1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ዜግነት ያገኙ የውጭ ዜጎች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 12 2003

በጎሮጎሮሳውያኑ 2010 ዓ.ም የጀርመን ዜግነት የተሰጣቸው የውጭ ዜጎች ቁጥር ከአምናው መጨመሩን የፌደራል ጀርመን የስታትስቲክስ ቢሮ አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/Raeh
ምስል picture-alliance/dpa

በመስሪያ ቤቱ መግለጫ መሠረት ዜግነት ካገኙት አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን በተለይም ቱርኮች ናቸው ።እ.ጎ.አ በ 2010 ዓ.ም ፣ 101,600 የውጭ ተወላጆች የጀርመን ዜግነት አግኝተዋል ። ይህም ከዚያ በቀደመው ዓመት የጀርመን ዜግነት ከተሰጣቸው የውጭ ዜጎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ5 ሺህ ያህል ገደማ ከፍ ያለ ነው ። በቀደሙት ዓመታት ግን ለዜግነት የሚያመለክቱም ሆነ ዜግነት የሚያገኙ የውጭ ዜጎች ቁጥር ቀንሶ ነበር ። ለዚህም እንደ አንድ አብይ ምክንያት ሆኖ የሚነሳው ከዛሬ 3 ዓመት አንስቶ የዜግነት ጥያቄ የሚያቀርቡ አመልካቾች እንዲያሟሉ የሚጠየቁት ተጨማሪ ግዴታ ነው ። እ.ጎ.አ ከመስከረም 2008 ዓ.ም አንስቶ የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ መመዘኛ እንዲሁም የጀርመንን ታሪክና የመንግሥትን አወቃቀር የተመለከቱ ጥያቄዎችን ያካተተ ፈተና ማለፍ አንዱ ለጀርመን ዜግነት የሚያስፈልግ ቅድመ ግዴታ ሆኗል ። በአንዳንዶች አባባል ጀርመናውያን እንኳን በቅጡ ሊመልሷቸው የማይችሉ ከባድ ጥያቄዎችን ያካተተው ይኽው ፈተና የውጭ ዜጎች ለዜግነት እንዳያመለክቱ እየገፋቸው መሆኑን እ.ጎ.አ በ 2009 የአመልካቾች ቁጥር መቀነሱን መነሻ ያደረጉ ዘገባዎች አመልክተዋል ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኃላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ