1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደራሲ ውዳላት ገዳሙ «ካህኔዋ»

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 29 2012

«እኛ እቤት ተሰብስበናል። ነገር ግን እነዚህ ሀኪሞች በሀገራችንም ይሁን በዓለም ላይ ያሉ ሀኪሞች እኛን ጋርደው እነሱ ፊት ለፊት ቆመዋል። ኮሮና ከመጣ ወዲህ በፌስ ቡክ ብዙ እጽፋለሁ ። የእነሱን ነገር ሳየው ግን ውስጤ ነው የገቡት። እነዚህ ሰዎች እኮ ነብስ አላቸው ስጋ ለባሲ ናቸው።  ነገር ግን እኛን ብለው ፊት ለፊት ገጥመዋል።»

https://p.dw.com/p/3bu8C
Screenshot Äthiopien Autorin Wudalat Gedamu
ምስል privat

«በዘመነ ኮቪድ 19 የህክምና ባለሙያዎች ሥራ እየተመሰገነ ነው»

ደራሲ ውዳላት ገዳሙ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው አንጋፋ የሴት ደራሲያን መካከል አንዷ ስትሆን በርካታ የግጥም፣ የአጭር ልቦለድና የልጆች መጻሕፍትን ለአንባቢያን አቅርባለች። በሙያዋ ቀደም ሲል መምህር ቀጥላም የህዝብ ግንኙነትና የመረጃ ስርጭት ባለሙያ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአባይ ጣና የብዝሃ ሕይወት የአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሆና በመስራት ትገኛለች።ከእነዚህ መደበኛ ሥራዎቿ ጎን ለጎን ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ ከፍተኛ ፍቅርና ቦታ በምትሰጠው የሥነ-ፅሁፍ ህይወቷ ደግሞ እስካሁን 11 መጻሕፍትን ለአንባቢያን አቅርባለች።
ደራሲዋ ለህትመት ባበቃቻቸው መጻሐፎቿም ይሁን በተለያዩ መፅሔቶች ጋዜጦችና የሥነ-ፅሁፍ መድረኮች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ስታነሳ ቆይታለች። ስለሕይወት፣ ስለሀገር ፍቅር ፣ ስለቤተሰብ፣ ስለማህበራዊ ኑሮ ወዘተ ብዕሯ ያልዳሰሰው ርዕሰ ጉዳይ የለም። ከሰሞኑ ደግሞ «ካህኔዋ» በሚል ርዕስ የዓለምን ሕዝብ ስጋት ላይ የጣለውንና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ በግንባር ቀደምትነት እየተፋለሙ ለሚገኙት የጤና ባለሙያዎች መታሰቢያ እንዲሆን አንድ ግጥም እንካችሁ ብላለች።
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች እየሰሩት ባለው የሕይወት አድን ሥራ በመላው ዓለም ዝነኞች እየሆኑና ከፍተኛ አድናቆት እየተቸራቸው ነዉ። በስማቸው የሚነቀሱ፣ በቲዩተርና በሌሎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የአድናቂዎች ክለብ የሚመሰርቱም አሉ። በቅርቡም ከኮቪድ-19 በሽታ ያገገሙት የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ሳይቀሩ አዲስ ለተወለደው ልጃቸው ያስታምሟቸው የነበሩ ሁለት ዶክተሮችን ስም ሰጥተውታል ። ደራሲ ውዳላት ገዳሙም የጤና ባለሙያዎቹ ልብ የሚነካ ተግባር ግጥሙን ለመጻፍ እንዳነሳሳት ትገልፃለች።
«እኛ እቤት ተሰብስበናል። ነገር ግን እነዚህ ሀኪሞች በሀገራችንም ይሁን በዓለም ላይ ያሉ ሀኪሞች እኛን ጋርደው እነሱ ፊት ለፊት ቆመዋል። ከዚህ በሽታ ጋር ፊት ለፊት ቆመዋል። ኮሮና ከመጣ ወዲህ በፌስ ቡክ ብዙ እጽፋለሁ ። የእነሱን ነገር ሳየው ግን ውስጤ ነው የገቡት። እነዚህ ሰዎች እኮ ነብስ አላቸው ስጋ ለባሲ ናቸው።  ነገር ግን እኛን ብለው ፊት ለፊት ገጥመዋል። እኛ ተራራቅ ስንባል፣ እጅ ታጠቡ ስንባል ምንም ለማንከፍልበት ከብዶናል። እነዚህ ሰዎች ግን ትልቅ የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ ስለሆነ፤ ከውስጤ የመጣ ነው።»ብላለች።
ወረርሽኙን ለመከላከል ከእንቅስቃሴ ተገድበው ቤት ለተቀመጡ ልጆችና ወላጆችም ደራሲዋ በግሏ መጻሕፍትን በመለገስ የበኩሏን እየተወጣች ነው። የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በተቋቋመው ብሄራዊ የኪነጥበብና መገናኛ ብዙሃን ፀረ-ኮቪድ ግብረ-ኃይል አባል ሆና በመሥራት ላይ ስትሆን በቅርቡ በተካሄደው ተመልካች አልባ የኪነ ጥበብ ኮንሰርት ላይም ተሳታፊ ነበረች። በእንዲህ አይነቱ ወቅት የኪነ-ጥበብ ሰዎችም ልክ እንደ ጤና ባለሙያዎች ሕዝብን የበለጠ ማገልገል አለባቸው የሚል እምነትም አላት።
« እኔንም ሆነ ሌሎቻችንን የኪነ ጥበብ ሰዎች ይህ ሕዝብ ሲሞሽረንኖሯል። መጻሐፎቻችንን፣ ፊልሞቻችንን፣ ሥዕሎቻችንን ይክፋም ይልማም እየገዛ እየሸመተ ሲያበረታታን ሲሸልመን ኖሯል። አሁን ደግሞ እሱ አደጋ ላይ ነው። ስለዚህ እኛ ምንድነው ማድረግ  ያለብን የሚለውን ማሰብ አለብን።» በማለት የኪነ ጥበብ ሰዎች ኅብረተሰቡን እንዲያስተምሩና እንዲያበረታቱ አሳስባለች።
ደራሲ ውዳላት ገዳሙ የመጀመሪያ የግጥም መድብሏን በ1996 ዓ/ም «እናትና ልጅ» በሚል ርዕስ ለህትመት ያበቃች ቢሆንም፤ ግጥም መጻፍ የጀመረችው ግን ተወልዳ ባደገችበት በቀድሞው አጠራር ጎጃም ክፍለ ሀገር በአሁኑ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቸና ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በልጅነት ዕድሜዋ ነበር ። በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች በርካታ የሥነ-ፅሁፍ ሥራዎቿን ስታቀርብ መቆየቷን የምትናገረው ደራሲዋ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪዋን የያዘችበት የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ደግሞ ከአንጋፋ ፀሐፊያን ጋር ለመገናኘት እንዲሁም ግጥሞቿን ወደ መድረክ ይዛ ለመውጣት መንገድ ከፍቶላታል።
«በ19 86 ዓ/ም አካባቢ ከባሕርዳር እንደመጣሁ ግቢ ውስጥ ከጓደኞቼ ከገጣሚ ፊርማዬ ዓለሙና ከገጣሚ አረጋሽ ሰይፉ ጋር እንገናኝ ነበር። እነሱ ናቸው ወደዚህ ያስገቡኝ።» በማለት ታስታውሳለች።
የዜማ ብዕር ኢትዮጵያና የሴት ደራሲያን ማሕበርን ከመሰረቱት መካከል አንዷ ስትሆን በምክትል ፕሬዝዳንትነትና በፕሬዘዳንትነትም አገልግላለች። በእነዚህ ማሕበራት አማካኝነት ወጣት ደራሲንን በማበረታታት ላይ መሆኗንም አጫውታናለች።
«ዓለም ከሰጠችን ክፉ ነገር ይልቅ የሰጠችን በጎ ነገር ይበዛል» የሚለው የሕይወት ፍልስፍናዋ ከእናትነት ፀጋ ጋር ተዳምሮ ልጆችን በበጎ ነገር መቅረፅ የሁል ጊዜ ምኞቷ ነው። ከዚህ የተነሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አትኩሮቷን ወደ ልጆች መጻሕፍት አዙራለች። ማኅበረሰቡን ለማገልገል በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይም በመሳተፍ ላይ ነች።
«ሙሉ ለሙሉ ከባሁ ባልልም ቀደም ባሉት ዓመታት ጀምሮ ሜሪ ጆይ ጋር በጣም እሠራለሁ።» ካለች በኃላ «ከዚያ ሁሉ በላይ ግን የልብ ባይሞላም በሰፈሬ ላሉ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ይህ ከምንም የመነጨ ሳይሆን፤ ከታዋቂነት፣ ከፀሐፊነት ሳይሆን እናት ከመሆን ፣ኢትዮጵያዊ ከመሆን ከምንም በላይ ሰው ከመሆን የሚመጣ ነው።» ብላለች።
ኅብረተሰቡም በመደጋገፍና በመተሳሰብ እንዲሁም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረግ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል እንዳለበት ደራሲ ውዳላት ገዳሙ ያሳሰበች ሲሆን ፤በዚህም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አርአያ እንዲሆኑ ምክር ለግሳለች። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

Äthiopien Autorin Wudalat Gedamu
ምስል privat
Äthiopien Autorin Wudalat Gedamu
ምስል privat