1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታህሳስ 12 ቀን 2017 የዓለም ዜና

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄርቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12 2017

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፋኖ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አከባቢ ዕዝ እንዲመሰርቱ መንግስት ድጋፍ አድርጓል ሲል ከሰሰ፡፡ በጀርመን በደረሰው ጥቃት 5ሞቱ ከ200 በላይ ቆሰሉ

https://p.dw.com/p/4oT0C

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፋኖ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አከባቢ ዕዝ እንዲመሰርቱ መንግስት ድጋፍ አድርጓል ሲል ከሰሰ፡፡
«ሰሞኑ ፋኖ ብሎ ራሱን የሚጠራ ኃይል የወለጋ ዕዝ ብሎ ኃይሉን ማጠናከሩን  ንጉሴ ዋለልኝ በተባለ ሰው መግለጫ ሲሰጥ ተመልክቷል» ያለው ኦነግ፤ የፋኖ ታጣቂዎች በአከባቢው እንዲጠናከሩ በተለያዩ ጊዜያት በፌዴራል መንግስት እና በሁለቱ ክልሎች መንግስታት ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል ብሏል፡፡ 
በዚህ ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ፤ ከዚህ በፊት በተለይም ከጎርጎሳውያኑ 2019 ጀምሮ የፌዴራል መንግስት ብሎም የኦሮሚያ እና አማራ ክልል መንግስታት ለታጣቂዎቹ ተደጋጋሚ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁንም ድረስ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለታጣቂዎቹ ድጋፍ ያደርጋል ሲል መግለጫ ያወጣው ኦነግ፤ “ይህ የተደራጀ” ያለው “የፋኖ ታጣቂ” የኦሮሞ ህዝብን በቀዬው መረጋጋት አሰጥቶታል ሲል ከሷልም፡፡ መንግስት ከፋኖ ጋር እየተዋጋ እንዴት የፋኖ ኃይልን በኦሮሚያ ሊያደራጅ ይችላል ተብለው የተጠየቁት የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ይህን መልሰዋል፡፡ 
 የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዮም ጌቱ በዚህ ላይ የመንግስት አስተያየት ለማካተት ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን እና ለፌዴራል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ስልክ ደውሎ ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሻቸውን ማካተት እንዳልቻለ ዘግቧል።


የፈረንሳዩ ፕረዚዳን የጅቡቲ ጉብኝት

በአፍሪካ የወታደራዊ ሰፈር መቆናጠጫ መሬት እያጣች የመጣችው ፈረንሳይ በጂቡቲ ያላትን የጦር ሰፈር ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታውቃለች። የፈረንሳዩ ፕረዚደንት ማክሮን ዛሬ በጅቡቲ ባደረጉት ጉብኝት ከጅቡቲው ፕረዚደንት ኢስማኢል ጉሌህ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን እዛው የሚገኘውን የሃገሪቱን የጦር ሰፈርም ጎብኝተዋል።
ማክሮን ከፕረዚደንት ኢስማዒል ጉሌህ በነበራቸው ቆይታ ጅቡቲ የሚገኘው የፈረንሳይ ጦር ሰፈር የኢንዶፓስፊክ የንግድ ግኑኝነት መስመር ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ፈረንሳይ በኢንዶ ፓስፊክ ያላትን ስትራተጂያዊ ጥቅም በጅቡቲ ካለው የጦር ሰፈሯ ውጭ የማይታሰብ እንደሆነም አክለዋል። ፈረንሳይ ጅቡቲ በሚገኘው የጦር ሰፈሯ 1,500 ወታደሮች ያላት መሆኑን ይታወቃል።
ፈረንሳይ፤ በማሊ፣ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ የነበራት ጦር እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2022 እና 23 በየሃገራቱ ሥልጣን በተቆናጠጡ ወታደራዊ ሁንታዎች የፈረንሳይ ወታደሮች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው ይታወቃል። በቻድ ያለው ወታደራዊ ሁንታም ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የነበረውን  ወታደራዊ ግኑኝነት ማቋረጡን ተከትሎ የፈረንሳይ ወታደሮች በቅርብ ሳምንታት ሐገሪቱን ለቀው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ፈረንሳይ በአፍሪካ ያላትን ወታደራዊ የመቆናጠጫ ቦታ ሙሉ በሙሉ ላለማጣት ከጅቡቲ ጋር ያላትን ግኑኝነት ማጠናከር እንደምትፈልግ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በጋዛ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 45, 230 ገደማ መድረሱን

ከአስራ አራት ወራት በላይ ባስቆቸረው የጋዛ ጦርነት በእስራኤል ጥቃት የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር ወደ 45,230 ግድም መድረሱን የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ባለፉት 24 ሰዓታት 21 ሰዎች መገደላቸውንም አክሏል። የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ በጋዛ የንጹሃን ሕጻናት መገደልን አውግዘዋል።
እስራኤል ትናንት በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 7 ህጻናት የሚገኙባቸው 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውን የጋዛ የስቪል መከላከያ የተባለ ተቋም አስታውቋል። ይህን ሪፖርት ተከትሎ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ እስራኤል በህጻናት ላይ ትፈጽመዋለች ያሉትን ጥቃት አውግዘዋል። 
የጋዛ የዜና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ባዋጣው መግለጫም በአለፉት 24 ሰአታት 21 ስቪል ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ብሏል። ከ14 ወራት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት በእስራኤል ጥቃት የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር ወደ 45,230 ግድም፤ የቆሰሉት ደግሞ 107,573 መድረሱን አስታውቋል ሲል የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።

በጀርመን በደረሰው ጥቃት 5ሞቱ ከ200 በላይ ቆሰሉ

በጀርመን ማግድቡርግ ከተማ በገና ገበያ ላይ በነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ላይ አንድ ግለሰብ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይቆስለዋል። በጥቃቱ የተጠረጠረ አንድ ሳውዲአደቢያዊ ሀኪም በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ጀርመኖች የገና በዓል ከመድረሱ አንድ ወር ገደማ ሲቀረው በገና ዛፎችና መብራቶች ባሸበረቁ አደባባዮች «ግሉቫይን» እየተባለ የሚጠራውን ለብ ያለ ባሕላዊ የወይን መጠጥና ባሕላዊ ምግቦች እየተጠቀሙ በየምሽቱ መዝናናት የተለመደ ባሕላዊ እሴታቸው እንደሆነ ይታወቃል። በዘንድሮ የገና አከባበር ድንገተኛ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የጀርመን ፖሊስ ቀደም ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበረ። ትላንስ ምሽት ከበርሊን በስተደቡብ ምስራቅ በምትገኘው ማግድቡርግ ከተማ የገና በዓል በማክበር ላይ በነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ላይ አንድ ግለሰብ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎች ሲሞቱ ከ 200 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ከቆሰሉት ውስጥ 41ዱ ክፉኛ መጎዳታቸውንም ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ፖሊስ በጥቃቱ የጠረጠረውን የ50 ዓመቱ ሳውዲአረቢያዊ ሐኪም በቁጥጥር ሥር አውሏል። ይህ የሥነአእምሮ ሕክምና ባለሙያ የሆነው ሳውዲአረቢያዊ እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2006 ጀምሮ በጀርመን ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ይኖር እንደነበር ፖሊስ አክሏል። ይሁንና ድርጊቱ ከጽንፈኛ የፖለቲካ አልያም የሃይማኖት እሳቤ የመነጨ ይሁን አይሁን ለመናገር ጊዜው እንዳልሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጉዳት የደረሰበትን ቦታ የጎበኙ ሲሆን የሐዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ሾልስ በመልዕክታቸው ይህን ጭካኔ የተሞላበት ያሉትን ድርጊት አውግዘው ህጉ የሚፈቅድልንን ሃይል ተጠቅመን ለጥቃቱ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል።  ጀርመኖች በአንድነት እንዲቆሙም ጥሪ አስተላልፏል።
ጥቃት የፈጸመው የሥነአዕምሩ ሐኪሙ የእስልምና ጠል መሆኑን የጀርመን የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር አስታውቀዋል። የተለያዩ የዜና ምንጮች ደግሞ ተጠርጣሪው በግል የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ገጹ ቀደም ሲል የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ እንደነበረ መግለጹን፤ የእስልምና ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽ ይዘት ያላቸው መልእክቶች ያስተላልፍ እንደነበረም ዘግበዋል።
 የዛሬ 8 ዓመት በተመሳሳይ በጀርመኖች ባሕላዊ የገና ገበያ ላይ በአንድ ቱኒዝያዊ በተፈጸመ የመኪና ጥቃት 13 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የጀርመን የእግር ኳስ ማህበር በበኩሉ በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ እንዲጀመሩ አዟል። የዜናዎቹ ምንጮች የጀርመን ዜና አገልግሎትና (DPA) እና አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ናቸው።

ሩስያ የዩክሬይን አንድ ከተማ መቆጣጠሯን

ሩስያ በምስራቅ የዩክሬይን ግዛት የምትገኝ አንድ የዩክሬይን ከተማ መቆጣጠሯን የሐገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከተማዋ ቁልፍ ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዳላትም ገልጿል።
የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባሰራጨው መግለጫ የኢንዳስትሪ ዞን በሆነችው የኩራኮቭ ግዛት8 ኪሎሜትር ርቃ  የምትገኘውን ኮስትያኖፖለስክ ከተማ «ነጻ አውጥተናል» ማለቱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። በዚህ ጉዳይ ከዩክሬይን በኩል የተባለ ነገር የለም።
ሩስያ በትላንትናው ዕለትም በክየቭ ላይ በወሰደችው የሚሳይል ጥቃት 1 ሰው ሲሞት 12 መቁሰላቸውን ይታወሳል። የሚሳይል ጥቃቱ በስቪሎች መኖሪያ ቤቶችና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋም ይዞታ የሆኑ ህንጻዎች ላይ ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።