የዳግም ጦርነት ስጋት፣መዘዙና ሰላማዊ መፍትሄው
እሑድ፣ ግንቦት 14 2014የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ጋብ ያለ ቢመስልም ከመንግሥትም ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት በኩል የወረራና ጥቃት ውንጀላዎች እንዲሁም የተለያዩ ዛቻዎች መሰንዘራቸው አልቆመም። በጦርነቱ ጣልቃ ገብታለች የምትባለው ኤርትራም የውንጀላውና የዛቻው አካል ሆናለች። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሦስቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን ለዳግም ጦርነት ዝግጅት በማድረግ እየከሰሱ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ሊሰነዘርበት ለሚችል ማናቸውም ጥቃት ዝግጁ መሆኑን ገልጧል። ህወሓትም በበኩሉ አይቀሬ ላለው ጦርነት ህዝቡ እንዲዘጋጅ አዟል። የትግራይ ኃይሎች «የመጨረሻ» ላሉት ወታደራዊ ዘመቻ እየተዘጋጁ እንደሆነ ሚስጥር አይደለም ያለችው ኤርትራም ነጻነትዋንና ሉዓላዊነትዋን የምታስጠብቅ መሆንዋን አስታውቃለች። ውንጀላና ዛቻው በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት ከዚህ ቀደም በአፍሪቃ ኅብረትና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚሰማ ነገር የለም። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንንና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን የጦርነት ነጋሪት ጉሰማው እንዲቆምና የሰላም አማራጮች ላይ እንዲተኮር እያሳሰቡ ነው። በኢትዮጵያ የዳግም ጦርነት ስጋት መዘዙና ሰላማዊ መፍትሄው የዛሬው እንወያይ ትኩረት ነው። በዚህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ አራት እንግዶችን ጋብዘናል። የኢትዮዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሕግና ፖሊሲ ክፍል ሃላፊ ታሪክዋ ጌታቸው ፣የሕገ መንግሥትና የዴሞክራሲ ግንባታ አጥኚና አማካሪ ዶክተር አደም ካሴ ፣ ዶክተር ደመላሽ መንግስቱ በጂማ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒክሽን መምህርና የግጭት አፈታት ተመራማሪ እንዲሁም ዶክተር ታደሰ አክሎግ በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ናቸው።
ኂሩት መለሰ