የደሞዝ ይከፈለን ሰልፍ በዎላይታ
ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2016በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሶዶ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ይከፈለን ሲሉ በአደባባይ ሰልፍ ጠይቀዋል ፡፡ ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት እነኝሁ ሠራተኞች በወረዳው በተለያዩ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ መሆናቸው የሠራተኞቹ ተወካዮች ተናግረዋል ።
ሠራተኞቹ አንዶንዶቹ የሦስት ወራት የተቀሩት ደግሞ እስከ ሁለት ወራት ደሞዝ እንዳልተከፈላቸውና ክፍያው እንዲፈጸም የሚመለከታቸውን አካላት በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አስረድተዋል ፡፡ ያም ሆኖ ጥያቄቸው ምላሽ ባለማግኘቱ አሁን ላይ ችግራቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣታቸውን ነው የሠራተኞቹ ተወካዮች አቶ አሰፋ ጮፍሮ እና አቶ ብረሃኑ ያቆብ ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡በበጀት አዙሪት ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ክልል
የባለሥልጣናቱ ምላሽ
ሠልፈኞቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ለብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤቶች መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ ዶቼ ቬለ የጽህፈት ቤቶቹን ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሃላፊዎቹ ሥልካቸው ጥሪ ባለመመለሱ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ሠራተኞቹ ግን በጽህፈት ቤቶቹ መግቢያ በሮች ላይ ከተሰባሰቡት መካከል ተወካዮቻቸው ብቻ ወደ ውስጥ በማስገባት ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ መደረጉን ተናግረዋል ፡፡ ያምሆኖ ከሥራ ሃላፊዎች የተለየ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ነው ከሠራተኞቹ ተወካዮች አንዱ አቶ ብርሃኑ ያቆብ የገለጹት ፡፡ በተለይም የብልፅግና ጽህፈት ቤት ተወካዩ “ እናያለን ታገሱ “ የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ “ እኛ በረሃብ ላይ እያለን ምን ትዕግስት አለ ፡፡ ምላሻቸው አላረካንም ፡፡ ከዚህ በተረፈ ርዕሰ መስተዳድሩን አላገኘናቸውም ፡፡ ተወካዩ ግን ጥያቄያችንን እሳቸው ከሄዱበት ሲመለሱ እንደሚያቀርቡልን ገልጸውልናል “ ብለዋል ፡፡
የሠራተኞቹ ፈተና
የቀድሞው የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ቀደምሲል የወረዳዎችን በጀት በዋስትና በማሲያዝ በቢሊየን ብር የሚቆጠር የአፈር ማዳበሪ በብድር መውሰዱ አሁን ለተፈጠረው የፋይናንስ ቀውስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ይነገራል ፡፡ ዕዳው በወቅቱ ባለመመለሱና አሁን ላይ ወደ አዳዲሶቹ ክልሎች መተላለፉ ክልሎቹን ለበጀት ቀውስ ዳርጓቸዋል ነው የሚባለው ፡፡ ዕዳው በጊዜው ከወረዳዎቹ ጥቅል በጀት ላይ ሲቀነስ የሠራተኞቹም ደሞዝ አብሮ በመቀነሱ ሠራተኛውን በየጊዜው ደሞዝ አልተከፈለንም ለሚሉ ቅሬታዎች እያዳረገው ይገኛል ፡፡የቀጠለው የሃድያ ዞን መምህራን አቤቱታ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሶዶ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች የዚሁ ችግር ሰለባ ከሆኑት መካከል ናቸው ፡፡ “ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት የሚደርስ ደሞዝ ባለመከፈሉ የተነሳ ቤተሰቦቻችንን ለመመገብም ሆነ ልጆቻችንን ለማስተማር ተቸግረናል” የሚሉት ሠራተኞቹ የአካባቢው መስተዳድርና ገዢው ፓርቲ ምላሽ እንዲሰጣቸው በሠልፍ ጭምር ጥቄያቸውን አቅርበዋል ፡፡
የቅሬታ አቅራቢዎቹ ቀጣይ እርምጃ
አሁን ላይ ደሞዝ ባለመከፈሉ የተነሳ ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብም ሆነ ልጆቻቸውን ለማስተማር መቸገራቸውን የተጠቀሱት ሠራተኞቹ ጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኝ ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ አመልክተዋል ፡፡ ያቀረብነው የደሞዝ ጥያቄ በአጭር ቀናት ምላሽ ያገኛል ብለው እንደሚገምቱ የጠቀሱት የሠራተኞቹ ተወካዮች አቶ አሰፋ ጮፍሮ እና አቶ ብርሃኑ ያቆብ “ ክልሉ ጥያቄያችንን ካልመለሰ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ድረስ አቤቱታችንን የምናቀርብ ይሆናል ፡፡ የዎላይታ ዞን መምሕራን ሥራ ማቆም፣ የትምሕርት ቤቶች መዘጋትየሰራንብትን ነው የጠየቅነው ፡፡ ይህ ካልሆነ የሠራተኞች መተዳደሪያ አዋጅ መሠረት የሰራንበት ክፍያ ባላገኘንብት ሁኔታ ሥራችንን ለመቀጠል እንቸገራለን ፡፡ ይህም ወደ ሥራ ማቆም ውሳኔ ሊያመራ ይችላል “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ