በሱዳን በድሮን ጥቃት 3 ስቪሎች መገደላቸውንና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች በምዕራብ ሱዳን ፈጸሙት በተባለ የድሮን ጥቃት 3 ስቪሎች መገደላቸውንና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን ተሰማ።
አንድ በአካባቢው ዕርዳታ የሚሰጥ ግብረሰናይ ድርጅትን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደዘገበው የሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ የሆነችው አል-ፋሺር ትላን ሌሊት በከባድ ፍንዳታ ስትናወጥ አድራለች። ከተማዋ ከአለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊ ዕመቃ ሥር መሆኗን ዘገባዎች ያመላክታሉ። ከተማዋን ተቆጣጥረው እንደመቆናጠጫነት ለመጠቀም ሁለቱም ሃይሎች በየጊዜው ከባድ ውግያዎች እያካሄዱ እንደሆነ ይታወቃል።
ዳርፉርን ሙሉለሙሉ በሚባል መልኩ፤ ደቡብ ኮርዶፋንና ማዕከላዊ ሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ጦር ቁጥጥር ሥር ያሉ ሲሆን፤ የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክርቤት ጦር ደግሞ ምስራቃዊና ሰሜናዊ የሐገሪቱ ክፍል እንደተቆጣጠረ ዜናው አክሏል።
ያለውጤት የተበተነው ድርድር
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ርዋንዳ መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ዛሬ ያለውጤት ተበተነ። በአንጎላ ፕረዚደንት ጆኦዎ ሎሬንሶ እና የአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለውጤት የተበተነው ሩዋንዳ፤ የኮንጎን መንግስት እሱን ነፍጥ አንግበው ከሚወጉት MI 23 ከተባሉ ታጣቂዎች ቀጥተኛ ውይይት እንዲያደርግ ቅድመሁኔታ በማስቀመጧ ነው ተብሏል። የኮንጎን ምዕራባዊ ግዛትን የተቆጣጠሩት የMI 23 ታጣቂዎች በሩዋንዳ ይደገፋሉ ስትል ኮንጎ ትወቅሳለች።
በአንጎላ ተጀምሮ ዛሬ ያለውጤት በተበተነው ድርድር የሩዋንዳው ፕረዚደንት ፖል ካጋሜና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕረዚደንት ፍሊፕ ቲሺሴኬዲ ተሳትፈዋል።
ድርድሩ ከ2021 ጀምሮ በታጣቂዎቹና በኮንጎ መንግስት መካከል የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፤ የአንጎላ ፕረዚደንት የሕዝብ ግኑኝነት ሐላፊ ማርዮ ዬርግ ለጋዜጠኞች « ውይይቱ ተስፋ ከተጣለበት በተጻራሪ ወደፊት መሄድ አልቻለም» ብለዋል።
የኮንጎ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው «ውይይቱ ያለውጤት የተበተነው ሩዋንዳ፤ የኮንጎ መንግስት እሷ ከምትረዳቸውና ምዕራብ ኮንጎን ከተቆጣጠሩት የMI 23 ታጣቂዎች ጋር የቀጥታ ውይይት እንድናደርግ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጧ ነው» ብለዋል።
የሩዋንዳ የውጭጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ፤ በኮንጎ መንግስት በኩል ከአማጽያኑ ጋር በጊዜ ገደብ በታጠረ ሁኔታ ለመነጋገር ቁርጠኝት የለም ሲል ወቅሷል። የዜናው ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
ከ7,500 የሚበልጡ ሶሪያውያን ስደተኞች ከቱርክ ወደሐገራቸው መግባታቸውን
የበሽር አልአሳድ መንግስት ከወደቀ ጊዜ አንስቶ ከ7,500 የሚበልጡ ሶሪያውያን ስደተኞች ከቱርክ ወደሐገራቸው መግባታቸውን የቱርክ የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ።
የቱርክ የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዬርሊካያ በኤክስ ገጻቸው የጻፉትን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) እንደዘገበው እስከአለፈው አርብ ድረስ በቀን በአማካይ 1,000 የሶሪያ ስደተኞች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን በበኩሉ በአለፈው አርብ ብቻ የቱርክ ድንበርን አቋርጠው ወደሐገራቸው የሚመለሱ 3,000 ሶርያውያን ስደተኞች መመዝገቡን አስታውቋል።
እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011 በሶሪያ የእርስበእርስ ጦርነት ከተጀመረበት ወዲህ ቱርክ ወደ 3 ሚልዮን የሚሆኑ ሶርያውያን ስደተኞችን መቀበሏን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሶሪያ ስደተኞችን በመቀበል ቀዳሚ ሐገር ያደርጋታል።
በጦርነቱ ምክንያት ከተፈናቀሉ ሶሪያውያን አብዛኛዎቹ ወደሐገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም የደህንነታቸው እና በሐገሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ውድቀት እንደሚያሳስባቸው ዜናው አክሏል።
ቱርክ የበሽር አልአሳድን መንግስት ለገረሰሱት አማጽያን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነች
ቱርክ የበሽር አልአሳድን መንግስት ለገረሰሱት አማጽያን ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነች አስታወቀች። የቱርክ የመከላከያ ሚኒስትር ዛሬ እንዳሉት ሐገራቸው ለአዲሱ መንግስት አስፈላጊ ከሆነ ወታደራዊ ድጋፍ ታደርጋለች።
የመከላከያሚኒስትሩ ያሳር ጉለር ለቱርኩ የዜና አገልግሎት አናዶል በሰጡት መግለጫ፤ ሐገራቸው ከብዙ ሐገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነት እንዳላት ጠቅሰው አዲሱ የሶሪያ መንግስት ጥያቄ ካቀረበ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ነው ያሉት።
ጉለር አያይዘውም አዲሱ መንግስት ምን ማድረግ እንደሚፈልግ መመልከት ያስፈልጋል፤ እድሉ እንዲሰጠው አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን ብለዋል።
በዚህ አዲስ ምዕራፍ በሶሪያ የሚገኙ የኩርድ አማጽያን አሁን ይሁን በሚመጡት ጊዚያት መደምሰሳቸው አይቀርም ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ እኛም ሆነ አዲሱ የሶሪያ አስተዳደር ይህ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል።
በመጨረሻም አዲሱ አስተዳደር ሁሉንም መንግስታዊ መዋቅሮች፣ የተባበሩት መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንዲያከብር ጥሪ አድርገዋል።
ጀርመን የሰሜን ጦር ቃልኪዳን አባልነቷን ልታስብበት ትችላለች መባሉን
አማራጭ ለጀርመን በጀርመንኛ ምህጻሩ AFD እየተባለ የሚጠራው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ጀርመን የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ጥምረት አባልነቷን በተመለከተ ልታስብበት እንደምትችል አስታወቀ። የፓርቲው ምክትል መሪ ዛሬ እንዳሉ በአሜሪካ የሚመራው ኔቶ ሩስያን ጨምሮ የአውሮፓ ሐገራት ፍላጎት ግምት ውስጥ አያስገባም ሲሉ ወቅሰዋል።
ቲኖ ሽሩፓላ «ጀርመን ዕለታዊ» ለተባለ የጀርመን ጋዜጣ ያሉትን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደዘገበው «አውሮፓ የአሜሪካን ፍላጎትን ለመተግበር እየተገደደች ነው፤ ይህን አንቀበልም» ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ኔቶ አባል ሐገራቱን እየታደገ አደለም ያሉት ምክትል መሪው፤ ኔቶ የሩስያን ጨምሮ የመላው የጥምረቱ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሐገራት ፍላጎት መቀበል አለበት ብለዋል።
ኔቶ ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን ጀርመን ይህ ጥምረት ለኛ ጠቀሚነቱ ምንድነው የሚለውን ዳግመግምት ልታደርግ ትችላለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በአለፈው ሳምንት ተመራጩ የአሜሪካ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አባል ሐገራት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ የማይፈጽሙ ከሆነ ሐገራቸው ከኔቶ ለመውጣት ልታስብበት እንደምትችል ገልጸው እንደነበረ ይታወሳል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ