የጀርመን የጥንድ ዜግነት ደንብ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2005በጀርመን ለተወሰኑ ሃገራት ዜጎች ብቻ ፣ የሚፈቀደው «ጥንድ ዜግነት» ለብዙ ዓመታት ሲያከራር የቆየ ና አሁንም የሚያነጋግር ጉዳይ ነው ። በጀርመን ጥንድ ዜግነት መያዝ ፣የውጭ ዜጎች በሙሉ መበት ሊሆን ይገባል የሚሉት በአንድ ወገን ፤ የጀርመንን ዜግነት የመረጠ ሌላ ተጨማሪ ዜግነት ሊይዝ አይገባም የሚሉት በሌላ ወገን ክርክራቸው እንደቀጠለ ነው ። ከ2 ሳምንት በፊት በጀርመን የውጭ ዜጎች ድርብ ዜግነት እንዲይዙ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ለጀርመን ፓርላማ ቀርቦ ነበር ። ይሁንና በፓርላማው አብላጫ ድምፅ ያላቸው ወግ አጥባቂዎች ለረቂቁ ድምፅቸውን ባለመስጠታቸው ሕጉ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል ። ያብራሩልናል ።
ዋነኛው ተቃዋሚ የጀርመን ሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ ና የአርንጓዴዎቹ ፓርቲ የረቂቁ ደጋፊዎች ናቸው ። እነዚህ ፓርቲዎች ሥልጣን በያዙበት እ.ጎ.አ በ1990 ዎቹ መጨረሻ ላይ የዜግነት ህግን ለማላላት ቃል ገብተው ነበር ። የረቂቅ ህጉ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በየበኩላቸው የሚያቀርቧቸውን የመከራከሪያ ሃሳቦች በርሊን ነዋሪ የሆኑት የምጣኔ ሃብት ምሁር ዶክተር ፀጋዮ ደግነህ ያብራሩልናል ።በጀርመን የጥንድ ዜግነት ክልከላ የውጭ ዜጎችን በሙሉ አይመለከትም ። እጎአ በ2ሺህ በተሻሻለው የጀርመን ህግ መሰረት ጀርመን ውስጥ ከውጭ ዜጎች የተወለዱ ልጆች 23 አመት እስኪሞላቸው ድረስ የወላጆቻቸውንና የጀርመን ዜግነት ይዘው መቆየት ይችላሉ ከ23 ዓመት በኋላ ግን አንዱን ዜግነት መምረጥ አላባቸው ። የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎች አሜሪካውያን የስዊትዘርላንድ ዜጎች ጥንድ ዜግነት መያዝ ይፈቀድላቸዋል ። በዚህ ሳቢያም አሁን የሚሰራበት የጥንድ ዜግነት አሰጣጥ ደንብ በአድሏዊነት ይተቻል ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ግን በዚህ አይስማሙም ።
ዶክተር ለማ እንደሚሉት ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውጭ የሚመጡ ዜጎችም ቢሆኑ ጥንድ ዜግነት መያዝ የሚያስችሏቸው ሌሎች ሁኔታዎችም አሉ ።ምንም እንኳን በጀርመን በተጠቀሱት ምክንያቶች ጥንድ ዜግነት መያዝ ቢፈቀድም ይህ ሊሳካ የሚችለው ዜግነቱን ይዞ መቆየት የሚፈልገው አመልካች ትውልድ ሀገር በዚህ ረገድ ከጀርመን ሕግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የህግ አንቀፅ ካለው ብቻ ነው ። ዶክተር ፀጋዮ ደግነህ እንደሚሉት የጀርመን ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ በኢትዮጵያ የዜግነት ህግ ምክንያት የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን አይችሉም ። የሁለቱ ሃገራት ህግ በመለያየቱ ወይም በሁለቱ ሃገራት መካከል ልዩ ስምምነት ባለመኖሩ ምክንያት የኢትዮጵያንም የጀርመንንም ዜግነት በአን ድ ላይ መያዝ ባይቻልም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ልዩ መታወቂያ ዜግነትን ባይተካም የሚበረታታ ነው እንደ ዶክተር ለማ ።ዶክተር ፀጋዮ ደግሞ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ልዩ መታወቂያ መሰጠቱ ጥሩ ቢሆንም ከዚህም የተሻለ ህግ ሊወጣ ይገባል ይላሉ ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ