የባህላዊ ሕጉ የዕውቅና ምስክር ወረቀት
የዒሳ ማህበረሰብ ባሕላዊ ሕግ በዩኒስኮ ዕውቅና አግኝቶ የተመዘገበበትን ሰርተፍኬት የጎሳው ዑጋዝ ተረከቡ። በሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሀገር ሲመለስ የማህበረሰቡ መሪ የሆኑት ዑጋዝ መቀመጫ በሆነችው ድሬደዋ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለት ቅርሱ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበበትን ሰርተፍኬት ለዑጋዙ አስረክበዋል ሲል መሳይ ተክሉ ከድሬዳዋ ዘግቧል። ከሳምንታት በፊት በፓራጓይ 19 ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን ያካሄደው አለማቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በእንግሊዘኛ ምዕፃሩ - UNESCO ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በጋራ ላቀረቡት የሂሳ ማህበረሰብ ሀብት የሆነው ባሕላዊ ሕግ ቅርስ ይመዝገብልን ጥያቄ አዎንታዊ ውሳኔ ሰጥቷል። በመድረኩ በሶስቱ ሀገራት የሚኖረው የሶማሌ ዒሳ ማህበረሰብ ሀብት የሆነው ያልተፃፈው ባህላዊ ህግ « ሄር ሂሴ» በሰው ልጆች የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያደረገው ውሳኔ በየሀገራቱ የሚኖረውን የሂሳ ማህበረሰብ በእጅጉ ማስደሰቱን ታውቋል።
በህገወጥ የወርቅ ቁፋሮ የተጠረጠሩ ቻይናውያን
ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ በሕገወጥ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ተጠርጥረው ታስረው ከነበሩ 17 ቻይናውያን 14ቱን መፍታቷን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ። ግለሰቦቹ ያለሕጋዊ ፍቃድና አስፈላጊ ሓጋዊ ሰነዶች ማዕድን ሲያወጡ መታሰራቸውን ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።
በደቡባዊ የሃገሪቱ ግዛት የምትገኘው የኪቮ ገዢ፤ ዣን ዣክ ፑሩሲ ሳዲኪ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ «ቻይናውያኑ ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበት 10 ሚልዮን ዶላር ግብር አለባቸው። ይሁንና የመፈታታቸው ዜና ስሰማ አስደንጋጭ ሆኖብኛል» ሲሉ ተደምጠዋል።
በአካባቢው 60 የሚሆኑ ቻይናውያን በማዕድን ቁፋሮ ተሰማርተው እንደሚገኙም ታውቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በኪንሻሳ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ሐሳብ ከመስጠት ተቆጥቧል ሲል የዘገበው ሮይተርስ የዜና ወኪል ነው።
የአዘርባጃን አውሮፕላን ተከስክሶ ከ30 በላይ ተሳፋሪዎች መሞታቸውን
67 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የአዘርባጃን አየርመንገድ አውሮፕላን ዛሬ በመከስከሱ ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተሰማ። ከተሳፋሪዎቹ ቢያንስ 32 ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል። አንዳንድ የዜና ምንጮች ደግሞ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ቁጥር 29 እንደሆነ ዘግበዋል።
የካዛኪስታን የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር ፤ አውሮፕላኑ ከአዘርባጃኗ የባኩ ከተማ ወደ ሩስያዋ የግሮዥኒ ከተማ ሲጓዝ የነበረ ቢሆንም አክታው በተባለች የካዛኪስታን ከተማ አቅራቢያ ድንገት ሊያርፍ ሲሞክር መከስከሱን አስታውቋል።
በተሳፋሪዎች የተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረጹ ቪድዮዎች አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት ከክንፎቹ ጥቁር ጭስ ይቦን እንደነበር ማመላከታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሉት ዘግቧል።
ከተሳፋሪዎቹ 42ቱ አዘርባጃናውያን፣ 16ቱ ሩስያውያን፤ 6ቱ ካዛኪስታናውያን ቀሪ 5ቱ ደግሞ የአውሮፕላኑ የበረራ ሰራተኞች መሆናቸውን ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። አዘርባጃን የሞቱትን ዜጎቿን ለማስታወስ የአንድ ቀን ሐዘን አውጃለች።
የአዘርባጃን አየርመንገድ የአደጋው መንስኤ እስከሚጣራ ድረስ ከባኩ ወደሩስያ የሚደረጉ በረራዎችን ለጊዜው ማቆሙንም ታውቋል።
ሐዘን ያጠላበት የገና በዓል በጀርመን
ጀርመናውያን በማግድቡርግ በደረሰ አደጋ ምክንያት ሐዘን ያጠላበት የገና በዓላ እያከበሩ ነው። የጀርመን ፕረዚደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በማግድቡርግ የደረሰው ጥቃት አሰቃቂና የሚያሰቃይ ቢሆን ጀርመናውያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፏል።
ሽታይን ማየር በመልዕክታቸው ጥላቻና ዓመጻ ቦታ ሊሰጣቸው እንደማይገባም አሳስበዋል። በፖለቲካ፣በንግድና ፍትሃዊነት ላይ ብዙ ቅሬታዎች አሉ ያሉት ሽታይን ማየር በአገራችን ያለው ሁኔታ ጠጣር አንዳንዴም በዕለተ ዕለት ኑሮአችን ለግጭት የሚዳርግ እየሆነ ነው ብለዋል። «ልንጋፈጣቸው የሚገቡ ብዙ ፈተናዎች አሉ፤ እየተከሰተ ስላለው ነገር በቅንነት መነጋገር አለብን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአስቸኳይ መደረግ ስላለበት ነገር መነጋገር አለብን» ሲሉም አክለዋል። ፕረዚደንት ሽታይን ማየር አያይዘውም «በአደጋው ወዳጆቻችሁን ያጣችሁ ሰዎች ትርጉም ያላቸው የማጽናኛ ቃላት እንደማታገኙ አውቃለሁ፤ ይሁንና ብቻችሁን አደላችሁም፤ መላው የአገራችን ሕዝብ የሐዘናችሁ ተጋሪ መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ» ብለዋል።
በሌላ ዜና በደቡብ ጀርመን በምትገኛ የሙኒክ ከተማ ዛሬ ባጋጠመ የእሳት አደጋ በ15 ሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። እሳቱ የተነሳው በአንድ የእንክብካቤ ማዕከል ሲሆን የአደጋው መንስኤ እስከ አሁን ግልጽ አይደለም ነው የተባለው።
እሳቱ ከመዛመቱ በፊት 120 የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተሰማርተው 60 ሰዎችን ከማእከሉ ያስወጡ ሲሆን ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎችም በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው የሙኒክ ቴክኒካዊ ዩንቨርስቲ ህንጻ በጊዚያዊነት እንዲቆዩ አድርገዋል ሲል የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘግቧል።
በሌላ ዙና የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ በመላው ዓለም የሚገኙ የጦር መሳሪያዎች ላንቃቸው ሊዘጋ ይገባል አሉ። ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ የገና በዓል አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በሱዳን፣ በመካከለኛ ምስራቅ፣ በዩክሬይንና ሌሎች ጦርነት ያለባቸው ሐገራት ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል ሲል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በጀርመን የሚኖሩ ሶሪያውያን ወደሃገራቸው እንዲመለሱ መጠየቁን
የቀድሞው የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትርና የሊበራል ነጻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጀርመንኛ ምህጻሩ FDP መሪ ክርስትያን ሊንደርነር ሶርያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጠየቁ።
ሊንደርነር፤ ለጀርመን ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለምልልስ በእርስበእርስ ጦርነት ተሰደው ወደ ጀርመን የመጡ ሶሪያውያን ስደተኞች ወደ ሐገራቸው የመመለስ ጉዳይ ሕግ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
ሶሪያውያኑ በጀርመን የመቆየት ዕድላቸው በግልጽ መመዘኛዎች የተመሰረተ መሆን አለበት ያሉት ሊንደርነር አክለውም ከማሕበራዊ ድጎማ ነጻ ወጥተው እራሳቸውን የቻሉ፣ ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት ያልፈጸሙ እና ሌሎች የስደተኝነት ሕጉ የሚያሟሉት ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ማመልከት እንደሚችሉ ጠቅሰዋል። እንደ አስተናጋጅ አገር የመወሰን ስልጣን አለን ሲሉ በማከል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2015 በሶሪያ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ወደ 975,000 ሶሪያውያን ወደ ጀርመን ተሰደው እንደሚኖሩ የጀርመን የሐገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ሩስያ የዩክሬይን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አወደመች
ሩስያ «ለወታደራዊ ፋብሪካዎች የሃይል ምንጭ ነበር» ያለችውን የዩክሬይን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማውደሟን አስታወቀች። በምስራቅ ዩክሬይን የምትገኘውን ቪድሮድዥንያ የተባለች መንደር መቆጣጠሯንም አክላለች።
የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ያሰራጨውን መግለጫ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ጦሩ ቦታው በግልጽ ባልጠቀሰውና «ለክዬቭ ወታደራዊ ፋብሪካዎች የሃይል አቅራቢ ነበር» ባለው መሰረተ ልማት ላይ፤ «ከፍተኛ» ያለውን ጥቃት ማድረሱን ገልጿል። የዩክሬይኑ ፕሬዚደንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ጥቃቱ መፈጸመን አምነዋል። ዘለንስኪ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሩስያ የሐገራቸውን የኢሌክትሪክ ሃይል መሰረተልማትና የተወሰኑ ከተሞችን በሚሳይሎችና ድሮኖች ማጥቃቷን አስታውቀዋል። በጥቃቱ በካርካዬቭ አንድ ሰው ሲገደል ቢያንስ 6 መቁሰላቸውን በመግለፅም በገና ዋዜማ የተፈጸመ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሲሉ አውግዘዋል።
በሌላ ዜና ዩክሬይን በሩስያው የክርሱክ ግዛት በፈጸመችው የከባድ መሳሪያ ድብደባ 4 ሩስያውያን ስቪሎች መሞታቸውንና 5 መቁሰላቸውን ሩስያ አስታውቃለች። በጥቃቱ የስቪሎች መኖሪያ የሆኑ ሕንጻዎችም ወድመዋል ነው የተባለው።