1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬይን እና የሩስያ ፍጥጫ

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2011

የሩስያ የዩክሬይንን መርከቦች ማገትዋን ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለዉ ፍጥቻ ተካርዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖርሼንኮ ፍጥጫዉን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

https://p.dw.com/p/38wRp
Ukraine Kiew Präsident Petro Poroschenko
ምስል Reuters/Handout Ukrainian Presidential Press Service/M. Markiv

ሩስያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአከራካሪው የክሬሚያ አካባቢ በሚገኘው ባህር ተኩስ ከፍታ ሶስት የዩክሬይን ባህር ኃይል መርከቦችን ከያዘች በኋላ ዩክሬይን ጦሯን በተጠንቀቅ አቁማለች። የዩክሬይን ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ ዛሬ ለተሰበሰበው የሀገራቸው ብሔራዊ ምክር ቤት እንዳስታወቁት፣ ሩስያ ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ የዩክሬይን ጦር ኃይል አባላት በኃይል በመያዟ የሩስያ ባለስልጣናት እንድትለቋቸው አሳስበዋል።

« የባህር ኃይል አባላቱን ከነመርከቦቻቸው ባስቸኳይ ለዩክሬይን እንድታስረክብ እንጠይቃለን።  በአዞቭ ባህር እና በሌሎች አካባቢዎች የሚታየውን ውዝግብም እንድታበርድ እናሳስባለን። ለዚህ ፈጣን ምላሽ እጠብቃለሁ። »

የሩስያ የክሬምለን ቤተመንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ግን ፣ የዩክሬይን መርከቦች ሩስያ ባህር ክልል ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ መግባታቸውን እና የሩስያ ጠረፍ ጠባቂዎች ሊያነጋግሯቸው ያደረጉትን ሙከራ ችላ ማለታቸውን ተናግረዋል። የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ዶናልድ ቱስክ ሩስያ ወስዳዋለች ያሉትን የኃይል ተግባር በጥብቅ አውግዘው ፣ ሩስያ የዩክሬይንን መርከቦች ከነባህር ኃይል አባላቱ እንድትለቅ ጠይቀዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ