የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የማድቡርጉን ጥቃት ለመመርመር ቃል ገቡ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 13 2017የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በማድቡርግ ከተማ በገና የገበያ ስፍራ ለደረሰው እና ለአምስት ሰዎች ሞት እንዲሁም ከ 200 በላይ ሰዎች መጎዳት ምክንያት የሆነውን በመኪና በመግጨት በተፈፀመ ጥቃት የጸጥታ አካላት አስቀድመው መከላከል ይችሉ ነበር ወይ የሚለውን ለማጣራት ቃል ገቡ ።
የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር እና የሀገር ውስጥ እና የውጭ የስለላ አገልግሎት ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡበት የፊታችን ጥር 1 ቀን 2017 ዓ ም ፓርላማ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሀገር ውስጥ ሚንስትሯ እና የደህንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎቹ ፓርላማ የሚቀርቡት ሁለት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት መልስ እንዲሰጥበት ከጠየቁ በኋላ ነው ተብሏል።
በከተማዋ የደረሰውን የተሽከርካሪ አደጋ ፈጽሟል ተብሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ሳዑዲ አረቢያዊ የስነ አዕምሮ ሀኪም ጣሊብ አል አብዱልሞሀሰን የጀርመን ዜጎችን ለመግደል ይዝት እንደነበር ከኢንተርኔት የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል። በተጨማሪም የ50 ዓመቱ ግለሰብ አስቀድሞ ፍርድ ቤት የቀረበበት ጉዳይ እንደነበረው እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።
ዴር ሽፒግል የተባለ አንድ የጀርመን ጋዜጣ የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የሳዑዲ ሚስጥራዊ አገልግሎት ከአንድ ዓመት በፊት ለጀርመን የስለላ መስሪያ ቤት BND አብዱልሞሀሰን በቲውተር ገጹ ጀርመንን ለማስፈራራት ያሰፈረው መልዕክት በጀርመን ላይ አደጋ ይዞ ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቆ እንደነበር ነው።
በተጨማሪም ተጠርጣሪው ግለሰብ ባለፈው የነሐሴ ወር በማህበራዊ የመገናኛ ገጾቹ ላይ ባሰፈራቸው ጽሁፎቹ «በጀርመን ፍትህን ለማግኘት ኤምባሲዎቿን ከማፈንዳት እና ዜጎቿን ከመግደል ያለፈ መንገድ ይኖር ይሆን?» ሲል መጻፉም ተመላክቷል።
የሀገር ውስጥ ሚንስትሯ ይህንኑ በተመለከተ እንዳሉት « "የምርመራ ባለስልጣናት ከጥቃቱ በፊት ምን አይነት መረጃ ነበራቸው የሚለውን ጨምሮ ምን አይነት ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ሁሉንም ዳራዎች ያብራራሉ» ብለዋል።
የደህንነት ምንጮችን ጠቅሶ ሌላው ዕለታዊ ጋዜጣ ዲ ቬልት እንደዘገበው ደግሞ የጀርመን ግዛት እና የፌደራል ፖሊስ ባለፈው አመት አብዱልሞሀሰን ላይ “የአደጋ ግምገማ” ቢያካሂዱም “ምንም የተለየ አደጋ” የሚያስከትል ነገር የለም በማለት ደምድመዋል።
ታምራት ዲንሳ
ልደት አበበ