1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐርብ ኅዳር 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017

ሕጻናትን ጨምሮ የግዳጅ የውትድርና ምልመላ በኦሮሚያ ክልል፤ ምሥራቅ ወለጋ ዞን መንግሥት ትጥቅ እንዲፈቱ ያደረጋቸው የአማራ ተወላጆች የደህንነት ስጋት ላይ መውደቃቸው ተገለጠ፤፥ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ መላኳ ተዘገበ፥ ሶማሊያ ኢትዮጵያ በጁባላንድ ግዛቴ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ከሳለች ።

https://p.dw.com/p/4nrLv

 አርዕስተ ዜና

*ሶማሊያ በደቡብ ጁባ ላንድ ግዛቴ ኢትዮፕያ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ዛሬ መክሰሷን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘገበ ። ቁጥራቸው በውል ያልተገለጠ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ጊዶ ክልል ዶሎው ከተማ ውስጥ መግባታቸውን ተዘገበ ።

*በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን መንግሥት ትጥቅ እንዲፈቱ ያደረጋቸው የአማራ ተወላጆች የደህንነት ስጋት ላይ ወድቀዋል ሲል እናት ፓርቲ ገለፀ ። ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ)የሚለው እና መንግሥት ኦነግ ሸኔ ሲል የሚገልጠው ኃይል ትጥቅ እንዲፈቱ ከተደረጉ የአማራ ተወላጆች አቅራቢያ በ15 እና በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል ተብሏል ።

*በኦሮሚያ ክልል «የሰራዊቱን አሠራር እና መስፈርቶች በጣሰ ሁኔታ» ሕጻናትን ጨምሮ የግዳጅ የውትድርና ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደረገ ።

*የሶሪያ አማጺያን ሐማ እና አሌፖ ከተሞችን በቀላሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ሆምስ ከተማ ማእከል መቃረባቸው ተዘገበ ።  

ሙሉ የዜና ዘገባውን ከድምፁ ማቅቀፍ ማድመጥ ይቻላል ።

ዜናው በዝርዝር

ወለጋ፥ መንግሥት ትጥቅ እንዲፈቱ ያደረጋቸው የአማራ ተወላጆች የደህንነት ስጋት ላይ መውደቃቸው ተገለጠ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን  መንግሥት ትጥቅ እንዲፈቱ ያደረጋቸው የአማራ ተወላጆች የደህንነት ስጋት ላይ ወድቀዋል ሲል እናት ፓርቲ ገለፀ ። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት፦ በምሥራቅ ወለጋ የአማራ ተወላጆች በመንግሥት ፈቃድ የታጠቁትን መሣሪያ ሰሞኑን እንዲፈቱ ተደርገዋል ።

«በአንድ ሌሊት ሁለት መቶ ሦስት መቶ ሰው ተገድሎ የሚያድርበት አካባቢ ነው ። በ15 እና በ20 ኪሎ ሜትር ራሱን ኦነሰ የሚለው ወይንም መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው ኃይል አለ ። እና ሲነግሩሽ በአንዲት ቅጽበት የፈለጉትን አድርገው መሄድ ይችላሉ ። እስካሁን መከላከያ አለ፥ መከላከያው በማንኛው ሰአት፤ በማንኛውም ደቂቃ ከዚያ ቦታ በተንቀሳቀሰ  ጊዜ እነዚህ ሰዎች በቀላሉ የጥቃት ዒላማ ነው የሚሆኑት ።»

ነዋሪዎቹ እንዲፈቱ የተደረጉትን መሣሪያ፤ በመንግሥት ፈቃድ እና በአብዛኛው ራሳቸው ገዝተው የታጠቁት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ይህ የሆነውም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው እና መንግሥት «ኦነግ  ሸኔ» የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለያዩ ጊዜያት በነዋሪዎች ላይ ከሚፈጽመው ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል እንደነበር  አስረድረዋል ። ሆኖም ግን  ነዋሪዎቹ ሰሞኑን  ትጥቅ እንደፈቱ መደረጋቸው ዳግም ለጥቃት ያጋልጠናል የሚል የደኅንነት ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል ።

«ለማንም የሚመከረው፥ እንደ [አንድ አገረ-መንግሥት] ነኝ ለሚል አካል ምንም አይነት እዚህ ውስጥ አተካራ ከመግባት ቀድሞ የመንግሥት ሚናውን መወጣት ነው ያም የዜጎችን ወጥቶ የመግባት መብት ማስጠበቅ ነው ይኼ ከሆነ መሣሪያ አንግቶ የመዋል አባዜ ያለበት ሰው ያለ አይመስለኝም ሲያመርቱ፣ ሲያርሱ፤ ደፋ ቀና ሲሉ የሚውሉ ሰዎች ናቸው »

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ጥቃት ሲፈፀም መቆየቱን የገለፁት ኃላፊው፤ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት ሰፍሮ የሚገኝ ቢሆንም፤ ሠራዊቱ ቦታውን ለቅቆ ከወጣ ግን ተመሳሳይ ጥቃት ሊደርስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አክለዋል ።  በመሆኑም መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ኃ  ላፊነቱን እንዲወጣ እና የደህንነት ዋስትና እንደሰጥ የእናት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጠይቀዋል።

ጁባላንድ፥ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ መላኳ ተዘገበ

ሶማሊያ በደቡብ ጁባ ላንድ ግዛቴ ኢትዮጵያ ጣልቃ እየገባች ነው ስትል ዛሬ መክሰሷን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘገበ ። ቁጥራቸው በውል ያልተገለጠ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ጊዶ ክልል ዶሎው ከተማ ውስጥ መግባታቸውን የአፍሪቃ ጉዳዮችን የሚከታተለው (BBC Monitoring) ይፋ አደረገ ። ወታደሮቹ ወደተጠቀሰው የሶማሊያ አካባቢ የገቡት በሶማሊያ ፌደራል መንግስት እና በጁባላንድ ክልላዊ መንግስት መካከል አለመግባባት በተፈጠረበት ወቅት መሆኑንን «ካስሚዳ» የተባለው የዜና ድረ-ገጽ ትናንት መዘገቡን የቢቢሲ መረጃ ቁጥጥር ገልጧል ። «የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት በደርዘን በሚቆጠሩ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ጭኖ በሶማሊያ ዶሎው ግዛት ጌዶ ወረዳ ገብቷል» ሲል ዘገባው አመልክቷል። ዘገባው ይፋ የሆነው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ በታችኛው ጁባ ክልል በደቡባዊ ራስ ካምቦኒ ከተማ ከሚያደርጉት ጉብኝት ቀደም ብሎ ነው ። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ የመንግስት ኃይሎች ጋር በክልሉ ለሚወዛገቡት የጁባላንድ ክልልል ፕሬዝዳንት አህመድ ማዶቤ  «ምናልባትም ወታደራዊ ድጋፍ  ያደርጋሉ» ሲል ድረ ገጹ መዘገቡን የቢቢሲ መረጃ ቁጥጥር ጠቁሟል ። ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሚገኙ አማፂ ቡድኖችን ትደግፋለች የሚለው ወቀሳ እና የሁለቱ መንግስታት ውዝግብ ተባብሶ የቀጠለው፤ ራሷን እንደ ሀገር ከምትቆጥረው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ከምትላት የሶማሌላንድ ሪፐብሊክ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ ነው።

ሻሸመኔ፥ ሕጻናትን ጨምሮ የግዳጅ የውትድርና ምልመላ በኦሮሚያ ክልል

በኦሮሚያ ክልል «የሰራዊቱን አሠራር እና መስፈርቶች በጣሰ ሁኔታ» ሕጻናትን ጨምሮ የግዳጅ የውትድርና ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አደረገ ። ኮሚሽኑ ትናንት ይፋ ባደረገው መግለጫው፦ «ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎች በግዳጅ ስለመያዛቸው እና የተያዙትን ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደዳቸው» መረጃዎች እንደደረሱት ገልጧል ።  መረጃዎቹንም መሠረት አድርጎ ኢሰመኮ በክልሉ «ከኅዳር 4 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ» በተለያዩ አካባቢዎች ክትትል እና ምርመራ ማከናወኑን ዐሳውቋል ። አንዳንድ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ወጣቶችን ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ምልመላ በሚል ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል ። ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ በክልሉ ባለስልጣናት እና የፀጥታ ኃይሎች ሕጻናት እና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ በርካቶችን የመከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ በሚል በግዳጅ እየያዙ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል ። ይህንንም ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው ተጎጂዎች እና ምስክሮች፣ በአካል ምልከታ ካደረገባቸው የማቆያ ስፍራዎች እና ከክልሉ የፀጥታ እና አስተዳደር አካላት ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች ማረጋገጥ መቻሉን ገልጿል ። ኢሰመኮ «መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን» አሰባሰብኩባቸው ባለባቸው የተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች «የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ» በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ ሰዎችን የመከላከያ ሰራዊት በምልምል ወታደርነት ያለመቀበሉን ማወቁንም ገልጧል ።  ኢሰመኮ፦ «ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ ለምልመላ በሚል ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ ላይ የተሳተፉ እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁ፣ የተቀበሉ እና ይህንኑ የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ» ያላቸው አካላት ላይ «ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተከናውኖ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ» አሳስቧል ። “በቀጣይ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚካሔዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች ሰራዊቱ ባስቀመጠው አሠራር እና መስፈርት መሠረት በፈቃደኛነት ላይ ብቻ ተመሥርተው መከናወናቸውን ሊያረጋገጥ ይገባል” ብሏል ።

ቴክሳስ፥ ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች አደጋ ጥፋተኛነቱን የሚቀበልበት ስምምነት በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ

የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ የ346 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው የ737 ማክስ አውሮፕላኖች የመከስከስ አደጋ ጥፋተኛነቱን ተቀብሎ የሚጣልበትን ቅጣት ለመክፈል የሚያስችለው ስምምነት ዛሬ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ ። በስምምነቱ መሠረት፦ ቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖቹ ኢንዶኔዢያ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ከመከስከሳቸው በፊት የአሜሪካ መንግሥት ተቆጣጣሪዎችን ስለአውሮፕላኑ ደሕንነት በማሳሳት ጥፋተኛነቱን ይቀበል ነበር ተብሏል ። ቦይንግ በፍርድ ቤት ውሳኔው ወዲያው አስተያየት አለመስጠቱ ተዘግቧል ። በአውሮፕላኖቹ አደጋዎች ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦች ስምምነቱ ተቀባይነት የነበረው መሆኑን ገልጠው ነበር ሲሉ የዜና ምንጮች ዘግበዋል ።   በቴክሳስ የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ዳኛ የሆኑት እና ለወግ አጥባቂዎች እንደሚያደሉ የሚነገርላቸው ሪድ ኦኮኖር ስምምነቱን ውድቅ ያደረጉት በማመልከቻው ላይ አንዲት አረፍተ ነገር መዝዘው እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል ። ዳኛው ለአውሮፕላኖቹ ገለልተኛ አጣሪን በመምረጥ ረገድ ክፍተት አለ ሲሉ ስምምነቱን ውድቅ ማድረጋቸው ተዘግቧል ። ቦይንግ እና የዩናይትድ ስቴትስ ፍትሕ መሥሪያ ቤት አቤት ለማለት 30 ቀናት እንደተሰጣቸውም ታውቋል ። ከአምስት ዓመታት በፊት  ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በረራ ከጀመረ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጃቫ ባሕር ላይ ተከስክሶ 189 ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል ። 737 ማክስ አውሮፕላኖች በጥቂት ወራት ልዩነቶች ኢንዶኔዢያ እና ኢትዮጵያ ውስጥም ተከስክሰው በአጠቃላይ 346 ሰዎች ለሞት ተዳርገውም ነበር ።

አክራ፥ ለቅዳሜው የጋና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ቅስቀሳው ዛሬ ተጠናቀቀ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋናውያን ነገ የሚሳተፉበት የፕሬዚደንት ምርጫ ቅስቀሳ ዛሬ ተጠናቀቀ ። ጋናውያን ቀጣዩን የሀገራቸውን ፕሬዚደንት ለመምረጥ ቅዳሜ ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የፍጆታ እቃዎች ዋጋ እጅግ መናር እና ሕገወጥ የወርቅ ማእድን ቁፋሮ ጉዳዮች የምርጫ ዘመቻው ዐበይት ትኩረቶች ነበሩ ።  የጋና መንግሥት ገዢው ፓርቲ እና የተቃዋሚ ተወካዮች በከበሮ፤ በሞተር ብስክሌት እና በተሽከርካሪ ጥሩምባዎች ታጅበው የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ዛሬ አከናውነዋል ።  የጋና ምርጫ በታሪክ በዋናነት የሁለት ሰዎች ፉክክር ሲሆን፤ በዘንድሮው ምርጫ 12 እጩዎች ይወዳደራሉ ። እንደተለመደውም ዋነኛ ሁለት ተፎካካሪዎች የገዢው አዲስ ጀግኖች ፓርቲ  (NPP)  ምክትል ፕሬዚደንት ማሐሙዱ ባሙዋሚ እና የዋነኛ ተቃዋሚው ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ምክር ቤት (NDC) ተወካይ የቀድሞው  ፕሬዚደንት ጆን ማሐማ መካከል ነው ።

ደማስቆስ፥ የሶሪያ አማጺያን ወደተለያዩ ከተሞች እየገሰገሱ ነው

የሶሪያ አማጺያን ሐማ እና አሌፖ ከተሞችን በቀላሉ ከተቆጣጠሩ በኋላ ወደ ሆምስ ከተማ ማእከል መቃረባቸው ተዘገበ ።  በርካታ ነዋሪዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ ከተሞች እየሸሹ ነው ። ሐያት ጣህሪር ኧል-ሻም በሚባለው (HTS) ጂሐዲስት ቡድን የሚመሩ አማጺያን ወደ ሆምስ ከተማ አማካይ እየገሰገሱ መሆናቸውን ብሪታንያ የሚገኘው እና ጦርነትን የሚከታተለው የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ተመልካች ዐሳውቋል ። የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆስን በምታገናኘው ሆምስ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አማጺያኑ እንደሚገኙም አክሏል ። አማጺያኑ ፕሬዚደንት ባሽር ኧል አሳድ ወደሚገኙባት የደማስቆስ ከተማ እንደሚገሰግሱም ዝተዋል ። ሐማ ከተማ የሚገኙት አማጺያን ላይ የሶሪያ እና የሩስያ ጦር ጄቶች ዛሬ ድብደባ መፈጸማቸው ተገልጧል ። አማጺያኑ ግባቸው የሶሪያ ፕሬዚደንትን መገልበጥ መሆኑን የአማጺያኑ መሪ አቡ ሞሐመድ ኧል-ሻም ዐሳውቀዋል ።  ፕሬዚደንቱ በኢራን እና በሩስያ ይደገፋሉ ። የቱርክ ፕሬዚደንት ራቺፕ ጣይብ ኤርዶሐን የአማጺያኑ ግስጋሴ የቱርክ ፍላጎት ባይሆንም፤ ሰላማዊ ዜጎችን ሳይጎዱ መገስገሳቸውን በመልካም እንደሚቀበሉት ዐሳውቀዋል ። አማጺያኑ ሰሜን ሶሪያ ውስጥ ጥቃት የጀመሩት በእሥራኤል እና በሊባኖሱ ታጣቂ ሒዝቦላህ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን በጀመረበት የመጀመሪያ ቀን ነው ።   

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።