የደቡብ አፍሪቃ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እወጣለሁ አልወጣም ዉዝግብ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 21 2015የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፊታችን ነሐሴ መገባደጃ ላይ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አምስት ሃገራት በሚሳተፉበት ጉባዬ ላይ ለመገኘት ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንደሚጓዙ ተገለፀ። ይህን ተከትሎ ደቡብ አፍሪቃ ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት እወጣለሁ አልወጣም መልስ ዉዥንብር ዉስጥ ከቷት ነዉ የሰነበተዉ። «ብሪክስ» በሚል አህጽሮት የሚጠሩት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኙ አምስት ሃገራት ማለትም ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ በዓመቱ መገባደጃ ላይ ደቡብ አፍሪቃ ላይ ይሰበሰባሉ። ደቡብ አፍሪቃ የሩስያዉ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋብዛለች። ይሁን እና ደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) ሩስያ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ህጻናትን በሕገ-ወጥ መንገድ ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ናቸው ሲል የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸዉን የሩስያዉን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲንን ለ ICC አሳልፋ እንድትሰጥ ጥሪ ማቅረቡን ችላ ያለችዉ ሆኖ ታይቷል። የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ፓርቲ የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግረንስ የANC የአቋም በመንግስት ውስጥ ራስ ምታትና ግራ መጋባት ያስከተለም ይመስላል።
ባለፈዉ ማክሰኞ የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በደቡብ አፍሪቃ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት ከፊንላንድ ፕሬዝዳንት ሳውሊ ኒኒስቶ ጋር በሰጡት መግለጫ፥ ደቡብ አፍሪቃ ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) መውጣት አለባት ሲሉ ተደምጠዋል። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) ለተወሰኑ ሀገራት ኢፍትሃዊነቱን ማሳየቱን ተከትሎ ገዥው የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግረንስ (ANC) ከዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ለመውጣት መወሰኑን ነበር ራማፎዛ በመግለጫቸው የተናገሩት።
ይኸው የፕሬዚዳንቱ አቋም ከፓርቲው ብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ በገዥዉ የአፍሪቃ ናሽናል ኮንግረንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊኪሌ ምባሉላ በተለያዩ ሚዲያዎች ተገልጿል።
ይሁን እና አሁን የፕሬዚዳንት ራማፎሳ ቢሮ የተለየ አቋሙን ይዞ መግለጫዉን በፕሬዚዳንቱ ቃል-አቀባይ ቪንሰንት ማግዌኒያ በኩል ወደሚዲያ መቷል፤
« ባለፈዉ ዓመት ታኅሣሥ ወር 2022 ዓም ላይ በተካሄደው 55ኛው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ በተላለፈዉ ዉሳኔ መሰረት ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ለመውጣት የተያዘው እቅድ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፤ ደቡብ አፍሪቃ፣ የድርጅቱ ፈራሚ ሃገር ሆናም ትቀጥላለች። ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጉባኤም የባለፈው አመት ውሳኔ እንዲጸና ነው የተወሰነው»
በመቀጠል ደቡብ አፍሪቃን ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) በአፋጣኝ ለማውጣት አፍሪቃ ናሽናል ኮንግረንስ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳልወሰነ የፓርቲዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀደም ሲል የሰጡትን አስተያየት በሚሽር መግለጫዉ ይዘዉ በመዉጣት አስረድቷል።
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ፤ ፓርቲው ባለፈዉ ዓመት ታህሳስ ወር ባካሄደዉ ጉባኤ ደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል ሆና እንድትቀጥል እና ከውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ለማድረግ እንድትገፋፋ መፍትሄ ማገኘቱንም አስረድተዋል።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ሲፋምላንድላ ዞንዲ እንደሚሉት ደቡብ አፍሪቃ ከ ICC ብትወጣ እንኳ ለአንድ ዓመት ሙሉ ደንቦችን ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለባት።
«ደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) አባል በሆነችበት ወቅት የነበሩባትን ግዴታዎች ሁሉ ታሟላለች፤ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከወጣች በኋላ እንኳ ግዴታዎቹ ሁሉ ተግባራዊ ማድረጓ ይቀጥላል። እናም ያለመከሰስ መብት እና ሌሎች ጉዳዮች እንዴት መደረግ እንዳለበት እና እንደምንችል በመላው ዓለም የተገለፀ ጉዳይ ነዉ።»
የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባለፈው መጋቢት ወር በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎም ይሄው ጉዳይ ዳግም ማነጋገሩን ቀጥሏል።
ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞች እና ባለሙያዎች እንደሚሉት ፑቲን ደቡብ አፍሪቃ ቢመጡ ሀገሪቱ ፑቲንን ከማሰር በስተቀር ሌላ አማራጭ የላትም። ይሁን እና ደቡብ አፍሪቃ ይህን ማድረግ ትችላለች የሚለዉ ጥያቄ ትልቅ ጥያቄ ነዉ። ምክንያቱም በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የእስር ማዘዣ ያወጣባቸዉ የቀድሞ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል-ባሻር እንደ ጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር በ 2016 ደቡብ አፍሪቃ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ በተገኙበት ወቅት ሀገሪቱ አልበሽርን መያዝ እና አሳልፋ መስጠት አለመቻልዋ የሚታወስ ነዉ።
ከሞስኮ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያላት ደቡብ አፍሪቃ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ጦርነቱን አላወገዘችም በሚል ቅሬታ በደጋጋሚ ተሰምቶባታል። ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ወታደራዊ ልምምድ በማድረግም አሰላለፏን በግልጽ አሳይታለች ተብላ ትተቻለች። ደቡብ አፍሪቃ ግን በጦርነቱ ገለልተኛ አቋም እንዳላት በመግለጽ በማስተባበልዋን እንደቀጠለች ነዉ።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ