2012ላለፉት ወራት የሁሉም ትኩረት ዓለምን ያስደነገጠው ድንገተኛው ኮቪድ 19 በመሆኑ ሌሎቹ ግንባር ቀደም ገዳይ የሚባሉ በሽታዎች ውስጥ ውስጡን ሲቀጣጠሉ መሰንበታቸውን የሚመለክቱ መረጃዎች መሰማት ጀምረዋል። በአማራ ክልል በ25 ወረዳዎች በተቀሰቀሰው የወባ ወረርሽኝ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተይዘዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የወባ ወረርሽኝ የሚቀሰቀስባቸው ሁለት ወቅቶች መኖራቸውን ነው ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁት ባለሙያዎች ለመረዳት የቻልነው። ከፍተኛ የወረርሽኝ ስርጭት የሚኖረው ከመስከረም እስከ ታኅሣስ ባለው ጊዜ ሲሆን፤ ከሚያዚያ እስከሰኔ ደግሞ መካከለኛ የሚባል የወረርሽኝ ስርጭት አለ። በአማራ ክልል ዘንድሮን ጨምሮ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መካከለኛ በሚባለው የወባ ወረርሽኝ ወቅት የተቀሰቀሰው ከ70 በመቶ በላይ መሆኑን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ተቋም የወባ ክፍል ባለሙያ አቶ አማረ ደስታ ገልጸውልናል።
በመላው ዓለም 5,5 ሚሊየን ገደማ ሰዎችን የለከፈው የኮሮና ተሐዋሲ ኢትዮጵያ ውስጥም የታማሚዎቹ ቁጥር ከዕለት ወደዕለት የመጨመረ መሄዱ እየተነገረ ነው። የወረርሽኙ ዓለም አቀፋዊነት ከተነገረበትና የመዛመቱ ፍጥነት ካየለበት ወቅት አንስቶ በሽታው በሀገሪቱ ትኩረትን በመሳቡ ሌሎች በሽታዎች የተዘነጉ እንዲመስሉ ማድረጉ ነው የሚነገረው። ወረርሽኙ በፈጠረው ስጋት ምክንያትም ሰዎች ወደሀኪም ቤት መሄድን የሸሹበት አጋጣሚ እንዳለም ለመረዳት ችለናል። የደቡብ ክልል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅና ካውዛ ከአንድ ወር በፊት የወረርሽኙ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልነበር ነው ያመለከቱት። ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች በወባ እና ኮሌራ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች መያዛቸው ተሰምቷል። በድሬደዋና አካባቢውም እንዲሁ የወባና የቺኩንጉኒያ ወረርሽኝ መቀስቀስ ስጋት መኖሩን ከአካባቢው ለመረዳት ችለናል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በየዓመቱ ከ200 ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎች በወባ እንደሚያልቁ ተመዝግቧል። በየሁለት ደቂቃም የአንድ ልጅ ሕይወት በወባ ሰበብ ይቀጠፋል። እንደድርጅቱ ምንም እንኳን ከጎርጎሪዮሳዊው 2000ዓ,ም ወዲህ ወባ በሚያጠቃቸው ሃገራት የሟቾች ቁጥር በጣም ቀንሶ ቢታይም ይህ ለውጥ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ለውጥ ማሳየት አቁሟል። እንደውም በአንዳንድ ሃገራት በሽታው እንደአዲስ እያንሰራራ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑንም ጠቁሟል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ