የዩጋንዳ ወታደሮች በኮንጎ የመንገድ ግንባታ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27 2015በጎርጎሪዮሳዊው 2021 ኅዳር ወር መጨረሻ ገደማ ነው የዩጋንዳ ጦር ወደ ኮንጎ ድንበር የተመመው። ኮንጎዎች ያልጠበቁት ነበርና ተገረሙ። ምክንያቱም ከጦር መሣሪያዎቹ መካከል ቡልዶዘሮች፤ ኤክስካቫተሮች እና የአስፋልት መንገድ መሥሪያ ማሽኖች አብረው ይታያሉ። የጦር ቀጣና በሆነው ምሥራቃዊ ኮንጎ ያለው የተቆፋፈረ ጎዳና እየታሰባቸውም ደስታና እልልታው ቀለጠ። ከድንበሩ ጥቂት ኪሎ ሜትር እንዳለፉ ግን አጀቡ በሙሉ ለመቆም ተገደደ። ሰምሊኪ ወንዝን ለመሻገር ያለችው አነስተኛ የእንጨት ድልድይ ናት። ያ ሁሉ የከባድ ተሽከርካሪ አጀብ ሊሻገርበት አይችልም። ወዲያው ወታደሮቹ ከለላ እየሰጡ የመንገድ መሥሪያ ማሽኖቹ ወደ ግንባታው ገቡ።
የዛሬ 25 ዓመት ነበር በዚህ መልኩ የዩጋንዳ ወታደሮች የኮንጎን ድንበር ዘልቀው የገቡት። ከጎርጎሪዮሳዊው 1998 እስከ 2003 በነበረው ሁለተኛው የኮንጎ ጦርነት ወቅት የዩጋንዳ ወታደሮች ሳይፈቀድላቸው ድንበር ጥሰው የገቡት ወርቅ እና አልማዝን የመሳሰሉ የኮንጎን የማዕድን ሀብቶች ለመዝረፍ ነበር። ዩጋንዳውያን አምስት ዓመታት እዚያ ቆይተው ሲወጡ መንገዱም ሆነ ድልድዮቹ እንደልብ የሚያንቀሳቅሱ አልሆኑም። አሁን ግን የዩጋንዳ ወታደሮች የመጡት በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ነው። በይፋ በተነገረው መሠረት ሁለቱም በጋራ በመሆን ከጎርጎሪዮሳው 2007 ዓም ጀምሮ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የጽንፈኛ እስላማዊው ቡድን የተባበሩት የዴምክራሲ ኃይሎች በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ADF አማጽያንን ለማስወገድ ነው። እንዲያም ሆኖ በዚህ ጊዜ የዩጋንዳ ሠራዊት የኮንጎን መሠረተ ልማት ለማውደም አልተሰማራም፤ እንደውም አሳምሮ ሊገነባ ነው። ይኽንንም በሠራዊቱ ውስጥ የተሰማሩት ዩጋንዳዊ የጦር መኮንን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። እሳቸው እንደተናገሩትም መንገዶችን መገንባቱ ለዩጋንዳ ጦር አስፈላጊ ተግባር ነው።
ጦርነት የጠናባት ምሥራቅ ኮንጎ ደህንነቷ መንገዶች ያስፈልጓታል
በምሥራቅ ኮንጎ የጸጥታ ይዞታውን ለማሻሻል የተመቻቹ መንገዶች ማግኘቷ ወሳኝ እንደሆነ በቤልጂየም አንትቬርፕ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስቶፍ ቲቴካ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉትም የመንገዶቹ በተሻለ መልኩ መንገንባት ግን ለመንግሥታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ላሉት ታጣቂ ኃይሎችም መጥቀሙ አይቀርም። በአካባቢው በርካታ ታጣቂ ኃይሎች እንደሚንቀሳቀሱ ያመለከቱት ፕሮፌሰሩ በመሠረተ ልማቱ ኋላቀርነት ምክንያት የመንግሥት እንቅስቃሴ በአካባቢው ውሱን በመሆኑ ለታጣቂ ቡድኖች የምድረ ገነት ያህል ምቹ እንደሆነም ይገልጻሉ። ያም ሆነ ይኽ በአካባቢው መንገዶቹ መሻሻላቸው አዎንታዊ ጎን እንዳለው ባይካድም፤ በሁለት በኩል የሚዋጋ ጦር መሆኑ ግን አይቀርም ይላሉ።
የተሻሉ መንገዶች ኮንጎ ውስጥ መኖራቸው ለዩጋንዳ ኤኮኖሚ ጠቃሚ እንደሆነ የዩጋንዳ የመጓጓዣ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ሱዛን ካታይሬ ይናገራሉ። «ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ካሉባት ተግዳሮቶች አንዱ መሰረተ ልማቷ ነው። ታውቃለህ ዩጋንዳ ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ጋር ብዙ ንግድ ትሠራለች፤ በርካታ አትክልቶችን እናገኛለን። ሆኖም ግን እዚህ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ይፈጅባቸዋል። እናም በንግዱ በኩል ብዙ ይሠራሉ። ከካሲኖ እስከ ቤኔ ያለው መንገድ በጣም ተሻሽሏል፤ እንደሰማሁት ሦስት ሰዓት ይወስድ የነበረው ጉዞ አሁን 40 ደቂቃ ብቻ ሆኗል። ይኽ ነው ፕሮጀክቱን ቆንጆ የሚያደርገው።» በማለትም በሁለቱ ሃገራት መካከል የንግድ ትስስሩን ለማጠናከር የመንገዶች መሠረተ ልማት ወሳኝ ይገልጻሉ።
የፕሮጀክቱ ታሪካዊ ዳራ
ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በአካባቢው ጠቀም ያለ የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት። የአካባቢው ባለ ከባድ ሚዛን ኤኮኖሚ ኮንጎ በቅርቡ ነው የምሥራቅ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ትብብር አባል የሆነችው። እንዲያም ሆኖ ከዚያ የሚወጣ ጥሬ ሀብት እንጂ ያለቀለት ምርት የለም። ከዩጋንዳ ጋር በሚያጎራብታት የድንበር አካባቢም የነዳጅ ክምችት እንዳላት ይነገራል። ነዳጇን አውጥቶ በዩጋንዳ በኩል ለዓለም ገበያ ያቀርባል የተባለለት የቧንቧ መስመር በግንባታ ላይ ነው። እንቅፋት ግን አለ፤ እስካሁን በግዙፏ ኮንጎ ውስጥ የተዘረጋው መንገድ ከ3000 ኪሎ ሜትር አይበልጥም። ለዚህም ነው ዩጋንዳ በመንገድ ግንባታው ለማገዝ ለኮንጎ ቃል የገባችው። ስልታዊ ፕሮጀክቱም ለኮንጎ ብቻ ሳይሆን የካምፓላ መንግሥትን የውጪ ንግድ እንዲያጠናክር የታሰበ ነው። ሆኖም በዩጋንዳ ታክስ ከፋዮች ገንዘብ የሚገነባው የኮንጎ መሠረተ ልማት ጉዳይ ግን በሀገሪቱ ምክር ቤት ክርክር አስነስቷል። ዩጋንዳ ኮንጎ ውስጥ በቆየችባቸው አምስት ዓመት ለተመዘመረው የወርቅ፤ አልማዝና የእንጨት ምርት ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ገንዘብ እንድከፍል ከ20 ዓመታት በፊት ወስኖባታል። የገንዘቡ መጠን ግን በሁለቱ ሃገራት የጋራ ስምምነት የሚወሰን ነው። ለመንገድ ፕሮጀክቱ የዩጋንዳ መንግሥት የሚያደርገው የገንዘብ አስተዋጽኦ ከካሣ ጋር አይገናኝም ነው የሚሉት የሀገሪቱ የመጓጓዣ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ሱዛን ካታይሬ። «ይኽ የተለየ ስምምነት ነው። ከማካካስ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። »
ከዚህ ይልቅ የመንገድ ግንባታው ለሁለቱም ሃገራት የሚኖረው ጠቀሜታ ላይ ያተኮሩት ቃል አቀባይዋ፤ በአካባቢው የጸጥታ ይዞታው አስተማማኝ መሆን ወሳኝነቱን «DRC ውስጥ መንገዶችን መገንባቱ ስጋቱን ለማስወገድ የሚረዳ ከሆነ ለሕዝቡ በጣም ጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው። ከደህንነት እና ዩጋንዳውያንን ከመጠበቅ አንጻር ከተመለከትከው ደግሞ ቀዳሚ ጉዳይ ይሆናል። ደህንነታችን አስተማማኝ ካልሆነና እርግጠኛ ካልሆንን ሥራ መሥራት አንችልም።» በማለት ገልጸዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ